አባወራ በስሜት አይነዳም

ሳተናው!

እኔ አባወራ ብዬ የምገልጸውን ወንድ ከሴቶችም ኾነ ከሌሎች ወንዶች የሚለየው አንድን ድርጊት ቀድሞ በተሰማው ስሜት ተነድቶ አለመፈጸሙ ነው። ማናችንም ብንኾን ሰው ነንና በአንድ ክስተት ላይ አንድም ኾነ ብዙ ዓይነት ስሜት ሊሰማን ይችላል። ይኼም ደግሞ ተፈጥሮኣዊና ጤናማ ነው።

ይኹን እንጂ የተሰማን ስሜት ገንፍሎ ወደ ተግባር እና ንግግር ከመለወጡ በፊት መቆጣጠር፤ ቀጥሎም ጉዳዩን አጢኖ አመክንዮን፣ የሕይወት ልምድን፣ እውቀትን ተጠቅሞ ተገቢውን ውሳኔ በንግግርም ኾነ በድርጊት መግለጽ የአባወራ ብቃት ነው።

ይኽንን ማድረግ የሚችለው ወንድ ራሱን(ስሜቱን) ገዝቶ ሲያበቃ አካባቢውንም ኾነ ሌሎችን መቆጣጠር ይችላል።

ዛሬ ዛሬ ስሜትን እንደአመጣጡ በአደባባይ መግለጽ “ግልጽነት እና ራስንም የመግለጽ ነፃነት” እየተባለ ወንዱ ስሜቱን መግዛትና መቆጣጠር የማይችል ኾደ ባሻ እና ግንፍል ኾኗል። እንደዚኽ ዓይነት ስሜታዊ እና ቆዳ ስስ ወንድ ደግሞ ለሚስቱ እረፍት፣ ማዕበል ለኾኑት ስሜቶቿም ወደብ መኾን አይችልም።

ከዚኽም የተነሳ በትንሹ ጥቂት አባላት ያሉትን ተቋም፦ ትዳርን  በሰፊው ደግሞ ሕዝብን ማስተዳደር ሀገርንም መምራት አይችልም።እንደዚኽ ዓይነት ወንዶች ባለፈው እንደገለጽኩት የእማወራዋ ውጤት ናቸው።

ሴቷም ብትኾን ተፈጥሮኣዊው ሴትነቷ የሚፈቅደው ልቧም ያለምንም ማመንታት የሚማረከው ስሜቱን መቆጣጠር ራሱን፣ አካባቢውንና ሌሎችን በተረጋጋ ኹኔታ መምራት ለሚችል እንጂ እንደ እረሷ እንባ ባየ ቁጥር ኾዱ እየባባ፣ በሚያስደስተው እየፈነጠዘ፣ በዶሮ ጩኸት እየደነበረ፣ በሚያናድደውም ለሚገነፍል ወንድ አይደለም።

=========================================

ሳተናው!
ይኹንና አንተ ከስሜታዊነትህ የተነሳ ለተፈጠሩት ክስተቶች በረጋ እና በሰከነ ልብ ውሳኔ መስጠት የማትችል፣ እርምጃም መውሰድ የሚሳንህ ከኾነ ላንተ ያላት አክብሮት እየቀነሰ ባንተ ላይ ያላት አመኔታም እየወረደ ይመጣል።

ከዚኽም የተነሳ በጥንቃቄ ሊያዙ እና ሊፈጸሙ የሚገባቸውን ገጠመኞቿን ካንተ ይልቅ በተሻለ ዳር ለሚያደርስላት ወንድ(ዱርዬም ቢኾን) አሳልፋ ትሰጣቸዋለች። ኋላ ላይ አንተ ስታውቀውና “ለምን አልነገርሽኝም?” ስትላት እንኳ “እንዳላስቸግርህ ብዬ”፣ “እንዳላጨናንቅህ ብዬ እኮ ነው” ትልሃለች። ቁምነገሩ ግን “አንተ ከእኔ የማትሻል ቆዳ ስስ (ስሜታዊ) ኾነህ ሳለ ታላቅሰኝ ዘንድ፣ ወይስ አብረኸኝ ትገነፍል ዘንድ ልንገርህ” ማለቷ ነው።

አንተ ስሜታዊ ስትኾን ሚስትህ “እንዲህ ነህ” ብላ አትነግርህም። ነገር ግን ስሜታዊ ያደርጉሃል ብላ የምታስባቸውን ውሳኔዎችና ድርጊቶቻቸውን ካንተ ታርቃቸዋለች ትደብቃቸዋለችም። ይኽ ሲኾን ታዲያ ልቧ ከልብህ እየራቀ መኾኑን አስተውል።

=========================================
ሳተናው!
ነገር ግን ያንተ ስሜትህን ገዝተህ፣ አካባቢህን ተቆጣጥረህ ተረጋግተህም የምትወስናቸውም ውሳኔዎች የማይመቿት፤ ረብሻ በበዛበት፣ አለመረጋጋት ባየለበት፣ አንዳንዴም እርሷ ራሷ ኾን ብላ በምትፈትንህ ወቅት ያንተ ጉዳዮችህን በረጋና በሰከነ መንፈስ ማስተናገድ ሰላሟን የሚነሳት ሴት ብትኖር እርሷ እማወራዋ ብቻ ናት።

ምክንያቱም እርሷ ያንተን የተፈጥሮ ዐላማ፣ በእርሱም ውስጥ ያለህን ሚና፣ ለእርሱም የተሰጠህን ጸጋ፣ ንቃና አቅልላ ትዳሯን(ቤቷን) ለመምራት ካንተ ጋር የ”ስልጣን” ሽኩቻ ትገጥማለችና ነው።

ከዚህ የተነሳ አንተ በሕይወት ወጀብ መካከል የምታሳያት መረጋጋት እርሷን ከማረጋጋት ይልቅ የበታችነት ውዥንብር ውስጥ ከቷት አንተን “ግድ የለሽ” ብላ የምትከስበት ይኾናል። በተጨማሪም የተፈጠሩት ክስተቶች ያመጡት አንዳች ዐይነት ስሜት ቢኖርም አንተ ግን በምክንያታዊነት አብላልተህ፣ በእውቀት አስተውለህ፣ ከልምድህም ጨልፈህ በወሰንከው ብትጸና “ግትር” መባልህ አይቀርም።

ሳተናው!
እንግዲህ ልብ አድርግ በስሜት ተነድቶ አለመወሰን የወንድ ልጅ ስጦታው(ጸጋው) ነው። ይኼንን የማታደንቅልህ፣ ባታደንቀው እንኳ የማታከብርልህ የማትቀበልህም ሴት ምን “እወድሃለሁ” ብትልህ ልቧ አይሸነፍልህም።

አስተውል!
የወንድ ልጅ ልኩ በተለይም የአባወራ ብቃቱ  ከራሱ(ከውስጡ)፣ ከአካባቢውም፣ ተጽዕኖዎች እነርሱም ከሚያሳድሩበት ስሜት በላይ ሰፍፎ መሰየም መጽናትም መቻሉ ነው።

ይኼም ውሳኔዎችህን፣ ንግግሮችህን እና ድርጊቶችህን አንተ እንጂ ስሜትህ የማይዘውራቸው፣ የማይነዳቸውና የማይወስናቸው ያደርግልሃል።

…….

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *