ወንድሜ ሴትን ወድጃለሁ ብለህ ውልህን አትሳት

እህ! ጀግናው አባወራ እንዴት ሰነበትክ? በዘመናችን ላሉ ቁምነገረኛ ሴቶች ትልቅ ፈተና ምን እንደኾነ ታውቃለህ? ወደድኩሽ፣ ከነፍኩልሽ፣ አበድኩልሽ፣ ካላንቺ መኖር አልችልም፣ የሚሉ ፍቅርን ሰበብ አድርገው የሚያላዝኑ ነገር ግን በሕይወታቸው ላይ ጥርት ያለ ዐላማ የሌላቸው ወንዶች መብዛታቸው፤ ራሷን ብትሰጥ አቅፎ ከመተኛት ውጪ የእርሷን የሴትነት የስሜት ማዕበል የማይረዱ ወደብም የማይኾኑ ያልጸኑ፣ ያልቆረጡ ወንዶች መገኘታቸው፤ ለምን እንዳገቡ እንኳን ከስጋዊ ስሜት ወጥተው ትልቅ ርዕይ አስቀምጠው ዐላማንም ሰቅለው ራሳቸውንም ኾነ ቤተሰባቸውን ስርዓት ባለው መንገድ መርተው የማያስከትሉ ከእርሷ የባሱ ስሜታውያን መብዛታቸው ነው። ከተሳሳትኩ እህቶቼ ያርሙኝ።

አንተን ወንድሜን ታዲያ አባወራ እንድትኾን ስመክርህ ከእንደነዚህ አይነት ወንዶች ቀጠና ወጥተህ በእውቀት እና በእውነት ላይ እንድትመሠረት ነው። ያቺ የመረጥካት ሴትም በልበሙሉነት “ይህ ወንድ ነው ባሌ፣ የልጆቼ አባት፣የቤታችንም ራስ(አባወራ) የሚኾነው” ትላለች።

አልያ ግን ፍቅር አሸነፈኝ እያልክ ዐላማህን ያዝ ለቀቅ፣ ሕልምህንም ጥረት ያልታከለበት “ላም አለኝ በሰማይ” ካደረግከው አንተም ሰው አትኾን እርሷም አታከብርህ። ዛሬ ዛሬ ስሜትን በሚቀሰቅሱ ዘፈኖች እና ፊልሞች….. የተሰማውን የ”ፍቅር” ስሜት እያራገበ ከትምህርት፣ ከሥራ፣ ከማሕበራዊ ሕይወቱ፣ ከሚሄድበት የሕይወት መንገድ፣ ከሰቀለው ዐላማ፣ በልቡ አርግዞ ከወለደውም ርዕይ ስንቱ ተሰናከሎ ቀርቷል።

ልብ አድርግ ወንድሜ! እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር መጀመሪያ አዳምን እንደፈጠረው ታውቃለህ፤ ከእርሱም ሔዋንን፤ ከሁለቱ ደግሞ ቤተሰብን….። ስለዚህም ወንድ የቤተሰብ፣ የማሕበረሰብ፣ የሕብረተሰብ፣ የትውልድ ብሎም የሃገር መሠረት ነው። ለዚህም ሔዋንን ለመሥራት(ለመፍጠር) እግዚአብሄር ተመልሶ ወደ አፈር እንዳልሄደ ይልቁንም ቀድሞ ከፈጠረው እንዳበጃት አስተውል። ምንም እንኳ በዘልማድ የሕብረተሰባችን መሠረቱ ቤተሰብ ነው ብንልም ስነ-ፍጥረትን ስታይ ግን ከሥር የምታገኘው ወንድን ነው።

መሠረት ለአንድ ሕንፃ ምን ያክል ወሳኝ እንደኾነ አታጣውም። መሠረትን የተፈጥሮው ዐላማ ከአድናቂዎች እይታ ውጪ ከተሸከመውም ሕንፃ ሥር አውሎታል።መሐንዲሶች ትልቁን ጥበብ፣ ጥንቃቄ እና ጊዜ ወስደው መሠረትን ይጥላሉ። ምክንያቱ ደግሞ ጣሪያ ቢያፈስ፣ ግድግዳ ቢሰነጠቅ፣መስታወቶቹም ቢነቁ(ቢሰነጠቁ) ወጪ ቢኖረውም ይታደሳሉ። ነገር ግን መሠረት ቢሸሽ ከቦታውም ባይገኝ የእዛ ቤት ህልውና ያከትማል። እኛ ሰዎችም ባይናችን ያየነውን የተጌጠውን ሕንፃ እናድንቅ እንጂ የተሸከመውን መሠረት ላፍታም አናስበውም።

ወንድሜ! አንተ የቤተሰብህ፣ የማሕበረሰብህ፣ የሕብረተሰብህ፣ የትውልድም ኾነ የሃገር መሠረት ነህ፤ እንዲህ ተፈጥረሃልና። ዐለም በድምጽ ብልጫ የምትሸልምህ ወይም የምትወስድብህ ሳይኾን የተሠራህበት ግሩም ጥበብ ነው። ሰዎች ቤትህን አይተው የተዋበውን ሕንፃ ሲያመሰግኑ መሠረቱን እንደረሱት አንተም ላትታወስ ትችላለህ። ነገር ግን የቤትህ(የትዳርህ) ሸክም(ከውጭ ጀምረህ በእልፍኝህ አድርገህ እስከ መኝታህ አልጋ ላይ ባለው ግዳጅ ሁሉ) ሙሉ ለሙሉ አንተ ላይ መኾኑን አትርሳ።

ስለዚህም ኃላፊነትህን ለመሸከም ትውልድን ከዘመን ዘመን ለማሻገር መጠንከር በእውቀት እና በእውነት ላይም ልትመሠረት ይገባሃል። ይህን በማድረግህም ዓለም የሙገሳን ዜማ እና ግጥም ትሰጠኛለች ብለህ ተስፋ አታድርግ። ምክንያቱ ደግሞ ሕንፃ በሠረት መቆሙን አንድም ቀን አስባ፣ መሠረትን ዘክራ አታውቅምና። አንተ ግን ከቦታህ ስትንሸራተት፣ ከኃላፊነትህ ስትሸሽ ትዳር፣ ቤተሰብ፣ ማሕበረሰብ፣ ሕብረሰብ፣ ትውልድ ብሎም ሀገር ይናጋሉ። የአንድ ሀገር ሉዓላዊ ጥንካሬ፣የትውልድም ልቀት(excellence)፣ የሕብረተሰብ የመተሳሰብ እና የመተሳሰር ሠንሠለት፣ የማሕበረሰብም አንድነት፣ የቅጠኛ ቤተሰብም ግኝት፣ የትዳርም ስኬት የወንዶቹን በእውነት እና በእውቀት የመመሥረት፣ ዐላማቸውን የማወቅ፣ ርዕያቸውን የመኖር ሐቅ ይመሠክራል።….ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *