አባወራ ለቤቱ….. (የቀጠለ)

እንደዛሬ ሴታቆርቋዦቹ(Feminist) አባባል ሴት ልጅ በተለይ ደግሞ “ከተማረች” ራሷን ችላ ትመራለች ሕግ ታወጣለች እንጂ ለባሏ ሕግ መገዛት የለባትም። ይኽ ያወጣውን ሕግማ አስከብራለሁ ብሎ ግሳጼ፣ ቁጣና ቅጣት የማይታሰቡ ናቸው።

ስለዚህም ተሰብሰቢ፣ ለልጆችሽ የስነስርዓትና የስነምግባር አርአያ ኹኚ ማለት እርሷ በፈቃዷ የምታደርገው እንጂ እርሱ ግድ ቢል ትዳሩ ይፈታል፣ አትሰማውም። ይኽ ለእርሷም ኾነ እርሷን ለመረዟት የመብት ረገጣ፣ ነጻነትም ገፈፋ ነው።

እንደዚህ አይነት ሴቶች ራሳቸውም ኾነ ቤተሰቡ በጋራ የሚጠቀምበትን ስርዓት ላለመቀበል በቃለ እግዚአብሄር የጸናውን፣ በወሲብ አንድ የኾኑበትንና የአብራክ ክፋይ ያገኙበትን ትዳር ሲንዱት ትንሽም ቅሬታ አይሰማቸውም። እንደውም በፈረሰው ትዳር፣ በተበተነው ቤተሰብና በሚቅበዘበዙት ልጆቻቸው ፊት “በኩራት” እና “በድል አድራጊነት” ይቆማሉ።

ወንድሜ አንተ አባወራ ነህ!

ቤትህን፣ ሚስትህንና ልጆችህን አንተ በተሞገስክበትና በተከበርክበት ስነስርዓት አኑራቸው።

በትዳርህ ውስጥ አለመግባባት ሲኖር የምትኼድባቸውን የምታማክራቸውንም ሰዎች ተጠንቅቀህ ምረጥ። ሚስትህ ስሜታዊ ናት የሰማት፣ ረጅም ሰዓት ቁጭ ብሎ ያደመጣት ኹሉ የሚታደጋት ይመስላታል።

እውነት እልሃለሁ ትዳርን፣ ቤተሰብን፣ ልጆችን አግዛለሁ ብሎ መጽሐፍ ጽፎ ወንበር ዘርግቶ የተቀመጠ ሰው ኹሉ ትዳርኽን አይታደግም። አለመታደግ ብቻም አይደለም ከድጡ ወደ ማጡ ሊነዳህም ይችላል። አንዲት እናቷ የስነስርዓት አርአያ ያልኾነቻት ሴት፣ አባቷ ስነስርአት እንድትይዝ በሚቆነጥጣት ቁንጥጫ (ለምን ተቆነጠጥኩ ብላ)ቂም የምትይዝ ሴት ለትዳር አትኾንህም እያልኩህ፤ ይኽቺን ሴት እንዴት አድርገህ ነው የትዳርህ አማካሪ የምታደርጋት?

አባወራው ቤቱን ስነስርአት እንዳያሲዝ፣ ትውልዱ መረን እንዲወጣ፣ ወንዶቻችን ጤናማ የኾነ የወንድ አስተዳደግ አድገው ብቁ እና ምስጉን ዜጋ እንዳይኾኑ፣ ፈሪና ድብቅ ግልፍተኝነት መገለጫቸውም እንዲኾን ኾን ተብሎ ተደርጓል።

አባወራው ሚስቱን በስነስርዓት እንዳይመራ፣ ሴት ልጁን ሳያበላልጥ ግን በልዩነት እንዳያሳድግ፣ እናትነትን ወዳ እና አክብራ እንዳትይዝ፣ ለእናትነት በተሰጣትም ጸጋ(ሰውነት) እንዳትሸቅጥ፣ ለባሏም ትኹት ኾና እንዳትኖር ኾን ተብሎ ተደርጓል።

ይኼን ደግሞ ኾዳቸው አምላካቸው በኾነ፣ በውጭ መንግስታት (ሕዝባቸውን ከፈጣሪ ለይተው መረን ባወጡ ከስልጣኔ ጫፍ ደርሰናል ብለው ከእንሰሳ በታች በኾነ በዘቀጠ ሞራል የሚኖሩ) እርዳታ የሚተዳደሩ ድብቅ ዐላማቸውም በፈጣሪ የተመሠረተውን ፈቃዱም የሚገለጥበትን ቤተሰብ በነጻነት ስም መናድ ነው።

እነዚህ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች የሴቷን መብት “እናስከብራለን” በሚል ሸፍጥ ነው የሚንቀሳቀሱት። የአባወራው የቤት ኃላፊነት(መሪነት)፣ ስነምግባር የተሞላ ቤተሰብ፣ ስነስርዓት ያላት ሚስትና ጤናማ የልጆች አስተዳደግ ለእነርሱ የ”አምባገኑ” የወንድ የበላይነት ውጤቶች ናቸው።

በዚህ ውስጥ ታዲያ ሴቷ ከፈጣሪ ትዕዛዝ፣ ከባሏ ፈቃድ፣ ከተፈጥሮዋም ጠባይ መውጣቷ አይመለከታቸውም። ውጤቱ ግን እንደመከሯትና እንዳሰበችውም ሳይኾን ፈጣሪ የሚያዝንበት፣ ልቧ የማያርፍበት፣ ዘሯም የማይባረክበት የዘመኗንም መጨረሻ የስቃይ ያደርገዋል።

እነዚህ ግለሰቦችና ድርጅቶች የአባወራውን ቤት በመናድ ምን ይጠቀማሉ ብትሉኝ? ራስን ለመቻል በሚል ሰበብ ከማያገቡ፣ ትዳራቸውን አፍርሰው ራሳቸውን ለማቆም የሚታትሩ ሴቶችን እናቋቁማለን እያሉ መነገድን ያተርፋሉ።

እነዚህን ግለሰቦችም ኾነ ድርጅቶች በገንዘብ፣ በአቅርቦት፣ “በትምሕርት” የሚደግፉ በፈሪሃ እግዚአብሄር የምትተዳደርን ሀገርንና ቤተሰብ የሚያፈርሱ ደግሞ የውጭ መንግስታትና ተቋማት ናቸው። በዚህም ለሴሰኛ ፍትወታቸው ማሟያ የሚኾኑ ሴቶችን በtourism ስም ያገኛሉ(ምስራቅ አውሮፓን ልብ ይሏል)።

አባወራው ቢወድቅ
አባወራው ሲወድቅ ቤቱም ሲፈርስ፣ ትዳሩም ሲፈታ ልጆች/ትውልዱ መረን ይወጣል። ወንዱ የወንድነት መገለጫውን ያጣል። ዛሬ የምናየው ስለውበቱ የሚጨነቅ፣ ሠርቶ ደክሞ ሳይኾን ባቋራጭ መበልጸግ የሚፈልግ፣ ስርዓት የለሽ ይኾናል።

ሴቷ ደግሞ ትዳር የማያሳርፋት፣ በሴትነቷ ከመጉላት ይልቅ ከወንዱ ጋር መበላለጥን የምታስቀድም ትኾናለች። ፀጉሯን መቆረጥና ማቅለም፣ ንቅሳት መነቀስ፣ ቂጧን ጥላ ጡቷን አንጠልጥላ መታየትንም ጀብዱ ታደርጋለች። ለወንድ ልጅ በተለይም ለባሏ የምትሰጠው ትኅትና አይኖርም ከዚህም የተነሳ በወሲብማረፍ አትችልም።

ጀግናው ወንድሜ አንተ ግን አባወራ ነህ!

ቤትህን፣ ሚስትህንና ልጆችህን አንተ በተሞገስክበትና በተከበርክበት ስነስርዓት አኑራቸው፣ ጠብቃቸው ከስርዓትህ ሲወጡም መክረህና ቀጥተህ መልሳቸው። ዐለም ትዳርህ ላይ፣ ሚስተህ ላይና ልጆችህ ላይ ከሰበቀችው ጦር ካነጣጠረችው ጥይት ታደጋቸው። ሴታቆርቋዦቹ(Feminist)፦ ሚስቶች ባሎቻቸውን እንዲተው፣ ልጆቻቸውን በማስወረድ እንዲገድሉ በመጨረሻም ግብረ ሰዶማዊ እንዲኾኑ ያበረታታልና በተሰጠህ አመክንዮ ልትጠብቃቸው ይገባሃል።
ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *