አባወራ ከቤቱ ባሻገር (ሀገርን ትውልድን ይሠራል)

ሀገርህን እንዴት ተረከብክ?
ወንድሜ አባቶችህ ሀገርህን በምን ዓይነት ፈተና ውስጥ አልፈው እንዳቆዩልህ ስታውቅ አንተም ለልጆችህ ለምታቆይላቸው ሀገር መክፈል ያለብህን ዋጋ ትረዳለህ።

“ሀገሬ ለእኔ ምን አደረገችልኝ?” የምትለኝ ወዳጄ ይኽች “ምን አደረገችልኝ” የምትለኝ ሀገርህን መጀመሪያ እስቲ እወቃት። የሀገርህን መልክዓ ምድር፣ ያሏትን ተፈጥሮኣዊ ጸጋዎች(የማዕድናት፣ የአዝርዕት፣ የእንሰሳት፣ የውሃና ሌሎችም ክምችትም ኾነ ስብጥር እወቅ። ቀጥለህም አባቶችህ ራሳቸውንም ኾነ ትውልዳቸው እንዴት እንደጠቀሙበት ተገንዘብ።

ሲቀጥልም ሰው ከእናቱ ኾድ ሲወጣ ምንም ይዞ እንዳልመጣ ሲሞትም ኹሉን ትቶ ባዶውን እንዲኼድ አባቶችህ ላንተ ትተውልህ የኼዱትን እወቅ። ከዚህ በኋላ ሀገርህ ላንተ ያደረገችልህን አንተ ልታደርግላት ከሚገባህ ጋር ማወዳደር ትችላለህ።

አንተ በአባወራነት ሚናህ “ዶሮ ብታልም ጥሬዋን” እንዲሉ ኾድህን ብቻ ለመሙላት አትሩጥ። ኾዳቸውን በመቀነት አስረው ባጭርም ታጥቀው የአፍሪካን ኾድ መቀለብ የምትችል ሀገር እንዳቆዩልህ አስብ።
ቤተሰብህን/ሀገርህን ከጠላት መታደግ
ወዳጄ ሀገርህን ከጠላት መታደግ በዋነኛነት ለመከላከያ ሠራዊት የተሰጠ ነው። መከላከያ ሠራዊት የሚኾኑት ያንተ ልጆች እርሱም ሲያንስና ጠላት ሲበረታ አንተ ማስፈለግህ አይቀርም(መቼም አንተ እያለህ ሚስትህን፣ እናትህን፣ ሴት ልጅህን አትልክም)።

ጠላቴ ድንበር ላይ ነው ብለህ ጦርነቱ ደጅህ እስኪመጣ መጠበቅ ራስህን የማያተርፍ ራስ ወዳድነት ነው። ከዚህ ራስ ወዳድነት ወጥተህ ድንበር ላይ ስለሚዋደቁት አባወራዎች ግድ እንዲልህ ስለ ሀገር ስለወገን መሞት ምን ማለት እንደኾነም ትረዳ ዘንድ ሀገርህን ማወቅ አለብህ።

ድህነትን አሸንፈህ ሀገርህን ለመገንባት
ወንድ(ሰው) ኾነህ በተፈጠርክበት ማንነት ውስጥ ትልቁ ትዕዛዝ “ጥረህ ፣ ግረህ” እንድትበላ ነው። ከጥገኝነት፣ ከሌብነት፣ ከሙስና በራቀ ሕይወት ራስህን መቻል ትልቅ ቁምነገር ነው።
ሲቀጥል ደግሞ ቤተሰብህ ካንተ የሚፈልገውን ወጥተህ ወርደህ በላብህ ባገኘኸው መጠን በሕግና በአግባብ ማኖር ነው።

በዚህም መሠረት ከኹሉ አስቀድመህ ስንፍናንና ሥርዓት የለሽነትን አስወግደህ መጀመሪያ አንተ ራስህ ሰው ኹን። ሲቀጥል ግን በዚህ ጥረትህና አርአያነትህ የምትገነባው ቤተሰብ ለሀገርህ የምትሰጣት ትልቁ ስጦታህ ይኾናል።

ምን ቢማሩ ከደሃ አፍ የሚቀሙ፣ ፍርድን በሙስና የሚያጣምሙ፣ ፍትህን ማስፈን የማይፈልጉ ልጆችን ወደ ሕብረተሰቡ ስትጨምር ለትውልድ ሸክም ለሀገርም በደል እንደሚኾኑ አስተውል።

ስለዚህም “ዶሮ ብታልም…” እንዲሉ በራስወዳድነት ተጠርንፈህ ኾድህን ብቻ ስለመሙላት አታስብ። የምትበላውን አግኝተህ የምትበላበት ጊዜና ጤናም ታጣለህና። ይልቁንስ ከጠባቧ “ለእኔ ብቻ” አስተሳሰብ ተላቀህ በሰፊው አርቀህም አስብ።

ከቤታችን፣ ከቤተሰባችን ውጪ ማሰብ ሞኝነት አንዳንዴም ስህተት በሚባልበት ዘመን አንተ ግን አንዳንዴ ከቤትህ ወጣ በል የሀገርህን ዙሪያ ገባውን ጎብኝ። አንተ ጋር የተትረፈረፈ ሌላው ጋር ጠፍቶ፣ ሌላውን ያጣበበ አንተ ጋር አጥሮ ታገኘዋለህ።

ወጣ ስትል ከቤትህና ከቤተሰብህ በተጨማሪ እግዚአብሄር የሠራው፣ በጸጋ ያደለው ሰፊ ዐለም እንዳለ ታያለህ። ከተሰጡህ ስጦታዎች( እውቀት፣ ጊዜ፣ ገንዘብ፣ ጤና፣ ምግብ፣ …) ሲተርፍህ አታባክን ከሚያስፈልጋቸው ጋር በመደጋገፍና በመገበያየት ወገንህን ሀገርህን ገንባ እንጂ።

የርዕይን ጥቅም ትረዳለህ
ወንድሜ ይህች ሀገር ለእኔ እና አንተ የቆየችው ራሳቸው ከሚኖሩበት ዘመን ብዙ ሺህ ዘመናትን ወደፊት የተሻገረ ርዕይ በነበራቸው አባቶቻችን ነው። እነዚህ ድንቅ አባቶች ለዚህ ርዕያቸው በወቅቱ የተጋረጠባቸውን ፈተና ተቋቁመው፣ ሳይሸሹም ያገባናል ይመለከተናል ሲሉ ኃላፊነትን ወስደው ትኩረታቸውን፣ ጥረታቸውንና ያላቸውን ኹሉ(ሕይወታቸውን ጭምር) ገብረዋል።

ጠቢቡ “ርዕይ የሌለው ትውልድ መረን ይኾናል” ብሏልና የእኔና ያንተም አባቶች ትልቅ ርዕይ ነበራቸው፦ ትውልዳቸውን ሀገራቸውን ትልቅ የማድረግ ያንንም አሳክተው አልፈዋል። እኔ እና አንተስ? ሀገራችንን ስናውቅ የርዕይን ጥቅም ከእነርሱ እንማራለን በዚህም ከራሳችን፣ ከቤተሰባችን ሀልፈን ሀገራዊ ፋይዳ ያለው ሀገራዊ ርዕይ ይኖረናል።

ጥቆማ እኔ ቀምሼ ያጣጣምኩትን እነኾ፦
ወንድሜ ንሳ! ርዕይህን አውቀህ ከራስህ አልፈህ ወገንህን ሀገርህን ጥቀም። በዚህ በኩል እንዲያግዝህ ትፈልግ ከኾነ #DawitDreams ( #Dreamssuccesscoach) እንድትጎበኝ እጠቁምሃለሁ።

ሀገርህንስ በቡድን የፈለግከውን ቦታ አልያም ቀድሞ በተዘጋጀ መርሃ ግብር መጎብኘት ትሻለህን? እንግዲያውስ #አልፋአልፋ አልያም #zelalemberhanu ብለህ ቀጠሮ አስይዝ። ይኽች ድንቅ ሀገራቸውን ገልጸው በማይጠግቡ ለማሳወቅም በቆረጡ አስጎብኚዎች በምናብ ዘመናትን ወደኋላ ሄደህ ራስህን ታገኘዋለህ። በዚህም ከግለኝነት ተላቀህ ራስህን በሀገራዊ ሚና አባወራነትህንም በኃላፊነት ከፍታ ታንጻለህ …. ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *