አባወራው በሚስት መረጣ(ካለፈው የቀጠለ)

፪ በሴታቆርቋዡ (Feminism) ያልተመረዘችውን ምረጥ

አባወራው በሚስት ምርጫው የአባቷን ልጅ እንዲያስቀድም አንብበናል አኹን ደግሞ የዘመናችን በሽታ በኾነው ሴታቆርቋዥ(Feminism) አለመታመሟን ማረጋገጥ አለበት።

አንዲት ሴት በዚህ በሽታ ስትለከፍ የመጀመሪያውና ዋነኛው ምልክቷ መለኮታዊ የኾነውን የፈጣሪን ትዕዛዝ መሻር ነው። የወንድ ልጅ የቤቱ መሪነት ሲነሳ ያንገሸግሻታል።

“እርሱ ማን ነው፦እንዲህ አትልበሽ፣ በዚህ አትለፊ፣ በዚህ ሰዓት ግቢ፣ የሚለኝ እኔ በምን አንሼ ነው ” በማለት ተፈጥሮኣዊውን የወንድ ልጅ መሪነት አትቀበልም።

እንዲህ ዐይነቷ ሴት ወንድን የምትፈልገው ለወጪ መጋራት ነው። ወጪዎቿን በደንብ መሸፈን ስትችል ወንድ አትፈልግም። ለእርሷ የትዳር ዐላማ በእርሱም ውስጥ ያለ ትኅትና አይገባትም።

ልብ አድርግ! ብዙ ሴቶች ጭምት፣ ጠባየኛ፣ መንፈሳዊ፣ ትኁት መስለው ይታያሉ። በማሕበራዊ ድረ ገጽ የሚለጥፉትንም ፎቶም ኾነ ጽሑፍ ይኼን እንዲገልጽላቸው ይፈልጋሉ።

እኔ ግን እልሃለሁ እነዚህን ወደ ጎን ተውና ባንተ መሠረታዊ የፍላጎት መሥፈርት ላይ የአባቷ ልጅ መኾኗንና በሴታቆርቋዡ(Feminism) አለመለከፏን ከማሕበራዊ ድረገጽ ውጣና በአካል አግኛትና አረጋግጥ። መኾንና መምሰል ፍጹም ይለያያሉና።

አንተ ደግሞ ባዝነህ መጥፋት የሌለብህ ፈጣሪህ በምክንያት ለዓላማ የፈጠረህ፤ በሴታውልነት ልትባክን የማይገባህ በደም ዋጋ የተገዛህ፤ አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍሰው ያቆዩልህን የአባቶችህን አደራ የተሸከምክ፤ እርሱንም በማስቀጠል የተጠመድክ ውድና ክቡር ፍጥረት ነህ።

የሴት ምርጫህ ያንተን ሕይወት፣ የትውልድህን ርዕይ፣ የሀገርህን ሕልውና ይወስናል። ስህተትህ ቤትህን፣ ትውልድን፣ ሀገርን ያጠፋልና ከስሜታዊነት ወጥተህ ምክንያታዊ ኹን።

የአባቷን ልጅ እንዴት እለያለሁ?

ከፈጣሪ የተሰጠህን ዓላማ ይዘህ በምድራዊ ሕይወት የምታግዝህን ሴት ለመምረጥ አትፍራ። በማሕበራዊ ድረገጽ ረጅም ጊዜ ከማጥፈፋትም በአካል አግኛትና “ትኾነኛለች አትኾነኝም” ብለህ ወስን ይኽ ላንተም ኾነ ለእርሷ እረፍት ነው።

የተዋወቅሃትን ሴት ከአባቷ ጋር ስላላት ግንኙነት በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ መጠየቅ ነገሩን ቀላል ያደርገዋል።
ስለአንተ አባት አንስተህ ስለእርሷ አባት እንድትነግርህ መንገድ መክፈት ትችላለህ። ቤታቸው ውስጥ ማንን እንደምትፈራ፣ ለምን፣ ውሳኔ ማን እንደሚሰጥ፣ ስታጠፋ፣ ስታመሽ፣ ማን እንደሚቀጣት፣ ተቀጥታ ታቅስ እንደኾነ፣ ለመጨረሻ ጊዜ የተቀጣችበት ጊዜ፣ ማን እንደቀጣት፣ የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ “አባቴ” ከኾነ ጥሩ ነው፤ “እናቴ” ከኾነ ግን ምርጫህን እንደገና ብታስብበት ይሻላል።

የአባቷ ልጅ ካልኾነች ስለአባቷ ማንሳት አትወድም፣ ስለአባቷ መልካም ትዝታ የላትም። ይኽ ማለት ደግሞ ለወንድ ያላት አመለካከት ጤናማ አይኾንም። ለሥርዓት ተገዢ አይደለችም።

በአንጻሩ ደግሞ “አባቴን እወደዋለሁ እንደፈለኩ እንድኾን ነጻነት ይሰጠኛል” ስትልህም አስብበት።

***የአባቷ ልጅ የኾነችው ግን ስለ አባቷ አውርታ አትጠግብም። ወሬዎቿ በአባቷ ጀምረው በአባቷ የሚጠናቀቁ ናቸው(ካልታገስካት ሊሰለችህቅናት ቢጤም ሊይዝህ ይችላል)።

ለእርሷ አባቷ የወንድ ልክ መሥፈሪያዊው ሌሎችን ወንዶች የምታይበት የምትለካበት ሚዛኗ ነው። ይኼን ስልህ አባቷ ያቀበጣት እንዳይመስልህ ለሥርዓት መገዛትን፣ ለስብዕናዋ ክብር መስጠትን፣ ጥፋቷን ማመንንና እርምት መውሰድን እንጂ።

**ልብ አድርግ! የምትተዋወቃት ልጅ አባቷ ሊሞትባት፣ አልያም በአንድም ኾነ በሌላ ምክንያት እናቷ ብቻ ልታሳድጋት ትችላለች። ይኽ ግን ላንተ ምርጫ ማቅለያ እንጂ ስሜታዊ ኾነህ “ስታሳዝን ተበድላለች እኮን” እያልክ በፍቅር ስም ለመነፋረቅ ለራስህ እድል መስጠት የለበትም።

በሥርዓት መክሮ፣ ቀጥቶ ያሳደገ አባት ከሌለ የመልካምና ጤናማ ወንድ ተምሳሌት የኾናት የለም ማለት ነው። ትላንትና በሕይወቷ ውስጥ ስለወንድ መልካም ስብዕና ስለመሪነቱም በልቧ የዘራባት የለም፤ ያልተዘራባትን ደግሞ… በዚህ ላይም ራሷን ለመለወጥ ፈቃደኛ ካልኾች በእንቅርት ላይ ጆሮደግፍ…ስለዚህ …..

ያንተ ሥራ አስተዳደጓን መርምረህ ኹነኛ ሚስት መርጠህ ትዳር መመሥረትን እንጂ በአባት እጦት ወይም በሥርዓት ሳታድግ የቀረችን (ጭምት፣ መንፈሳዊ፣ ጨዋ)መሳይ ሴትና መሰሎቿን መርጃ ማዕከል ማቋቋም አይደለም።
ትዳር እንደጫማ ክር በደረስክበት የምታስረው የምትፈታው ሳይኾን አንድ ገዜ ገብተህበት ወደ አንድነት የምትመጣበት እንጂ።

ስለዚህም መክረህበት ወስን።

ሳታውቅ የገባህበት ደግሞ በትዳርህ ውስጥ አመጸኝነትን፣ እምቢተኝነትን ከሚስትህ ዘወትር ሲገጥምህ ምክንያቱ ይኽ እንደኾነ መርምር ከኾነም አውቀኸው ኑር።

****በተለይ የሴት ልጆች አባት የኾናችሁ የዘመኑን እብደት ትታችሁ በመጀመሪያ እናንተ የጥሩ ሥነምግባር አርኣያ ኹኑ። በሴት ልጆቻችሁ ዘንድ የመጀመሪያው ፍቅራቸው መኾናችሁን አስተውላችሁ ሥርዓትና መታዘዝን ለልጆቻችሁ አስተምሩ። በምንም ዐይነት መልኩ እነርሱን ከመምከርም ኾነ ከመቅጣት ችላ አትበሉ።
….ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *