ከአባወራነት ጉዞህ የሚያስተጓጉሉህ


ሳተናው!

ራስህን በማሻሻሉ ሂደት ላይ ኾነህ ወደ ኋላ የሚጎትቱህን ኃይሎች መለየት ለውጥህን ከማፍጠኑም በላይ በጥራትም እንዲኾን ያደርገዋል።

እነዚህ ኃይሎች ብዙውን ጊዜ የማናስተውላቸው የጭቃ ውስጥ እሾኾች አንዳንዴም ደግሞ የምናውቃቸው፣ የምናያቸው በቀላሉ ግን ቆርጠን ለመጣል የሚከብዱን ይኾናሉ።

አንዱ እና ዋነኛው አንተን ከአባወራነት ጉዞህ የሚያስተጓጉልህ አንተው ራስህ ነህ። ከበዛው የራስ በራስህ እንቅፋትነት ውስጥ ደግሞ ትልቁን ቦታ የሚይዘው በሥነ-ስርዓት አለማደግህ ነው።

ሳተናው ልብ አድርግ! በሥነ-ምግባር አለማደግህ አላልኩም በሥነ-ስርዓት አልኩኝ እንጂ። ብዙዎቻችን አንገታችንን ስለደፋን፣ ጭምት ስለኾንን፣ መንፈሳዊ ቦታም ስላዘወተርን ብቻ በሥነ-ስርዓት ተኮትኩተን ያደግን ይመስለናል።

ይኹን እንጂ በዓላማ የመንቀሳቀስ፣ በሚናችን የመገኘትና ጸጋችንን የመረዳት ክፍተት ስላለብን ኑሮኣችን ትርጉም የለሽና ፍሬ አልባም ይኾናል።

በተጨማሪም ነገሮችን የምናደርግበት የታወቀ፣ የተረዳና ጉልህ የኾነ አካኼድ ስለማይኖረን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን አሰልቺ እና ተስፋ አስቆራጭ ቢኾን አይገርምም።


ሳተናው!
ከዚህም የተነሳ ለኑሮህ አሰልቺነት ሰውን፣ ዓለምን፣ መንግስትን ከመውቀስህ በፊት ራስህን በሥነ-ስርዓት አሰልጥን ከዚያ ግዛው፣ ምራውም።

ከማንም እና ከምንም በፊት ራስህ በራሰህ ላይ ሙሉ ስልጣን ይኑርህ፤ ለስንፍናህ በ”ሳይንስ” የተደገፈ በ”መንፈሳዊነት”ም የተከሸነ ሰበብ አስባብ አትደርድር። ከሰው በፊት ደካማ ጎኖችህን ነቅሰህ አውጣ አስወግዳቸውም።

ከዚህ ሲቀጥል ብዙውን ጊዜ ወደ ኋላ የሚጎትቱህ በአንተም ኾነ በራሳቸው ሕይወት ላይ ምንም ዓይነት እሴት የማይጨምሩ ወዳጆችህ ናቸው።

ምንም እንኳ ማሕበራዊ ሕይወትህ በኑሮህ ውስጥ ጉልህ ሚና ቢኖረውም ብዙውን ጊዜ ግን ከወዳጆችህ ምንም ዓይነት ፋይዳ በሌለው በእንቶ ፈንቶም በተሞላ ግንኙነት ታሳልፈዋለህ።

እነዚህ ወዳጆችህ ምንም እንኳ አንተን የመጉዳት ዓላማ ባይኖራቸውም የእነርሱ የኑሮ ዓላማ ቢስነት ኢ-ሥነስርዓታዊም ጉዞ አንተን ከርዕይህ ወደ ኋላ የመጎተት አቅም አለው።

ስለዚህም ወይ እንዳንተው ዓላማን ሰቅለው ራሳቸውን ገዝተው ለመኖር ይሞክራሉ አልያም አንተ ከእነርሱ ተለይተህ ትኖራለህ። በአጉል “አብሮ-ኣደጌ” ነት ተይዘህ የሌሎች ስንፍና እንዲጋባብህ አትፍቀድ።

በመጨረሻ ላይ ልጨምርልህ የምፈልገው ደግሞ ስንፍናቸውን ማስወገድ ያልቻሉ ነገር ግን ሌሎች ከስንፍናቸው ተላቀው ወደ ስኬት ሲኼዱ ሲሳካላቸውም መቀበል ከማይፈልጉት እንድትርቅ ነው።

እነርሱ የትኛውንም ጥረትህን ለመቀበል፣ ለማበረታታትና ለማድነቅ የሚተናነቃቸው ናቸው። ይበልጡንም በጥረትህ ውስጥም ያለን ትጋት፣ በሙከራህ ውስጥም ያለህን ተስፋ፣ በውድቀትህ ማግስት ያለህን ትንሳዔ ከማየት ይልቅ ስሕተትህ እና ውድቀትህ ብቻ እየታያቸው እርሱንም እያስተጋቡ የሚነግሩህ ናቸው።

ለምሳሌም ማልደህ መነሳትህን፣ ስፖርት ማዘውተርህን፣ ማንበብ መውደድህን፣ ራስህን የመለወጥ ጥረትህን፣ ትዳርህንና ቤትህን የመምራት ጥበብህን የመሳሰሉትንም ጭምር ማድረጉን አይችሉምና የራሳቸውንም ኾነ የዓለምን “ማስረጃ” በማቅረብ ይነቅፉብሃል፣ ያጣጥሉብሃል፣ ይኮንኑህማል።

አንድም ቀን አፋቸውን ሞልተው “ይኼን ጥረትህን፣ ይኼንና ይኼን ስኬትህን አደንቃለሁ፤ እንዴትስ አድርጌ እኔም ገንዘብ አደርጋቸዋለሁ? ” አይሉህም። ይልቁንስ ከመንፈሳዊ ሕይወትህ ሕጸጽ፣ ከኑሮህም ድካም፣ ከልምምድህም ዝንፈትን ነቅሰው በማቅረብ ያንተን በማጣጣል ለእነርሱ ስንፍና “መጽናኛን” ያበጃሉ።

ሳተናው!
በተለይ እነዚህ በመጨረሻ ላይ የጠቀስኩልህን “ወዳጆች” ምንም ዓይነት ቅርበት ቢኖርህ እንኳ ልትርቃቸው ሲገባ ርቀህ የማትርቃቸው፣ ቆርጠህም የማትጥላቸው የቅርብ ዝምድና ቢኖርህ ግን በርዕይህ፣ በሚናህና በጸጋህ ዙሪያ አስተያየትን እንዲሰጡህ አትፍቀድላቸው፤ የምትጫወቱበትንም ድንበር በግልጽ አስቀምጥላቸው፤ ማንም ቢኾኑ እንኳ!

የአባወራነት ጉዞህን ሰዎች “ይደግፉልኛል፣ ያበረታቱኛል፣ ያግዙኛልም” ብለህ ወደ ዓለም አትሂድ። ዓለም እንዳንተ ዓይነት ባለርዕይ፣ ቆራጥ እና ጀግና ሰው ሲመጣላት ብትስተካከልና ቢያምርባትም አጨብጭባ ግን አትቀበልም።

ይልቁንስ መሰሎችህን በመፈለግ ድካም ሲሰማህና ፈተናውም ሲያይልብህ የእነርሱን ድጋፍ እየጠየቅክ፣ ስለተዘረጋልህም እጅ እያመሰገንክ ወደ ፊት ትገሰግሳለህ እንጂ።

ብዙውን ጊዜ ግን አሁን በምንኖርባት ዓለም ተፈጥሮህን ተረድተህ፣ እውነትን ጨብጠህ፣ ሚናህንም ለይተህ በተሰጠህ ጸጋ ወደ ዓላማህ ለመሄድ ከተነሳህ ጉዞህ የብቸኝነት እንደኾነ አስቀድመህ እወቅ፤ ኾኖም ግን አትፍራ ወንድምዓለም! በጭራሽ አትፍራ!

እውነት ከፈለግካት አርነትን ስታጎናጽፍህ ፍርሃትህን ገፋ ነው!

ልብ አድርግ!
ጀግና አንድ ቀን ነው የሚሞተው አልጫ ግን እድሜ ልኩን በፍርሃት ይሞታል!

በተፈጠርክበት ልክ፣ በተወሰነልህ ሚና፣ በተሰጠህም ጸጋ ጸንተህ በመክሊትህም አትርፈህ መገኘት አባወራነት ነው፤ ምንም እንኳ ይህን ዓለም ባትወድልህም።

ዓለም አባወራነትህን አትወደውምና አታግዝህም…. ይቆየን
Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *