ወስን! ፪ ምስኪንነትህን ሳትጥል ወደ ትዳር አትግባ

ሳተናው!

ወደ ትዳር ከመግባትህ በፊት ራስህን ፈትሽ። ምስኪን ነህን? ጥያቄው ግልጽ ካልኾነልህ ከዚህ በፊት ስለምስኪን የጻፍኳቸውን ጦማሮች አንብብና ራስህን የቱ ጋር እንዳለህ ታዘብ።

ዐለም ብዙ የውሸት ተረቶች አሏት። አንተ ግን የፈጣሪህን ትዕዛዝ ባንተ ላይ ያለውንም ዓላማ ስትረዳ የሚከተለውን ቃል እውነትነት ትገነዘባለህ፦

“ወንድ ልጅ መከበርን ሴት ልጅ መወደድን” እንዲሹ

“እርሱ እኮ በጣም ምስኪን ልጅ ነው!” ሲሉህ ተወድጃለሁ ብለህ አትደሰት። ተፈጥሮህ በምስኪንነት ከሰው ምስጋናና ሙጋሳ እየተቀበልክ ለመኖር አይደለም። እየኖርክ ስላለኸው ሕይወት እና ስለራስህም ጥርት ያለ ምንነት እና ማንነት አቋምም ይዘህ በዓላማ እንድትኖር እንጂ።

በፍጹም ሰው ወዶኛል ተጨብጭቦልኛልም እያልክ ሙገሳና ይኹንታን እየተከተልክ አትጓዝ። ይልቁንም ምስኪንነት የፍቅር ግንኙነትህን ከሚያሻክሩ፣ ትዳርህን ከሚያፈርሱ ቀንደኛና አፍራሽ ጠባዮችህ አንዱ እንደኾነ እወቅ።

ምስኪንነት በተለይ በዚህ “ዘመናዊ” ማሕበረሰብ ለፖለቲካ ፍጆታነት የዋለ ይኹንታና እውቅናም የተሰጠው ወንድነትህን ግን የሚሰልብ ማንነት ነው። 

ምስኪንነት፦ ሚስትህ “አክብሬ ላስከብርህ” ስትልህ እንኳ የተዋረደችብህ መስሎህ  የክብር ቦታህን ያሳጣሃል።

👉 በምስኪንነትህ በአፍኣ የኾነ (ከልብ ያልኾነ) የአንደበት ምስጋና ብታገኝበት እንጂ ምንም በጎ አታተርፍም።

👉 በምስኪንነትህ ሰውን ትጠቅምበታለህ እንጂ አትጠቀምበትም
👉 በምስኪንነትህ መልካም ብትዘራም አመድ አፋሽ ነህ
👉 በምስኪንነትህ ሴቶች ቢያሞግሱህም የፍቅር ጥያቄህ ግን ተቀባይነት የለውም
👉 በምስኪንነትህ ማር ብትኾን ሰዎች እያደነቁህ ልሰው ይጨርሱሃል እንጂ ያልቅብናል(ይጎዳብናል) ብለው አይሳሱልህም
👉 በምስኪንነትህ አመድ አፋሽነትህን ስታውቀው በውስጥህ ቁጣን ታጠራቅማለህ እርሱም የኃጢአትና የጥፋት ምክንያት ቢኾንህ እንጂ አንዳች ጽድቅን አይሠራልህም።
👉 ምስኪንነትህ ፍርሃትንና ስንፍናን በፍቅርና በመንፈሳዊነት ስም በላይህ ቢያሰለጥንብህ እንጂ ቆራጥና ደፋር አያደርግህም።
👉 በምስኪንነትህ ላላጠፋኸው ይቅርታ ላመንክበት ጉዳይ ይሉኝታ እንደ ወግ ያሲዝሃል
👉 በምስኪንነትህ ሰዎች ሳትበድላቸው ለካሳ፣ ባልሠራኸው ወንጀል ለከሰሳ ይጣደፉብሃል።
.
.
.
.

በጾታዊ ግንኙነት ምስኪን መኾን ስትጀምር ወይም ምስኪን ከኾንክ በዙሪያህ ያሉ ሴቶች መተኪያ የሌለው ወንድም “ምርጥም” ጓደኛም ያደርጉሃል። አንተ እንደምታስበውና እንደ እነርሱ “እርሱ እኮ እንዴት ዓይነት ምስኪን ልጅ መሰለሽ? ስወደውኮ!” አድናቆት ለፍቅር ጥያቄህ መልስ አያስገኝልህም።

ሳተናው!
ወደ ትዳር ከመምጣትህ በፊት ራስህን መጀመሪያ ከምስኪንነት አስተሳሰብ ነጻ አውጣ። የትዳርም ኾነ የጾታዊ ግንኙነት ስምረት ያንተን የወንዱንና የሴቷን ዋልታነት ያሻል።

መመሳሰላችሁ ሲያይል ዋልታነታችሁ ይፈዛል። ዋልታነታችሁ ሲዳከም በመሃል ያለው የመሳሳብ (የአንድነቱ) ኃይል ይላላል። የአንድነታችሁ(የአብሮነታች) ኃይል ሲላላ በተለምዶ ፍቅር ቀዘቀዘ፣ አለቀ(ጨዋታ ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ) ይባላል።

ለፍቅር ግን የሚለካና የሚቆረጥ የሚሰፈርም መጠን ኖሮት ሳይኾን በተለይም ምስኪንነት ሁለቱን ያዋደደውን ዋልታነት ስለሚያጠፋ የፍቅሩንም ጥፍጥና ስለሚያደበዝዝ እንጂ።

ለጭድ ሕልውና እሳት፣ ለብረትም ሕልውና ውሃ እንዳይስማማው ለጾታዊ ፍቅር፣ ለትዳርም ከውስጡ ለሚወጡት ልጆች ምስኪንነት አጥፊያቸው ነው።

ሳተናው!
አዎ! የምነግርህን ለመቀበል እንዲከብድህ አውቃለሁ ነገር ግን ጣፈጠህም መረረህም እውነቱ ይኼው ነው። በምስኪንነት የምትመሠርተው ፍቅር የምትገባበትም ትዳር ውጤቱ(መጨረሻው) አያምርም።

ልብአድርግ! ምስኪንነት ዘመን አመጣሽ፣ አጉል ስልጣኔ ግልብ-መንፈሳዊነትም ነው። በተፈጠርክበት ልክ፣ ለተጠራህበት ዓላማ፣ በተሰጠህም ሚና ምሉዕ ኾነህ እንድትኖር ጊዜው ያለበሰህን ምስኪንነት ተው።

አንተ ምስኪንነትን ስትተው ጤናማ ትዳር፣ ስርዓትና ርዕይ ያለው ትውልድ፣ ሀገራዊ አንድነት ያለውም ሕብረተሰብ ማፍራት ይቻልሃል።

ሳተናው! ምስኪንነት የወንድነት፣ የባልነት፣ የአባትነት፣ የራስነት ክብርህን የሚያሳጣህ የሚያስክድህም ነው። በጭራሽ እርሱን ሳትጥል ወደ ትዳር አታምራ ኋላ ማጣፊያው ያጥርሃና።

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *