እማወራነትና መዘዙ ክፍል 1 ፦ አባወራነት ሲጠወልግ እማወራነት ያብባል

(ይኽ ጽሑፍ የራሴ ጥናት ከኾነው ረጅም ጥንቅር ከመግቢያው የተቀነጨበ ነው)

ሳተናው!

በዚህ አኹን ባለንበት ዘመን ወንዱም ኾነ ሴቷ ለተፈጥሮኣዊው ባሕሪያቸው የተስማማውን እየተዉ ግራ በተጋባ ማንነት ውስጥ መዘፈቃቸው የሚታይ ሐቅ ነው።

ከዚህም የተነሳ በሕይወታቸው  ደስታን በማጣት፣ ለጭንቀትና ስኬት አልባ ኑሮ እየተዳረጉ ለባሕሪያቸው በማይስማማ ግብርም ተጠምደው በተጎሳቆለ ስብዕና እድሜያቸውን ባጭር ያጠናቅቃሉ። (ስኬትና ጉስቁልና ከቁሳዊነት ባሻገር መንፈሳዊ ዳራውንም አስብ)

ይኹን እንጂ በተለይም በትዳር ውስጥ አንዱ የተሰጠውን ተፈጥሮኣዊ ሚና ከ”ስንፍና ከግዴለሽነት፣ ጊዜም ኾነ አቅም” ከማጣት የተነሳ ሳይወጣ ቢቀር ሌላኛው ለመወጣት ይሞክራል/ይገደዳልም።

ይኽ ሲኾን ታዲያ ዐዲሱን ሚና ለመወጣት ባልተሰጠው ጸጋ መድከሙ እና እርሱንም በመወጣቱ ጭምር በስነልቦና፣ በመንፈሳዊ ሕይወቱና በአካሉ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም። በተጨማሪም  የሚናው ተጠቃሚ በኾኑት ላይም የተዛባ የማንነት ግንዛቤ እንዲይዙ በራሳቸው ማንነት ላይም እንዲሁ እንዲኾን መሠረት መጣሉ አይቀሬ ነው።

ሳተናው! ትዳርን፣ ቤትን፣ ሚስትን፣ ልጆችን … እንዲመራ ስልጣን የተሰጠው አባወራው (ወንዱ) ለመኾኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ነገር ግን አንተ ይኽንን ኃላፊነትህን ብትተው፣ ብትዘነጋ፣ እንደሚጠበቅብህም ባትወጣ አልያም የተሰጠህን የራስነት ስልጣን ለበደልና ለጭቆና ብትጠቀምበት ፈጣሪህን ማሳዘንህ ሴቷንም ከተሠራላት ስርዓት እንድታፈነግጥ ምክንያት መኾንህን አስተውል።

የሚስትህ የትምህርት ደረጃ በተለምዶው አጠራር በዲፕሎማ፣ በዲግሪ፣ በማስትሬትም ኾነ በዶክትሬት መስፈርት መገኘቱ ምድራዊ ኑሮኣችሁን ብታቀሉበት፣ ያንተንም የቤት አስተዳደር ብታግዝበት እንጂ አባወራነትህን የሚተካ(የሚሽር) መኾን የለበትም።

የሚስትህ የኃብት መጠን በተለምዶው አባባል በበብርና በወርቅ ቢሰፈር፣ በመኪናና በቤት ብዛት ቢታጀብ፣ እርሷም በላኪነትና ባስመጪነት ብትታወቅ፣ በቤተሰብ ውርስም ዝናዋ ቢናኝ አኹንም ምድራዊ ልፋታችሁን ቢያቀልላችሁ እንጂ የአባወራነትህን ስልጣንም ኾነ ከእርሱ የሚመነጨውን ሚና ሊያሳጣህ አይገባም።

የሚስትህ የስልጣን እርከን በአስተዳደራዊው አጠራር የወረዳ ሥራ አስፈጻሚ፣ የከተማ ከንቲባ፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድር፣ ኢታማዦር ሹም፣ ጠቅላይ ሚኒስቴርና ፕሬዝዳንት ቢባል አኹንም እርሷ ከጥረቷ ብዛት የደረሰችበትን ቢያሳይ፣ ዐለማዊ ኑሮኣችሁንም ቢያሰለጥን እንጂ በቤትህ፣ በትዳርህና ባንተ ላይ ራስ አድርጎ አያስቀምጣትም።

አንተ ግን ሚስትህ በጥረቷ የደረሰችባቸውን ማዕረጎች ዐይተህ ከአባወራነትህ ገሸሽ ልትል፣ ሚናህንም ልትተው፣ ስልጣንህንም አሳልፈህ ልትሰጥ አይገባህም። ሚስትህ በየትኛውም ዓይነት የመንፈሳዊ ልቀት፣ አእምሮኣዊ ምጥቀት እና አካላዊ ብቃት ላይ ብትገኝ ፈጣሪ አንተን ለስሜቷ ወደብ፣ ለስጋቷም እረፍት፣ ለኑሮዋ መሪ፣ በለምለም ማህፀኗም ትውልድን ዘሪ ማድረጉን አትርሳ። 

እነዚኽንም ስትወጣ መለኮታዊ ትዕዛዝን እየፈጸምክ፣ ሰብዓዊ ግዴታህን እየተወጣህ፣ አባወራዊ ሚናህንም እየተጫወትክ መኾንህን አስተውል። ይኹን እንጂ  አባወራነትህን ንቀህ እርሷን በራስህ ላይ አሰልጠነህ እማወራነቱን ብታጸድቅላት፣ እርሷም ካንተ ደካማነት ተነስታ አማራጭ በማጣት ራሷን፣ ትዳሯንና ልጆቿን ብትመራ ከዚህም የተነሳ ለሚፈጠረውም ኾነ ለሚፈጠርባት ችግር ግን የመጀመሪያው ተጠያቂ አንተው ራስህ ነህ።

ተፈጥሮዋን መመርመር፣ ተፈጥሮኣዊ ጥያቄዋን ባግባቡ መመለስ፣ አንተ በተሰጠህ ስልጣን መሰየምና መገኘት፣ እርሱንም በአግባቡ መፈጸም ኃላፊነትህ ግዴታህም ነው።

የአንተ በሚናህ መገኘት እርሷ ሚናዋን እንድታውቀው፣ እንድትወደው፣ እንድትወጣውም ያደርጋል ባትኾን(እርሷ) እንኳ አንተ እረሷን ግድ ብትል ወግ ይኾናል(ተገቢነቱ ይታያል)።

አንተ ትክክለኛ ቦታህን ስትይዝ ነውና እርሷም ቦታዋን የምታውቀው በአጉል ስልጣኔና በስንፍና ተይዘህ የአባወራነት ውልህን አትሳት። 

            ፨ መሪ መኾን ካልቻልክ በፍጹም እንደማትከተልህ፣ 
            ፨ በስርዓቱ ማዘዝን ካላወቅክበት እንደማትሰማህ፣ 
            ፨ አንተ አርኣያ ካልኾንካት ለልጆችህ ምሳሌ እንደማትኾናቸው ተረዳ።

ስለዚህ መጀመሪያ አንተ የቃልህ፣ የሕግህ፣ የስርዓትህ ሰው ኹን። ፈጣሪህ የሰጠህን ሕግ ከራስህ የወጣውንም ቃል ጠብቅ። ራስህን አትካድ። ሳይኾን ቢቀር ግን ከፍጹም ልብህ የመነጨን ንስሃን ከእርሱ፣ ይቅርታንም ከተገቢው አካል ጠይቅ። አንተ በሰውነትህ መከበርን እንደሻህ ሌሎችን በሰውነታቸው አክብር።

ያንተን የቤት ሥራ ከሠራህ ከሚሰትህም የምትጠብቀው እንዲሁ ይኹን። የፈጣሪዋን ቃል ያንተንም የቤትህን ስርዓት አስተምራት። ካወቀችውም በሕይወት መኖሩን ግድ በላት። በጭራሽ! ስንፍናዋን አልያም ግዴለሽ ሥራዎቿን ፍቅርን ተገን እያደረግክ አትለፍ! 

የምንዴት መልሶችንና የምንቸገረኝ ድርጊቶችን  ማለፍ በምንም ዓይነት መልኩ የፍቅር ውጤት አልያም መለኪያው አይኾንም። ይልቅስ ላንተ ያላትን ክብር የሚቀንሱ እንዲያውም ንቀቷንም የሚጨምሩ ግብዓቶች እንጂ። ይኽ ሲኾን በምክር ጀምረህ፣ በተግሳጽ ደግመህ፣ በቅጣት ብታሰልሰው አንተ በክብርህም ኾነ በቃልህ የማትደራደር መኾንህን ትረዳለች። 

ይኼ እንግዲህ ልትጨብጠው የሚገባህ ተፈጥሮኣዊ መርህ ነው። እኔም ኾንኩ አንተ አልያም ሌሎች ወንዶች ይኼን ግዴታችንን አውቀንም ኾነ ሳናውቅ የተሰጠንን ኃላፊነት ከነግዴታው ሳንወጣ አልያም በተሰጠን ስልጣን ብንበድል ከዚህም የተነሳ ሚስቶቻችንም ኾነ ልጆቻችን በኛም ኾነ በፈጣሪ እንዲሁም በሀገራዊው አስተዳደር ላይ ቢያምጹ ተጠያቂው እኛው (እኔና አንተ) ነን።

ለዚህ መፍትሔው ደግሞ ቀድሞውኑ ቦታውን ባለመያዙ የችግሩ መንስዔ የኾነውን ወንድ ማስተማር ነው። ይኼም እንዴት ነው ቢሉ …… ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *