ከጠረጴዛና ወንበር የሚልቀው ሀገርንም የሚገነባው ሚናህ

አንተ ዛሬ አባወራ (ባለትዳር፣ አባት፣ የቤትህ መሪ) ኾነሃል አልያም በዚያው መንገድ ላይ ትኾን ይኾናል። አንድ ልብ ልትልልኝ እና ልትገነዘብልኝ የምፈልገው ነገር አለ። በቤትህ ውስጥ ያንተ የሥራ ድርሻ ጠረጴዛና ወንበርህ ከሚጫወቱት ከሚሰጡትም አገልግሎት እጅግ የራቀ ነው።

የመገናኛ ብዙሃኑና እነዛ አልቅሰው የሚያስለቅሱህ “ዘፋኞች” ያለ ሴት መኖር እንደማትችል ሲነግሩህ ያንተን ሚና ገሸሽ በማድረግ ነው። በትዳር ውስጥ ደግሞ ለትውልድ መቀጠል የእናት ድርሻ በተደጋጋሚ ሲቆለጳጰስ የአባት ግን(በቁጣውና ቅጣቱ) ሲጠለሽ፣ ለልጆቹም እናት ሸክም ተደርጎም ሲሳል ታያለህ።

ይኹን እንጂ ይኽ ዛሬ ዛሬ ከቤትህ ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች የምታየው መረንነት ምንጩ የአባት(የባል) ሚስቱን፣ ልጆቹን፣ ቤቱን በስነስርዓትና በስነምግባር አንጾ ያለማሳደግ ችግር ነው። ጠንካራ የስብዕና ግንባታ በአባት የሚፈጸም ነው። ያለእርሱ ትዳር አይቆምም፣ ልጆች ቅጥ አይይዙም፣ ትውልድ መረን ሲወጣ ሀገርም ትፈርሳለች፣ ጠላቶቿ ሲዘባበቱባት፣ ስግብግቦችም ይናጠቋታል።

ሳተናው ወንድሜ!
በእርግጥ በዛሬ ጊዜ እንደድሮው ዘመን “ወንድ በችሎት ሴት በማጀት” ብሎ መኖሩ የሚከብድና ያንተን የቤት ውስጥ ተሳትፎ የሚስትህንም ሠርቶ መግባት ቢፈለግም ቅሉ፤ ይኽ ሚስትህን ልጆችህን ቅጥ ማስያዙን ለእነርሱም ኹነኛ ጊዜ መስጠቱን ሊያስተውህ ግን አይገባም።

አንተ ቤትህ ውስጥ ለሚስትህ እና ለልጆችህ የምትሰጣቸው ተፈጥሮኣዊው አገልግሎቶች (መሪነት የምትመራውን ማገልገል መኾኑን ልብ ብለሃል?) በፈለጉት ጊዜና ቦታ እንደፈለጉም ስበው ከሚቀመጡበት ጠረጴዛና ወንበር ፍጹም የተለየ ነው። አልያ ግን ልጆችህን እያበላሸህ፣ ትውልድን እየገደልክ፣ ለሀገርም ሸክም እያተረፍክ መኾንህን አስተውል።

አንተ እንደ አባት መኖርህ ለልጆችህ ከምትሰጣቸው የትኛውም ስጦታ ይበልጥ ያስፈልጋቸዋል። መኖርህ ደግሞ ብቻውን ሳይኾን ስሜታዊ ለኾኑት ልጆችህና ሚስትህ ስሜትን መግዛት፣ በስሜታቸው ላይ መሰልጠንና ከእርሱም በላይ ኾኖ ሚዛናዊና የተረጋጋ ኑሮ መመሥረትን የምታስተምራቸው አንተ ነህ።

ወንድሜ ብዙ ሴቶች እህቶቻችን ያሰበላቸው በሚመስላቸው ነገር ግን አጥፊያቸው በኾነው በሴታቆርቋዡ እሳቤ (Feminism) ጨርሰው ጠፍተዋል። ከዚህም የተነሳ የአባታቸው እነሱን፣ እናታቸውንና ቤቱን ቅጥ ማስያዝ ተጠይፈው፣ ሰብሳቢነቱንም ንቀው በአልባሌ ሕይወት ይገኛሉ። ይኼንኑም ሲያገቡ በባላቸው ላይ በሚያሳዩት ንቀት ይደግሙታል። 

ከዚህም የተነሳ የእነርሱን ፈለግ የተከተሉ ለአባታቸው ክብር የሌላቸው ስሜታቸውን ብቻ የሚሰሙ፣ ለእርሱም የተገዙ፣ ከእርሱም በላይ ነግሰው መኖር የማይችሉ ሲበዛ ስሜታውያን(ኾድ የባሳቸው፣ ሳይናገሯቸው የሚከፋቸው፣ ሳይመቷቸው የሚያለቅሱ፣ ሳይነኳቸው የተጠቁ፣ ሳያስቧቸው የተደፈሩ….) ልጆችን ያፈራሉ።

ቀላል የቤት ሥራ ልስጥህ
ከራስህ ጀምርና በዙሪያህ ያሉትን ጓደኞችህን ታዘብ፤ ልብ አድርግ ዙሪያህን ማየትህ ሌሎች ላይ ጣትህን እንድትቀስር እንድትከሳቸውም ሳይኾን ከስሕተታቸው እንድትማር እንጂ። ብዙዎች ኾደ ባሻዎች ናቸው በዚህም አባታቸው በቤት ውስጥ እንዳልነበረ ቢኖርም ከጠረጴዛና ወንበር የተሻለ ሚና እንዳልነበረው ትታዘባለህ። አልያም ደግሞ ልጆቹን የሚቀጣና ቅጥ የሚያሲዝ ከሚመስል ነገር ግን ሚስቱ ከምትግተው ንቀት የተነሳ ገንፍሎ ልጆቹን ከሚያጠቃ ምስኪንና ፈሪ አባት እንደተገኙ ታስተውላለህ።
፩ኛ ስለራሳቸው ያላቸው ዋጋ ዝቅተኝነት፦ ዋጋ የሌላቸው የማይጠቅሙ ርካሽ እንደኾኑ ያስባሉ አልያም ዋጋቸውን ከሌሎች አንጻር ያስቀምጣሉ፣ ራሳቸውን በማንጸሪያ ያስረዳሉ እንጂ በራሳቸው ምሉዕና በቂ መኾናቸውን አይገልጹም። 
፪ኛ ዝቅተኛ የራስ መተማመ ሲኖራቸው የራሳቸውን አቅም ይጠራጠራሉ፤ አባቶቻቸው የሠሩትንም ሥራ አለማመን ብቻ ሳይኾን ይክዳሉ የእነርሱንም ኾነ የወላጆቻቸውን አቅም ይጠራሉና።
፫ኛ ስሜታዊነት፦ ይኽ በተለይ የአብዛኞቹ ያለአባት የሚያድጉ ልጆች መለያ ነው። ማጅራታቸውን መትቶ የዘረፋቸውን አልፈው ሶፍት የወሰደባቸውን አፈር ድሜ ሲያስግጡ፤ የሚስታቸውን ንዴት ሊታለፍ የሚችለው የልጃቸው ጥፋት ላይ ገንፍለው አጉል ሲቀጡ ይስተዋላሉ። ጠዋት “ይኽ ሰው ጻድቅ ነው ታቦት በስሙ ካልቀረጽንለት መንገድም ካልሰየምንለት ብለው” ብለው መግቢያ መውጪያ ያሳጣሉ። ከሰዓት ላይ ይኽንኑ ሰው አርቀን ካልቀበርን አብረን መኖር አንችልም ብለው አድማ ይመራሉ።

እነዚህ ኹሉ እንግዲህ አንተ በቤትህ ያለህን ስነስርዓት የማስተማር ስነምግባርንም የማስረጽ ሚናህን ሳትወጣ ስትቀር የሚገኙ ጋጣወጥም የሚኾኑ ትውልዶች ናቸው። ሲጀመር አንተ የዚህ አስተዳደግ ሰለባ ከኾንክ ራስህን የመመለስ የማቅናትም አቅሙ አለክ እስከፈለክ ግን እንጂ።

ይኹንና ይኼን ዓይነት ትውልድ ተፈጥሮ በስሜት እየተነዳ ራሱን፣ ወገኑንና ሀገሩንም ሲያጠፋ እያየህ ከማዘን ልጆችህን በስጦታ ማንበሽበሹን ትተህ ራስህን ስጣቸው። በስነስርዓት እየኖርክ ግብረገብም ኾነህ አስተምራቸው። በቤትህ ውስጥ ከጠረጴዛና ወንበር በተሻለም አገልግላቸው።

ኖረኽ ኑሩ ኾነህም ኹኑ የምትል ቃልህና ምግባርህ የተስማማልህም ኹን።ይቆየን….

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *