አንተ ቤቱን ቅጥ የሚያሲዝ እውነት ነው

እስከዛሬ እያየን በመጣነው ያንተ አባወራነት ስልጣን ላይ ከሞላ ጎደል እየተስማማን የመጣን ይመስለኛል። በእርግጥ ያነሳናቸው ነጥቦች እውነት ቢኾኑም ለዚህኛው ትውልድ እንኳንስ ለሴቱ ለወንዱም መራር ናቸው። ምክንያቱ ደግሞ “ከስልጣኔ” ጋር ያስገባነው የጾታ “እኩልነት” እውነትን ያስተምራሉ በሚባሉት የእምነት ተቋማት ውስጥ ሳይቀር ገብቶ ወንድ ልጅ በቤቱ ያለው የአባወራነት ሚና ያረጀ ያፈጀ አመለካከት ተደርጎ ተቆጥሯልና ነው። መረረም ጣፈጠም ግን እውነት ነውና ጨክነህ ጨልጠው፦አንተ አባወራ ነህ።
ኹልጊዜም የምላት እና የምወዳት ኃይለቃል አለች እርሷም፦ እውነት አርነት ታወጣችኋለች።
ይኽችን ቃል ማን ይኾን ለመጀመሪያ ጊዜ የተናገራት? እውነትስ ማን ነው? እውነትን የሚናገራት፣ የሚያደርጋት፣ የሚኖራት፦ የሚሰብካት(የሚያስተምራት) ደፋር ፣ጀግና፣ አጨብጫቢ(ቲፎዞ) የማይፈልግ፣ ራሷ እውነት ስለራሷ ከምትመሰክረው ውጪ ምስክር ፍለጋ የማይባክን፣የሕሊና ወቀሳ የራቀለት፣ በአጭሩ ሰው ኾኖ ተፈጥሮ ሰው የኾነበትን ዓላማ እና ሚና የገባው ነው።
የተሰጠውን የአባወራነት ሚና ለዘመኑ አይመጥንም ብሎ ከተፈጥሮአዊው እውነት ያፈነገጠ ወንድ በበዛበት በዚህ ዘመን። ሴቶቻችን በግልጥ አይንገሩን(ደግሞም አይነግሩንም) እንጂ ከእኛ ከባሎቻቸው ያጡት እንዲህ አይነቱን ቤቱን ትዳሩን ቅጥ የሚያሲዝ ወንድ ነው። ገንዘብ፣የዓለም ስልጣን፣ዝና፣ ለኑሮአችን ብለን የተማርነውና ደመወዝ የምንቀበልበትም እውቀትም ኾነ የእውቀቱ ደረጃ ቤታችንን ቅጥ አያሲዙትም።እኛ የዛሬ ወንዶች ለቤታችን፣ ለትዳራችን፣ ለልጆቻችን ገንዘብ ማምጣት ወይም የሚያስፈልጋቸውን ወጪ መሸፈንን በሚናችን ውስጥ ትልቁን ቦታ ሰጥተነው እንንደፋደፋለን።ትልቁ የእኛ የወንዶችም የምንጊዜም ስህተት ሴቶችን
1ኛ በገንዘብ
2ኛ በዝና
3ኛ በውለታ
4ኛ በስጦታ
5ኛ በምስኪንነት ልባቸውን ለመግዛት መሞከሩ ነው። ይኽ ደረቅ እውነት ነው።
እነዚህን ነገሮች ለጊዜው ሴቶች ይወዷቸዋል ብንባልም፤ ተፈጥሮአዊ ውበት ካለው ቤቱን ቅጥ ማስያዝ ከሚያስችለው የወንዱ አባወራዊ ሚና አንጻር ሲታይ ለሴቶች ስህበት የሌላቸው፣ የነጡና የገረጡ ናቸው። ወንዶችም ይኽንን ተፈጥሮአዊ እና ውጤታማ የኾነውን የአባወራ ስልጣን ቢረዱት ሴቶችን ለማትረፍ(ለማግኘት፣ላለማጣት) ገንዘባቸውን በከንቱ ባልበተኑት፣ ስለመልካቸውና አለባበሳቸው፣ ስለትምህርትም ሆነ ስልጣን ደረጃቸው ባልተጨነቁ፣ ምስኪንም ባልኾኑ ነበር።
አንተ አባወራዊ ስልጣንህን አግባብነት ባለውና በሙሉ ኃላፊነት ስትለማመደው ብቻ የምትወዳትን ሴት ያንተ ታደርጋታለህ። ይኼን ጊዜ ብቻ ድርጊቶችህ የሚያስደስቷት፣ ፊትህ የሚናፍቃት፣ እንኳን ሳቅህ ቀርቶ ቁጣህ ሲቆጠብ የሚከፋት፣ ለቤትህም ንግስት ለራስህም አክሊል ገበናህንም ሸፋኝ ትኾናለች።
ካለበለዚያ ግን ልጆቻችሁን ስለተንከባከብክ፣ እናቷን ስላስታመምክ፣ አባቷን ስለደገፍኽ፣ ወንድሞቿን ስላስተማርክ፣ ዘመዶቿን ስለወደድህ፣ ለእርሷም ከምትለብሰው ከምታጌጠው ስላላጓደልክ፣ በቤትህ ላለው ሁሉ ከፍላጎቱ እንዳይጓደል እና ሌሎችንም ስላደረግህ ብትወድህም እንኳ መውደዷ ባለዕዳ ከመኾኗ አንጻር ብቻ ነው እንጂ ወንድነትህ ማርኳት አይደለም ወይም አይኾንም። አንተም በዚኽ መልኩ በጭራሽ፣ በጭራሽ ደግሜ እልሃለሁ በጭራሽ የምትወዳትን ሴት ልብ ለመግዛት አትሞክር አትችልምና(ልብ አድርግ ግን! እንዲህ የዋልክላት ሴት አግብታህ ልትወልድልህ ትችላለች)። መልካም ነገሮችን አታድርግላት አላልኩህም ልቧን ይገዛልኛል የእኔ ትኾናለች ብለህ አስበህ አታድርጋቸው አልኩህ እንጂ።ይኽንን የከፈልክላትን ዋጋ እስከ እለተሞት ያንተ ነኝ ብላ ራሷን ብቸኛ የዕዳዋ መክፈያ አድርጋ ባልተማረከችበት ሕይወት የግድ ልትኖር ትችላለች። ለምን አልተማረከችም? ተፈጥሮአዊ ለኾነው ትኅትናዋ ልከኛ የኾነ ልዕልና፣ በተለያዩ የስሜት ማዕበል ለሚናጠው ውስጧ እርፍ የሚያደርጋት ጽኑ ወደብ፣ ከፍተኛ የኾነውን ወሲባዊ ስሜቷን(ካንተ እንደሚበልጥ ታውቃለህ?) ጥግ የሚያደርስ ወንድ፣ ውሳኔ፣ ገደብ እና ልክ ላጣችላቸው ምርጫዎቿ አደላዳይ እና ቆራጥ አባወራ ስላጣች ብቻ ነው። ብዙ ወንዶች ለቤታቸው፣ ለትዳራቸው ብዙ ይኾናሉ ነገር ግን አመድ አፋሽ ናቸው። ተወቃሾቹም እራሳቸው ናቸው። ምክንያቱም ተፈጥሮአዊ ሚናቸውን፣ መለኮታዊ የኾነ ግዴታቸውን ወደ ጎን ትተው በዓለም ፖለቲካዊ የጾታ ልከኝነት ተወስደዋልና ነው። አንተ ግን አባወራ ነህ መወደድህም በዚህ ተፈጥሮአዊ በኾነ ልትኮተኩተው፣ ልትንከባከበው እንጂ ልትገዛው በማትችለው መለኮታዊ እውነት ይኹን። በይሉኝታ እና በውለታ የተተበተብክ የተፈጠርክበትን ልክ እና አቅም የተነፈግህ የስጋም ሆነ የነፍስ እስረኛ መኾን የለብህም።ማን ነበር እውነት ብቻ አርነት ታወጣችኋለች ያለው አልከኝ?…..ይቆየን።

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *