አባወራ ግብረገብ ነው

እንደዓለም መለኪያ በዓለማዊ እውቀት መካን (ሰርተፊኬት፣ዲፕሎማ፣ ዲግሪ፣ ማስተርስ፣ ፒ.ኤች.ዲ)መያዝህ የዚህን ዓለም ኑሮ ውጣውረድ፣ድካሙን፣ ታቀልበት እንደሆነ እንጂ ለአባወራነትህ በራሱ ብቁ አያደርግህም። አንተ ግን አባወራ ለመሆን ተፈጥሮህን መርምር፣ እወቅው፣ኑረውም። እንደወንድ በወንድነት ድንበር ታጥረህ እና ተወስነህ ተፈጥረህ ወንድነትህን አፍርሰህ ወይም ክደህ ግራ የተጋባ ማንነት አትያዝ። አልያ ግን ጉዳቱ ባንተ የሚያበቃ ሳይሆን የምታፈራው የነገው ትውልድ አንተ የወንድነትን አመራር፣ አስተዳደር፣ኃላፊነት ሚና ወኔ ስትሸሸ እርሱ ካንተ ብሶ የወንድነት ጾታውን የሚጠየፍ ወይንም የሚጠራጠር እንደሴት ሚስት መሆንን የሚሻ (ግብረሰዶማዊ) ትውልድ ታፈራለህ ወይንም እንደዚህ አይነት ትውልድ እንዲፈጠር መሠረት ትጥላለህ። ታዲያ ከተወቃሽነት እንደማታመልጥ አትርሳ።

ይህን ከላይ ያተትነውን ሌላ ጊዜ በሰፊው እናየዋለን ወደዛሬው ርዕስ ስንመጣ ግን የአባወራን ግብረገብነት እናገኛለን።
አባወራ መሪ ነው ብለናል በመሪነቱ ደግሞ የቤቱን ብቻ ሳይሆን የሀገሩን እና የኃይማኖቱን(የአምላኩን) ህግ እና ሥርዓት ሚስቱ፣ ልጆቹ በአጠቃላይ ቤቱ እንዲያውቅ አውቆ ያሳውቃል፣ እንዲጠብቁ ጠብቆ ያስጠብቃል እንዲኖሩት ኖሮ ያሳያቸዋል። አንተ ያልኖርከውን፣ ያላሳየኸውን እና በህይወትህ ያልተለማመድከውን ሥነምግባር ከሚስትህም ሆነ ከልጆችህ መጠበቅ ያልዘሩትን ለመሠብሰብ ከመሻት አይተናነስም። ስለዚህም ለቤትህ አርአያ ሁን። አርአያ ሲባል ደግሞ ሚናህን የሚሠርዝ የሚደልዝ መሆን የለበትም።
አስረጅ፦ በሥነሥርዓት፣ በሥነመግባር፣ የሰውን ዘር ሁሉ በሰውነቱ(በተፈጥሮው)፣ በአመለካከቱ፣ ማክበር …..እና ሌሎችም ናቸው።

በተለይ ደግሞ ወሳኝነትን፣ ቃል ጠባቂነትን(ቃልህን እንኳን ሌላ ሰው አንተም ልታፈርሰው እንዳይገባ)፣ ፍላጎትን መወሰንን፣ፈሪሃ እግዚአብሔርን፣የሀገር፣የወገን፣የባንዲራ ፍቅርን፣ደፋርነትን(አለመፍራትን፣ጀግንነትን)፣ ስኬትን፣ወንዳወንድ ተክለሰውነትን(በሥራም ሆነ በስፖርት የዳበረ)፣ብርታትን…እና ሌሎች ጠባያትን አክለህ ለወንዱ ልጅህ አርአያ ሁነው።

በዚህም ላይ ለሴት ልጆችህ አሳቢ፣ ለጋስ(ፍቅርን፣ ጊዜን፣ ስጦታን)፣ መከታ ከለላ (ከዱርዬ፣ ከቀማኛ)፣ አመስጋኝ አድናቂ፣ ተጫዋች አዝናኝ….እና ሌሎችንም በመሆን ነገ ልታገባው ለምታስበው ወንድ መልካም ስዕል ሳልላት። ነገ አብራው የምትኖረውን ወንድ የምታየው ባንተ ውስጥ ነውና።ስለዚህ ስለራስህ ብቻ ሳይሆን ስለ ትውልድ፣ ስለ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ስለነገ በማሰብ ተመላለስ።

አባወራ ክብር፣ድንበር አለው፤ይህንኑ ክብሩን፣ ድንበሩን ያስጠብቃል ወይም ሰዎች ክብሩን እንዲጠብቁ ድንበሩን እንዳያልፉ ያስጠነቅቃል። በዚህም አንጻር እርሱም የሌሎችን ክብር እና ድንበር ይጠብቃል። በተለይም የሚስቱን የሴትነት፣ የሚስትነት፣ የአጋርነት ከምንም በላይ ደግሞ የሰውነት ክብሯን ይጠብቃል። በምንም አይነት መልኩ ሴትን ልጅ (ሚስቱን) ከሰውነት ክብር አውርዶ በገንዘብ የምትገዛ ሸቀጥ፣ ዝናን ተከትላ የምትመጣ ሰነፍ፣ ሹመት የምትከተል ተቀጥላ አድርጎ አያስብም። እውነት እላችኋለሁእንዲህ የሚያስቡ ወንዶች ወንድነታቸው ራሱ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ነው። የጠቀስነውን የሚያደርጉ ሴቶች የሉም አይደለም ግን አብዛኞቹ እንዲህ አይደሉም። በርግጥ ሴቶች ወንድነትን አባወራነትን ውስጡ ያጡበትን ወንድ ይነዘንዙታል፣ ትዕግስታቸው ሲሟጠጥም ይፈቱታል ምክንያታቸውን የማይረዳው ምስኪኑ ወንድ ታዲያ ለገንዘብ፣ለዝና፣ ለቅንጦት ብላ ፈታቺኝ ብሎ ያስባል አስቦም አይቀር ያወራል። እውነቱ ግን ከዚህ የራቀ ሆኖ ሳለ። አንተ ታዲያ ሚስትህን ካለስሟ ስም በመስጠት በስነምግባር ጉድለት እንዳትገኝ ተፈጥሮህን አውቀህ ለአርአያነት ስትል ግራገብ ሳይሆን ግብረገብ ሁን።

ልጄ(ወንድሜ) ምን ብወድህ መራር ነው ብዬ እውነቱን ከመጋት እንደማልቦዝን እወቅ ፤ትተኸኝ መሄድ ምርጫህ ቢሆንም እውነቱን መጋት መንገድህን ማሳየት ግን የእኔ ግዴታ ነው ። ……ይቆየን..

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *