አባወራ

አባወራ የቤቱ ጌታ፣ የቤቱ መሪ ፣የቤቱ አስተዳዳሪ ፣የቤቱ ኃላፊ፣ ……ነው። ወንድሜ ቤቴን 50/50 በሆነ ሥልጣን እመራለሁየፍቅር ህይወቴን 50/50 በሆነ መዋደድ አዘልቃለሁ ብትል ልትኖርበት ከተጻፈልህ መመሪያ(manual) ከጸሓፊውም ፈቃድ ውጪ ነህና የኑሮ ድካምህም እረፍት የማይሰጥህ፣ሥራህ የማያስመሰግንህ፣ ብዙ ስትጥር ገና ብዙ የሚጠበቅብህ፣ ሩጫህ ጎዶሎን የሚሞላ ሳይሆን ራሱ ጎዶሎ ይሆንብሃል።

አንተ ከፈጣሪ በታች ከፍጥረትም ሁሉ በላይ ታላቅ ነህ።ታላቅነትህን እወቅ፣ እመን፣ተቀበል፣ ኑረውም።ልብምአድርግ የተጠራኸው እና የተመረጥከውም ለታላቅ ዓላማ ነው። ይህ 50/50 ኑሮ ዐለም አውቅልሃለው ብላ በሥልጣኔ ስም የምትጭንብህ፣ በዕውቀት ሰበብ የምታስታጥቅህ፣በዘመናዊነት መለዮ የምትከትብህ ተራ እና ተርታ ኃሳብ ነው።አውቃለሁ የምነግርህን ነገር ለመቀበል ይቸግርሃል አዎ ላንተ፣ለዚህ ትውልድ ይቸግራል፤ግን ቆም ብለህ ስለራስህ ተፈጥሮም ሆነ ስለሴቷ ተፈጥሮ አጢን። ” ገብቶኛል” ብለህ የምትሞግተኝ “መሪ ነህ፣ አለቃ ነህ፣ አዛዥ ነህ” ስልህ እርሱ ድሮ ቀረ የምትለኝ ወንድሜ ፦ይህ ዓለም አንተንም ሆነ ዘርህን ለማጥፋት የጠነሰሰችው ርካሽ እና መደዴ አመለካከት ነው እልሃለሁ።

ዐለም የዛሬ 60እና 70 ዓመት ገደማ እንደ አብዮት ያፈነዳችው ይህ ድውይ አመለካከት ዛሬ ፍሬው ደርሶ እየቃምነው እንገኛለን። ምዕራብያኑ የከሰሩበትን ጽንሰ ኃሳብ እያየህ እና እየሰማህ የምትከተላቸው ከሆነ ያንተ መማር ያንተ ፒኤችዲ ምን ጠቀመህ? ሰው ሰብዓዊ ተፈጥሮውን ፣በልቦናው ውስጥ የተጻፈውን ተከብሮበትና ተጠቅሞበት የነበረውን የህይወቱን መመሪያ ዓለም ጨቋኝ እና አዋራጅ ነው ብላው አሽቀንጥሮ ጣለ። በቦታውም ራሱን እንደ ግለሰብ ያዋረደ ፣ ትዳሩን የንዝንዝ፣ የፉክክር፣ ሲከፋም ለፍቺ የተመቸ ያደረገውን ከንቱ ዕውቀት ተቀበለ። ኑሮውን 50/50 ለማድረግ ሲሰፍር ሲቀንስ ሲቀጥል ሲያሳጥር በልዩነቱ ይገኝ የነበረው የፍቅር ጥፍጥና (intimacy) ጠፋ።በዚህም ብዙ ትዳሮች ፈረሱ ልጆችም ተበተኑ። ዛሬ ዛሬ የእናት አባት ፍቅር የማያውቁ አዛውንትን የናቁ ሰውን የማያፍሩ ፈጣሪን የማይፈሩ ጨርሰው ስድ የሆኑ ልጆች ለማየት ችለናል።

ይህም የዛሬው ሰው አንድም ተፈጥሮውን መርምሮ ፣በልቦናው የተጻፈውን አስተውሎ ፣በመጽሐፍ ያለውንም ጠንቅቆ ከመረዳት ይልቅ የሰውን ዘር በባርነት ቀንበር ከተው የአመለካከት ደሃ አድርገው መግዛት የሚፈልጉትን በዓለማዊው ሥልጣንም ሆነ ብዕል (ሀብት) የበላይ የሆኑትን ንግግር አምኖ እና ተቀብሎ የባርነት ኑሮ የመኖሩ ውጤት ነው። ሲቀጥልም እነዚህ ‘ልሂቃን’ በእነርሱ የኑሮ መመሪያ ስለሄደ የሰጡትን የትምህርት ምስክር ወረቀት(ዲፕሎማ፣ዲግሪ፣ማስተርስ፣PHD…) እንደትልቅ እና የመጨረሻ የህይወቱ ስኬት ቆጥሮት ስለራሱም ሆነ ስለአካባቢው ተጨማሪ እውቀት የማይፈልግ በትምህርት ደረጃውና ዓይነት ልክ ብቻ የሚያስብ በእዛም ልክ የተሰፈረለትን እየተቀበለ የመኖሩ ውጤት ነው።

አንተ ግን ራስህን፣ ተፈጥሮህን መርምር መጻህፍትንና የቀደሙትን አባቶችህን ጠይቅ። ዓለም ትኖርበት ዘንድ፣ ትወዳደርበት ዘንድ፣ ደመወዝ ታገኝበት ዘንድ የሰጠችህ የትምህርት ምስክር ወረቀት አንተን ዘወትር ስለተፈጥሮህ ከመማር እና ከመመራመር እውነቱንም ከማግኘት ሊያግድህ አይገባም። ፈጣሪ የተሰጠህን ሚና እወቅ አክብረውም። እርሱ ባወቀ የሠራውን ተረዳሁኝ ብለህ አታርም ይልቅስ አለማወቅህን አውቀህ ወደ አዋቂው እውቀት ተዘርጋ።አንተ ያልተቀበልከውን ወይም የናቅከውን አባወራነት ሚስትህ እንድታከብረው አትጠብቅ። አንተ አዛዥነትህን ፊት ስትነሳው ሚስትህ ለታዛዥነት ልቧ ድፍን ይሆናል። ሚስትህስ ያላሳየችውን መታዘዝ ልጆችህ ከየት ያመጡታል። አንተ ዛሬ ላይ ይህ የፍቅር ውጤት ነው ትለኝ ይሆናል እኔ ግን እልሃለሁ ይህ ያለማስተዋል ውጤት ነው።

ልብ በል የአባወራ ሚናህን በአግባቡ ስትኖር ላጤ ብትሆን ሴቶች የሚመርጡህ ብታገባ ሚስትህ የምትኮራብህና የምታከብርህ፣ የምትታዘዝህ ትሆናለች። ሁልጊዜም እንደምነግርህ ይህችን ሴት በወሲባዊ ጨዋታ ማስደሰትም ቀላል ይሆንልሃል አልያ ግን …….

ከአንገትህ ቀና ደረትክን ነፋ አድርገህ በሙሉ መተማመን ተመላለስ ምክንያቱም አንተ አባወራ ነህ!!!!!

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *