ወስን!

ሳተናው!

ብዙዎች አባወራ እንዴት መኾን እንደሚችሉ ማድረግ ያለባቸውንም ቅደም ተከተል ማወቅ ይፈልጋሉ። ብዙ ጊዜያቸውንም እነዚህን በመፈለግ ያጠፋሉ።

ይኹንና እነዚህን ቢያገኙም ስኬታማ ሳይኾኑ ይቀራሉ። ከዚህም ተነስተው በዚህ ዘመን/ዓለም ሴታውል፣ ዱርዬ አልያም ምስኪን ከመኾን ውጪ አባወራ መኾን እንደማይችሉ ይወስናሉ። ለዚህም ምክንያታቸው ዐለም “በውሸት/ በሙስና ተበላሽታለች” ነው።

አንተ ግን ሳተናው አባወራ ለመኾን የሚያስፈልግህ ቀዳሚው እርምጃህ ውሳኔ ነው። ሳትወስን የት ትሄዳለህ የትስ ትደርሳለህ። ምንም ዓይነት መጽሐፍ ብታነብ በየትኞቹም ዓይነት ልምምዶች ውስጥ ብታልፍ ልብህ ውስጥ ለመለወጥ ቁርጥ ውሳኔ ከሌለ ከንቱ ትደክማለህ። ምክንያቱም ምኞትና ውሳኔ ይለያያሉና።

አስረጅ የግል ታሪክ

የዛሬ አምስት ዓመት የዛሬውን ሄኖክ ኃይለገብርኤል  ከድሮው ምስኪኑ እና ንክሩ ሄኖክ ጋር የሚለይ አንድ አጋጣሚ ተፈጠረ።

በዚያንም ወቅት አንድ ነገር አደረግኩ እርሱም ራሴን በወቅቱ ከነበርኩበት “ምንም አይልም” ዝቅታ ዛሬ”አባወራ” ወደምለው ከፍታ ለመውጣት ወሰንኩ። ይኹን እንጂ እንዴት እንደምኾን አላውቅም፤ ነገር ግን ቆረጥኩ ከዚያ ወዲህ አንድም ቀን ወደኋላ አልተመለስኩም አላስብምም።

ሳተናው!

ቁርጥ ውሳኔ ሲኖርህ እንዴት እንደምትኾን እና የምትሄድበትም መንገድ ደረጃ በደረጃ እየተገለጸልህ ይመጣል። እውነታውን አልደብቅህም እርሱም፦ ይኼኛው መንገድ ትላንት ከነበርክበት የምስኪኑ መንገድ ይልቅ ብዙ አድካሚ እና ግጭትም የማያጣው ነው።

ኾኖም ግን ከቀደመው “ለጊዜውም ቢኾን ይበቃኛል፣ ይመቸኛል፣ ምንም አይልም፣ ችግር የለውም” ከምትለው መንገድ(ሕይወት) ጋር ደረጃው ፍጹም አይገናኝም። በዚኽኛው ሕይወትህ  ፍጹም ልዕልና ስሜቶችህ ላይ፣ ከፍተኛ የራስ በመተማመን በድርጊቶችህ ላይ እና እነዚህንም የምትፈጽምበት ኃይል(ወኔ) ትታጠቃለህ።

እኔ በዚያን ወቅት የትኛውም ፈተና፣ እንቅፋት ተስፋ አስቆርጦ ወደ ምስኪንነት እንደማይመልሰኝ ለራሴ ቃል ገባሁ። ኖሬ አይቼዋለሁ እና ከጥቅሙም ጉዳቱ አመዝኖብኛልና በየትኛውም ሽንፈት ወይም መደለያ ተመልሼ እንዳልወሰድ ራሴን አሳመንኩ።

ነገር ግን ሰው ነኝና ለዘመናት የኾንኩትን ማንነት በአንድ ቀን ውሳኔ እርግፍ አድርጌ መጣል አልችልም፤ አኹንም የዚያ “የምስኪኑ ሄኖክ”  ርዝራዥ ምስኪንነት ውስጤ እንዳለ ይሰማኛል፤ ይታወቀኛልም።

በዚያ የውሳኔ ወቅት እንዴት ከምስኪንነት እንደምወጣ፣ ማን እንደሚያግዘኝ የማውቀው ነገር የለም። ነገር ግን ቁርጥ ውሳኔ ራሴ ላይ አስተላለፍኩ። ሲቀጥል ያደረግኩት ነገር ይኼን “ምስኪን ሄኖክ” እንደማልፈልገው ውሳኔዬን ማሳወቅና ከእርሱ የምገላገልበትን መንገድ እንዲመራኝም በጸሎት ፈጣሪዬን መጠየቅ ነበር።

ለዚኽ ውሳኔዬ አማራጭ አላስቀመጥኩም፤ እርሱን መኾን ብቻ ነበር። ከውድቀቴ ከስሕተቴም እየተማርኩ መሄድን እንጂ ለሽንፈት እድል አልሰጠኹምና የሚያቆመኝ አልነበረም፣ ወደፊትም እንዲሁ።

ሳተናው!
ዝርዝር ጉዳዮቹን፣ መንገዱን ዘዴውንና አፈጻጸማቸውን ለጊዜው አቆይና መጀመሪያ ቁርጥ ውሳኔ ያዝ። መኾን ስለምትፈልገው ነገር (በእኛ ዐውደ-ንባብ “አባወራ”) ጥርት ያለ እውቀት፣ መኾን እንዳለብህም ቁርጥ ውሳኔ አለቀ! ሌላው ኹሉ ከፊት ለፊትህ  እየተገለጠ ይመጣል።

ብዙዎች
==================================
የአባወራ ገጽን አንብበው ተራ የምኞት ጽሑፍ ይመስላቸዋል። እውነትነት ያለው ነገር ግን በዚኽ ዘመን የማይሞከር መፈጸምም የማይቻል ከጽሑፍነት አልፎ ተግባራዊ የማይኾን ያደርጉታል። በእንቅልፋቸው ካዩት ሕልም ለይተው አያዩትም።

ለእኔ ግን በሕይወት የተፈተንኩበት፣ በንባብ ያዳበርኩት፣ በምክርም ያጸናኹት እውቀት እንጂ ተራ ፍላጎትና ምኞት አይደለም።

ጥቂቶች
=========================
እነዚህ ደግሞ መኾን ፈልገው በምኞት ብቻ ይባክናሉ፤ ብዙ ያነባሉ(ጠብቆ ይነበብ)፣ ይመከራሉ፣ ነገር ግን መለወጥ አይችሉም። ለምን? መኾን የፈለጉትን “አባወራ” ወይ አያውቁትም አልያም ለመኾን ቁርጥ ውሳኔ የላቸውምና ነው።

በጣም ጥቂቶች
================================
በጣም ጥቂቶች ግን ለመለወጥ ቁርጥ ውሳኔ ይወስናሉ፣ የመጣውንም ይጋፈጣሉ። አንድ በገሃዱ ዓለም ያለን ሐቅ በተለይም (ጾታዊ ፍላጎቶቻችን እና ሚናችን) ሰው ስለተስማማበት፣ በምክር ቤትም ስለጸደቀ ሳይኾን ተፈጥሮኣዊ እውነቱን ይፈልጋሉ፣ ይሞግታሉ፣ ያውቃሉም፤ ያወቁትንም በሕይወታቸው በመኖር እየወደቁ እየተነሱም ካሰቡት ይደርሳሉ።

ሳተናው! ይኽቺን ሕይወት ደግመህ አታገኛትም፤ በተጠራህበት ልክ፣ በተሰጠህ የአባወራነት ጸጋ ተጠቅመህ ለተፈጠርክለት ዓላማ ኑረህ እለፍ። …ይቆየን


Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *