ወንዱን አልጫ ሴቷን ወንዲላ


ወንዱን አልጫ
ትርጉም አልጫ፦ 3.ቡከን የማይረባ፣ ፎድፏዳ፣ ልፍስፍስ
4.የይድረስ ይድረስ ሥራ፣ ውስጡ ባዶ የኾነ፣ ፍሬ ከርስኪ ነገር
ባሕሩ ዘርጋው፡ ዘርጋው ከፍተኛ የአማርኛ መዝገበ ቃላት 2010 ዓ.ም. ሮኾቦት አታሚዎች

ሳተናው!
ማነው በዚኽ ዘመን ወንዱን ተነሳ ታጠቅ የሚለው? (አስፈላጊ ከኾነ የጦር መሣሪያ መታጠቁን ባልቃወምም እዚኽ ጋር ግን መጥቀስ የፈለግኩት ለሥራ፣ ለእድገት፣ ለምርት፣ ለለውጥ ነው)

እስቲ ወንድሞቻችን/ ልጆቻችን ምን እየተማሩ ነው? በተፈጥሮ የተሰጣቸውን ድፍረት፣ ጡንቻና ኃላፊነት መውሰድ እየሻርንና እያጠፋን መኾናችንን አናስተውለውም። አኹን ያለነው ወላጆችም ኾነ መምኽራን ደፋር፣ ጠንካራና ውድድር የተሞሉ ጨዋታዎችን ልጆች እንዳይጫወቱ እያደረግን በምትኩ ደግሞ ምንም ዓይነት “አደጋ”(risk) ሊያመጡ የማይችሉ፣ ፉክክርንና መሸናነፍን ያልተሞሉ፣ ከሌሎች ጋር መቀላቀልና መነጋገርን የማይጋብዙ ጨዋታዎችን እናበረታታለን።

ይኽ ሲኾን ወንዶች ልጆቻችን ያሉበትን የኑሮ ኹኔታ አሸንፈው ከመውጣት ይልቅ ተላምደውት የሚኖሩ ከዚህም የተነሳ በተገኘው ፈተና አእምሮኣቸውንና የአካል ብቃታቸውን በማጎልመስ ከማትረፍ ይልቅ በአቋራጭ ኑሮን ለማሸነፍ የሚተጉ ይኾናሉ። በማሕበራዊ ሕይወትም ያላቸው ሱታፌ አነስተኛ ነውና ራሳቸውን መግለጽ የማይችሉ ቢገልጹም ስነስርዓትና ስነምግባር በተለየው መልኩ መኾኑ እሙን ነው።

ይኼን ወንዱን አልጫ የማድረጉን “ጥበብ” ምዕራብያኑ በደንብ ተክነውበታል። ይኽንንም በራሳቸው ዜጎች ላይ ተግብረውት ተሳክቶላቸዋል። በዚህም ዜጎቻቸው(በተለይም ወንዶቻቸው) በጊዜያዊ ደስታ እንዲጠመዱ፣ የራሳቸውን ዓላማ ሰቅለው ለዚያም ዓላማ እንዳይኖሩ፣ አብዛኞቹ ሸማቾች እንዲኾኑ በዚህም ጥቂቶች እንዲበለጽጉ ኾነዋል። ሀገሪቷ ለምትተዳደርበት ፖለቲካ ግድ የሌላቸው ከንቱ ስጋዊ ፈቃዳቸውን በሕግ እያጸደቁ የሚኖሩ ብኩኖች ኾነዋል።

ወንዶቻቸው ብዙ ሴቶች እንደመተዋወቃቸውና ከአብዛኞቹም ጋር እንደመተኛታቸው ልብለልብ ተገናኝቶ ትዳርን መመሥረት ዘርንም መተካት ተስኗቸዋል። ብዙዎቹ እርስ በእርስ በቅጡ የማይነጋገሩ፣ የማይተዋወቁ ይልቁንም ከሰው ይልቅ ከTV እና ከsmart phone ጋር የተለየ ዝምድና ያላቸው ኾነዋል።

ከዚህም የተነሳ ወንዶቹ ሴቶቹን ለትዳር የመጠየቅ ወኔ የሌላቸው ይኾኑና ሴት ፍለጋ የኢንተርኔት መረብ (እኛም ጋር እንደተጀመረው ፌስቡክ….) ላይ ጊዜያቸውን ያጠፋሉ ቢያገኙም ደግሞ ከአንድ ሰሞን የወሲብ ልፊያ ያልዘለለ ቁምነገር አያገኙበትም።

እስቲ አኹን የመገናኛ ብዙኃኖቻችንን አስተውሉ፤ ምን ያክሎቻቸው ናቸው ትውልዱን ራሱን እንዲገዛ፣ በእቅድ እንዲኖር፣ የተለያዩ የሙያ ባለቤት እንዲኾን የሚመክሩ መክረውም የሚያስተምሩ? አብዛኞቹ እኮ ትውልዱን በማያሳርፍ ፍትወት ውስጥ ከተውት ሲታመም እንኳ ራሱን የሚያሳክምበት እንዳይኖረው አድርገው ሸማች ያደርጉታል። ደግሞ ትንሽ ቆይተው የመቆጠብ ባሕላችን ደካማ ነው ሲሉ ተቆርቋሪ መስለው ይመጣሉ።

ሴቷን ወንዲላ
ትርጉም ወንዲላ፦ 1.ከሴትነት ወደ ወንድነት የምታደላ ** ቀረሽ የወንድ ባሕርይ ያላት
2.የሴት ባልትና የሌላት

ባሕሩ ዘርጋው፡ ዘርጋው ከፍተኛ የአማርኛ መዝገበ ቃላት 2010 ዓ.ም. ሮኾቦት አታሚዎች
ስንዱ!
አንቺ እህቴ የመገናኛ ብዙኃን ሴቷን ከወንዱ በበለጠ ዓላማ ቢስና ብኩን አድርጓታል። ሴቷን ጠንካራ “የማትሸነፍ” ለወንድም “የማትንበረከክ” እና “ዘመንኛ” ምናባዊ ሴት በመሳል እንዲያ እንድትኾን አድርገዋታል። ከዚህም የተነሳ ሴቶቻችን ከፈጣሪ የተሰጣቸውን የሴትነት ጸጋ ወደጎን በመግፋት “አንቺም እንደወንዶቹ መኾን ትችያለሽ ” እንደምትባለው ዶክተር፣ ኢንጂነር፣ ወታደር…. ለመኾን ትደክማለች።

ይኽ በእንዲህ እንዳለ ማግባት፣ መውለድና ልጅንም ጡት አጥብቶ እንዲሁም ተንከባክቦ ማሳደግ የማይታሰብ ይኾናል። ቢኾንም እንኳ ለምለም እድሜዋ መጨረሻ ላይ እንደሚደርስ ይነገራታል እንዲሁም ይኾናል።

አንቺ ስንዱ ሴት!
የTV መርሃግብሮችን እስቲ አስተውይ ለሴቶች እህቶቻችን የቤት አያያዝ፣ የወጪ ምጣኔ፣ የሸመታ ዘዴ፣የባልትና ሙያ እና የእደ ጥበብ ትምሕርትን ማን ያስተምራል? እነዚህን አውቆ ማሳወቅና ቤተሰብን ማገልገል፣ ባልንም በገቢ ማገዝ፣? ራስን ከሸማችነት ወደ አምራችነት በመቀየር ሀገርንም ከውጭ ምንዛሪ መታደግ እንደሚቻል ማን ይናገራል?

ከዚህም የተነሳ አብዛኞቹ ሴቶች መኾንና መድረስ የሚፈልጉት ትልቁ ሕልማቸው ወንድ የደረሰበት መድረስ ነው። ይኽ ደግሞ ሴትነታቸውን ገብረው የሚያገኙት ነው። ትኅትና ጌጧ፣ ቤተሰቧን ማገልገል ሙያዋ፣ ባሏን መታዘዝ፣ ሀመልማሎ ጸጉሯ፣ የሴትነት ቀሚሷ ወደር የለሽ ውበቷ መኾናቸው ቀርቶ ወንዲላ መኾኗ እርግጥ ነው።

ይኽ በኹለቱ የጾታ ዋልታዎች መካከል የሚፈጠረው መዛባት ደግሞ በመካከላቸው ያለውን የመከጃጀሉንና የስበቱን ጥንካሬ(ፍቅር) እጅጉን ይቀንሰዋል ብሎም ይጎዳዋል ያጠፋዋል። ወንድሜ ከመጥፋትህ በፊት ከTV ሥር ተነስ እያነበብክ ተፈጥሮኣዊ ማንነትክን አግኝ።

…ይቆየን ሳምንት ወንዶችን “አልጫ” በማድረግ ወደር የማይገኝለት አኹን አኹን እያዘወተርን ያለነው ወንዶችን በመስለብ የወንዶች ጠላት የኾነው ምግብ ማን ነው?

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *