ወንድነትህ ሲነቀፍ አብረህ አታጨብጭብ ክፍል ፪ (ጅብን ሲወጉ በአህያ ይጠጉ….)

ሳተናው!

ዐለም ወንድነትህ ላይ የቃጣችውን ዘመቻ ባለፈው ሳምንት ፍጹም የወንድ ልጅ ጥላቻ ካላቸው እና እርሱንም ፊት ለፊት ከሚገልጹት ጀምረናል። ዛሬ ደግሞ ለሴቶች ተቆርቋሪ መስለው ወንዶችን በሕቡዕ(በድብቅ) እንዴት እንደሚሰልቡ እናያለን። 

፪ኛ በሴተችና በሕጻናት ተጠግተው (እነርሱን የሚጠቅሙ) መስለው ወንድን የሚያጠቁ

እነዚህ እንደቀደሙት ዓላማቸውን (ለወንድ ያላቸውን ጥላቻ) ፊት ለፊት አይገልጹትም። ብዙ መልካምና ጠቃሚ የሚመስሉ ትርክቶችን፣”ጥናቶችን” እና ተልዕኮዎችን ይዘው ስለሚነሱ ድብቅ ዓላማቸውን ለመረዳት ይከብዳል።ኹለ ነገራቸውም በሸፍጥ የተሞላ ነው። ከዚህም የተነሳ ከቀደሙት ይልቅ በተሻለ ወንዶችን ማሸማቀቁም ኾነ መስለቡ ይሳካላቸዋል።

እነዚህ በእባብ የሚመሰሉ ሰዎች/ተቋማት በጣም የተለሳለሱ አዛኝና አሳቢም መሳይ ናቸው። ስለሴቶች “ጥቃት” ሲያወሩና ሲያብራሩም ወደር የላቸውም።  

ስለሴቶች መብት ስለነጻነትም ቆመናል ይሏችኋል። በጄ ብላችሁ ስትሰሟቸው ወንድ ልጅ በሚስቱ ላይ ምንም ዓይነት ስልጣን እንደሌለውና እርሷም የእርሱ እኩያ ስለኾነችም የፈለገችውን ማድረግ መብቷ እንደኾነ ይነግሯቹኋል።

ትዳሩም መሪ እና ተመሪ የሌለበት፣ አዛዥና ታዛዥ የማይሰማበት፣ ልዕልና እና ትሕትና የማይታይበት፣ ራስ የተለየው ሰውነት ይኾናል። ይኼም ደግሞ ስልጣኔ ዘመናዊ አኗኗርም እንደኾነ ይተረካል።

በቤታችን ያለው እውነታ

ሳተናው!
እውነቱ ከዚህ የራቀ ነው። በባልና በሚስት “እኩልነት” ላይ የተመሠረተ ትዳር ተፈጥሮኣዊ ወንድነቱን ባልተቀበለ፣ በካደ፣ በተሰለበ፣ በማይለማመደውም ወንድና ከሴትነት ይልቅ ወንዳወንድት ባየለባት ሴት መካከል የሚፈጸም ነው።

ከዚኽም የተነሳ ሴቶች በባሎቻቸው ላይ አመጸኛ ይኾናሉ። አልያም አመጸኛ ላለመምሰልና ስልጡንም ለመባል ይበልጡንም ግን የባልን ውሳኔ ላለመቀበል ክስተቶችን ኹሉ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ይሞከራሉ። 

ይኽ ታዲያ እናቶቹን ለልጆቻቸው(ለትውልድ) ላለመታዘዝ አርኣያ ሲያደርጋቸው (አላሳይዋቸውምና) ወንዶቹን ደግሞ ተፈጥሮኣዊ ወንድነታቸውን ይሰልባቸዋል። ይኽም እንዴት ነው ቢሉ፦

፩ኛ ወንዶቹ ትርክቱን የስልጣኔና የዘመናዊነት ውጤት አድርገው ይቀበሉና ተፈጥሮኣዊ ወንድነታቸውን ከማጎልበትና ከማበልጸግ ይልቅ ያፍኑታል፣ ያኮስሱታል፣ ያፍሩበታልም፤ ከዚኽም የተነሳ የወንዳወንድነት ወኔያቸውን ያጣሉ።(ወንዳወንድነቱን መስለብ)

፪ኛው ደግሞ ትርክቱን ባያምኑበትም እንኳ “በዚህ ዘመን ሌላ ምን ምርጫ አለን?” ብለው(እንዳለ አያውቁምና) ትዳራቸውንና ልጆቻቸውን ላለማጣት ሚስቶቻቸውን የሚመሩበት ቤታቸውንም ቅጥ የሚያሲዙበትን ወኔ ይጥላሉ።

እንዲህ ዓይነቱ ሰይጣናዊ ዘመቻ በትውልዱ ላይ የሚያዘምቱት ግለሰቦችም ኾነ ተቋማት የሚጠቀሙበት ትልቁ ሽፋን “ሴቶችን ማገዝ፣ ሴቶችን ማብቃት እና ሴቶችን ከጥቃት መከላከል” …. የሚባሉ እና የመሳሰሉትም ናቸው። 

ማስመሰያ ፩ “ሴቷን ማገዝ”፣ “ሴቷን ማብቃት”

ሴቷ የተፈጠረችለትን ዓላማ አስቶ፦ ትምሕርቷን እና ሥራዋን ዓላማዋ ያደርጉታል። ይኽም ከቤት ውስጥ ኃላፊነት ወደ ውጭ፣ ለምትወደው ባሏ  ከመታዘዝ ለሥራ አለቃዋ፣ ለባሏ ከመገዛት ለቀጣሪዋ አደረጋት እንጂ “አበቃት” የሚያሰኝ ነገር የለውም። በዚኽም ባሏ(የሥራገበታ አለቃዋን ሽራፊ እንኳ) በእርሷ ላይ ምንም ዓይነት ስልጣን እንዳይኖረው ኾኗል፤ የሚፈልጉትም እርሱኑ ነው።(ወንዱ በቤቱ ያለውን ስልጣን መግፈፍ)

እነዚህ አካላት(ግለሰቦችም ኾኑ ተቋማት) ሴቷን የማገዝ፣ የማብቃት እና ከጥቃትም የመታደግ ሐቀኛ ዓላማ ቢኖራቸው ኖሮ ተፈጥሮዋን ባማከለ፣ በጠበቀ እና በተስማማ መልኩ በደገፏት ነበር። የሚመክሯት ግን ተፈጥሮኣዊ ጸጋዋን እንኳ የሚያሳጣትን እንድታደርግ ነው።

አስረጅ፦
እንጨትና ብረት ተፈጥሮኣቸው ለየቅል ቢኾንም በቢላዋ፣ በመዶሻ፣ በመጥረቢያ እና በመሳሰሉት መሣሪያዎች ላይ አንድነትን መሥርተው ይገኛሉ። እነዚህን የመገልገያ መሣሪያዎች ጥራታቸውን መጠበቅ፣ ብቃታቸውንም ማሳደግ ቢፈለግ እንጨቱን ብቻ አልያም ብረቱን ብቻ መሥራት በቂ አይኾንም። 

ይኹንና ሁለቱንም የማደስ ሥራ ቢሠራም አፈጻጸሙ ግን ለየቅል ነው። ብረቱን የሚያሰለጥኑት እሳትና መዶሻ ሲኾኑ እነርሱ ግን ለእንጨት መጥፊያው ናቸውና ብረቱን በእሳት እንጨቱን ግን በመላጊያ ይሠሩታል። ሴትና ወንድም ባላቸው የተፈጥሮ ልዩነት አንዱ ተፈጥሮውን በሚያጎለብትበት ሥራ ሌላው ቢገኝ የእርሱ ተፈጥሮ ይኮስሳል፤ በዚኽም ለአንድ ዓላማ ሚናቸው ግን ለየቅል እንደኾነ ልብ ይሏል።

ሴትን ማብቃት ማለት ወንድ በሚሰለጥንበት፣ በሚሠማራበት እና በሚገኝበት ቦታ ማስቀመጥ ማለት አይደለም። ወንድ የሠራውን መሥራት፣ ወንድ የጨጠውን መጨበጥ፣ ወንድ የረገጠውን መርገጥ፣ ወንድ የደረሰበት መድረስ ሴቶች ከወንድ “እኩል” መኾናቸውን ሳይኾን ሴቶች ወንድ ለመኾን መንገድ መጀመራቸውን የሚያሳይ ነው።

ማስመሰያ ፪ “ሴቶችን ከጥቃት ለመጠበቅ”

ወሬዎች(ዜናዎች) “ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት አመንጪውም ፈጻሚውም ወንዱ ነው” በሚመስል መልዕክት ከሴቶች ጋር የሚኖረው ግንኙነት “ጥንቃቄ”/ፍራቻ የተሞላው አልያ ግን በተለያዩ የክስ ስሞች ሊያስጠይቀው እንደሚችል ይነገረዋል። ከዚኽም የተነሳ ወንዱን ፈሪ፣ አልጫ ሲያደርገው ፤ ለምግባሩ የራሱ አቋምና መለኪያ ያለው ሳይኾን ከሴቶች ይኹንታንና ጭብጨባን የሚሻ አድርጎታል። 

በተጨማሪም በየዘፈኑና ፊልሙ ካለ አንቺ መኖር አልችልም፤ የምኖረው ላንቺ ነው፤ እታዘዝሻለሁ፤ ማለት በተለመደበት በዚህ ዘመን ወንዱን ሴቷ እግር ስር እንዲደፋ “ማፍቀሩ” ብቻ ያበቃዋል። 

** መራሩ እውነት ታዲያ ያለው እዚህ ጋር ነው። በየትኛውም ምክንያት ቢኾን ሴት ልጅ ክብሩን ጥሎ እግሯ ሥር ለወደቀ ወንድ የሚኾን ክብር ማጣቷ ነው፤ ልቧም ከእርሱ መራቁ ነው።**

ለጥፋቱ ይቅርታውን ትቀበል፣ መውደዷም ይኖር ይኾናል ፤ ነገር ግን ከዚህ በኋላ የእርሷና የእርሱ የአንድነት ኑሮ አፍኣዊ፣ ቁሳዊ ብቻ ይኾናል እንጂ። ከእርሱ ጋር የመተኛት(ለተራክቦ) ፍላጎት ግን አይኖራትም።

ስለዚህም የሁለቱ ማለትም ከላይ የጠቀስናቸው ዓይነት(ወንዳወንድ የኾነችው ሴትና ስነልቦናው የተሰለበው ወንድ) ትዳር ደግሞ ተፈጥሮኣዊ የፍቅር ስሕበት የማይታይበት፣ ወሲብ የራቀው ከዚኽም የተነሳ አንድነታቸው የላላ ይኾናል። ሴቷን በ”ማገዝ”፣ በ”ማብቃት” እና ከ”ጥቃት መጠበቅ” በሚሉ ማስመሰያዎች ወንዱ ላይ የሚቃጣው ዘመቻ በጣም ረቂቅ፣ ሰፊ፣ ጠላትንም ውጤታማ እያደረገው ነው።

፫ኛ በየዋህነት የሚነዱ…..ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *