አባወራውን በምን እንለየው?(ለእህቶቼ ብቻ)

ማስታወሻ!

ቅዳሜ ዕለት ተዘጋጅቶ በነበረው የአባወራዎቹ መድረክ ላይ ጥቂት እህቶቼ ለመሳተፍ ፈልጋችሁ ነበር። ይኹን እንጂ መድረኩ ለወንዶች ብቿ በመደረጉ ቅሬታችሁን በግልጽ ነግራችሁኛል።

የፌስቡክ ገጼ(ምንም እንኳ አኹን አኹን ሪፖርት እየተደረገበኝ ብቸገርም) እንዲሁም ድረገጼ (እርሱም ፌስቡክ ላይ ሼር እንዳላደርገው abusive ቢባልብኝም) በሁለቱም አማራጮች ያለጾታ ገደብ  መልዕክቶችን ለመለዋወጥ ይበቃሉ ብዬ አስባለሁ።

ይኹንና መድረኩ ላይ ለመሳተፍ ፈልጋችሁ ለነበራችሁት እህቶቼ መድረኩ ሙሉለሙሉ ለወንዶች የቀረበ ነበርና ለእናንተ ትኾን ዘንድ ግን ራሴን እንደታላቅ ወንድማችሁ ቆጥሬ ይኽችን ልዩ የምክር ጦማሬን እነኋት እላችኋለሁ።
==================================

ውቢቷ!

አኹን ባለንበት ዘመን ትዳር ለብዙዎች ዘላቂነቱ አስፈሪ የኾነ ተቋም ኾኗል። በተለይም ተፈጥሮኣዊ የኾነውን ጠባያችንን እየካድን የማያሳርፉንና ደመነፍሳዊ የኾኑትንም ፍላጎቶቻችን መግዛት እያቃተን ለእነርሱም እየተንበረከክን በመጣንበት ወቅት ጾታዊ ባሕርይ፣ ጠባይ እና ሚና ተዘበራርቆብናል።

ትውልዱ ተፈጥሮውን በ”መሰለኝ” ተቀብሎ፣ በ”ተመቸኝ” ይመራዋል። ከዚኽም የተነሳ እርሱ ምን እንዳለው፣ ምን እንደሚፈልግና ከማንስ እንደሚያገኘው ግራ ተጋብቷል። ነገር ግን አላውቅም እንኳ ሳይል በእውር ድንብር ይጓዛል(ሁሉን አውቃለሁ ማለት ከሊቅ እስከ ደቂቅ ወቅታዊ አባዜ መኾኑን ልብ ይሏል)።

አንቺ የውብ ዳር! እህቴ አንቺ ግን አስተውይ!

መቼም ጊዜያችን መክፋቱን ላንቺ መንገር ለቀባሪ ማርዳት ይኾንብኛል። ለቀጣዩ ትውልድ የምትመች ሀገርን ለማስረከብ፤ የምትመሠርችው ቤተሰብ ጤናማነት ትልቁን ሚና ይጫወታል። ጤናማ ቤተሰብ ለመመሥረት ደግሞ ተመክሮ፣ ተገስጾ እና ተቀጥቶ(ግብረገብ ኾኖ) ባደገው ማንነትሽ ላይ ለትዳር አጋርነት የምትመርጪው ወንድ ይወስናል።

ስለዚህም ከዚህ በታች ለጊዜው መሠረታዊ ናቸው ብዬ ያስቀመጥኩልሽን አራት ነጥቦች ታዘቢያቸው። አብረውሽ ካሉት ወንዶች መካከል ኹነኛውን ትመርጪበት ዘንድ ያግዙሻልና።
=======================================

ውዷ እህቴ!

አንድን ወንድ ለማጨት ስታስቢ እነዚህን አስታውሺ፦
1ኛ. ርዕይ ያለው
2ኛ. ቃሉን የሚጠብቅ
3ኛ. ስሜቱን የሚቆጣጠር
4ኛ. ወንዳወንድ አካሉን የሚጠብቅ……..እነዚኽና ሌሎችም በተለያየ ጊዜ የጠቀስኳቸው አንድን ወንድ በእኔ ዐውደ ንባብ “አባወራ” ያሰኙታል።

1ኛ. ርዕይ ያለው
አንድን ወንድ ልጅ ከምንም በላይ ሕይወቱን ትርጉም ያለው ኑሮውንም ለአንድ ዓላማ በስርዓት የተገራ የሚያደርግለት የሚኖርለት ርዕይ የሰቀለው ዓላማ ሲኖረው ነው። ቤቱን፣ መንደሩን፣ ሀገሩን የሚለውጥ ሕልምን ሳይሰንቅ እንዲሁ በዋል ፈሰስ የሚባዝን ከኾነ እርባና ቢስ ነው። እርሱም ለሚስቱ ሸክም፣ የማሕበረሰቡ ቁስል፣ የትውልድ መረን፣ የሀገሩ ሕመም ይኾናል።

አንቺ የውብ ዳር ስሚኝማ፤ ምን አፉ ቢጣፍጥ፣ ገንዘብ ቢኖረው፣ ባለስልጣንም ቢኾን የመጣበትን አውቆና ይዞ መድረሻውንም ወስኖ ከራሱ(ከኾዱ) አልፎ ለቤቱ፣ ለማሕበረሰቡ፣ ለሀገሩ ለመትረፍ ወደፊት ከማይዘረጋ ወንድ አንሶላ የመጋፈፍሽ ነገር አይታየኝም።

ዘንድሮ ወንዱን ስትታዘቢው ሁሉ ደርሶ “ካላንቺ መኖር አልችልም”፣ “ሲያምሽ ያመኛል” …… ባይ ነው። ውዷ እህቴ! በጭራሽ እልሻለሁ ሕይወቱን አንቺ ኑሮውም አንቺ የኾንሽበት ወንድ ስታገኚ ተወድጃለሁ አትበይ። የኽ ሰው ባልነቱ ቀርቶ ለምን እንደሚኖር እንኳ ያለገባው ለአቅመ አዳምም ያልደረሰ ከርሞ ጥጃ እንጂ።

ዘወትር “ላም አለኝ በሰማይ …..” ዓይነት ወሬ የሚያወራ፤ ሲተርከው በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሀብት የሚያሳፍስ ሕልም ያለው፤ ነገር ግን እርሱን እውን ለማድረግ ይቅርና የእለት ጉርሱን የሚያገኝበትን ሥራ እንኳ ለመሥራት ጠዋት በመከራ እየተበሳጨ የሚነሳ፤ የእረፍት ቀኑን ተኝቶ የሚውል፤ የሀገሩ “ድህነት” የመንግስቱም “ክፋት”  እንጂ የእርሱ ሕልምም ኾነ እርሱ ምርጥ እንደኾኑ እየደሰኮረ ክትፎ ከሚጋብዝሽ ወንድ ራቂ።

አንድን ወንድ “ቤተሰብ መመሥረት ያስችለኛል፤ እኔም ኾንኩ ልጆቼ እናተርፋለን?” ወይ ስትይ ካሰብሽው፦ ርዕዩ እንቅልፍ የሚነሳው፣ ኤሌክትሮኒክስ በኾነው ድድ ማስጫ(ማሕበራዊ ሚዲያ) ላይ ተጥዶ ፎቶ እየለጠፈ ለእያንዳንዱ ላይክ “አመሰግናለሁ” ለማለት ጊዜ የሌለውና በርዕዩም የማይደራደር ቆራጥ መኾኑን ፈትሺ ።

2ኛ.ቃሉን የሚጠብቅ…..ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *