ወንድነትህ ሲነቀፍ አብረህ አታጨብጭብ ፫ (በሬ ሆይ ሳሩን አይተህ ገደሉን ሳታይ)

ሳተናው!

ያለፉት ሁለት ሳምንታት አውቀውና ኾንም ብለው ወንድን በቁሙ እንዲሁም ባሕርይውና ጠባዩ፣ ስልጣንና ስርዓቱ ላይ ግልጽ የኾነ ጥቃት የሚፈጽሙትንና ይኸው ዓላማ ኖሯቸው ነገር ግን በሕቡዕ(በድብቅ) የሚንቀሳቀሱትን በቅደም ተከተል አይተናል።

ዛሬ ደግሞ የምናያቸው ከላይ የጠቀስናቸው አካላትም ኾነ ግለሰቦች ዓላማ ያልገባቸው፣  እነርሱም ከእንደዚህ ዓይነቱ ዓላማ የራቁ ናቸው።

ይኹን እንጂ በተለይ የመሠሪዎቹን(የኹለተኞቹን) “ለሴቶችና ለሕጻናት የቆመ” ልፈፋ ተከትለው ራሳቸውንም ኾነ ትውልድን አደጋ ላይ የሚጥሉ የሚጎዱትም ይኾናሉ።

አደጋውም በተለይ ወንዱን በስነልቦና መስለብ፦ ሰነፍ፣ ፈሪ፣ ምስኪን፣ ሱሰኛ ማድረግና ለቀደሙት ኹለቱ መገበር ነው።

“ትውልዱ (ወንዱ) የእነዚህ ጉዳት ለምን ይሸውደዋል?” ብትሉ እነዚህ አካላት የወንዱ የቅርብ ሰዎች ናቸውና ነው(ወላጆች፣ መምሕራን፣ ጓደኞች፣ የኃይማኖት አባቶች… የመሳሰሉት)።

በተጨማሪም የወንዶቹን ወንዳወንድነት ሲቃወሙ በተለይም ክፉ ድርጊቶችን ምክንያት አድርገው ሲኾን በወንዶች ራሱ ተቀባይነት ይኖራቸዋል።

አስረጅ ፩ ወላጆች

ወላጆች ወንዶች ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ “በእኩልነት” በታሸ እሳቤያቸው ወንዱ ልጅ “ጨዋ፣ አርፎ የሚቀመጥ፣ የማይጣላ(የማይደባደብ) እንዲኾን ይፈልጋሉ።

ብዙውን ጊዜ ደፋር፣ ጉልበተኛ፣ እልኸኛ፣ ዐዲስ ነገር የሚሞክርን ልጅ በቅርብ እርቀት ከመጠበቅ ይልቅ ከአደጋ ነጻ፣ ከጥል ነጻ፣ ከሽንፈት ነጻ(ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሁሉም አሸናፊ ነው የሚል የሰነፎች ፉከራ አልበዛባችሁም)፣ ከሐዘንም ነጻ የኾነ ከባቢ ይፈልጉላቸዋል።

ልጆቻችን በእኛ ሥር እያሉ ደስታውንም ሐዘኑንም፣ ሰላሙንም ጸቡንም፣ ድርድሩንም ድብድቡንም ማወቅ አለባቸው። አለበለዚያ ግን ከእኛ እርቀው መኖር ሲጀምሩ ሐዘኑን አይደለም የደስታውን ቅጥ እንኳ አያውቁትም፣ በጸብ ውስጥ አይደለም በሰላሙም መኖር ያቅታቸዋል፣ መደባደቡን ተዉት በአንድ ኃሳብ መስማማት ይሳናቸዋል።

እነዚህ ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ፣ ሲያስተምሩና ሲያሰለጥኑ ምስኪን አድርገው ያሳድጓቸዋል። ወንዶቹም ልጆች ምስኪንነት በዓለማዊው ስርዓት ደንበኛ፣ ግብረ ገብ እንደኾነ በመንፈሳዊውም ዓለምም ጽድቅን እንደሚያስገኝ እየተነገራቸው ያድጋሉ ይኼንንም ያምናሉ እውነታው ግን የዚህ ተቃራኒ ይኾናል።

አስረጅ ፪ መምሕራን

ከወላጆች ቀጥለው ትውልዱን(ወንዱን) በመስለብ ተስተካካይ የሌላቸው መምሕራን ናቸው። መምሕራን በሁለት ወገን ትውልዱን ይሰልባሉ፦

     ፪፥፩ እንደወላጆቹ ሁሉ በየዋህነት የኋላውን ጥፋት ባለማየትና ባለማወቅ ወንዶቹን እንደ ሴቶቹ እንዲቀመጡ፣ እንዲጫወቱ፣ እንዲያጠኑ ይወስናሉ ያስገድዷቸዋልም። ይኽም የወንዶቹ ተፈጥሮኣዊ አቅማቸው፣ ዝንባሌያቸው እና ስጦታቸው በሴቶቹ አንጻር እንዲቃኝና እንዲኮስስም ይኾናል።

    ፪፥፪ ኛው አኹን ላይ በከተማ በተለይም በግል ትምሕርት ቤቶች ላይ በሰፊው እያየነው የመጣው የመጀመሪያ ደረጃ ትምሕርት ቤት መምሕራን በአብዛኛዎቹ አንዳንዴም ኹሉም ሴቶች መኾናቸው ነው።

      ይኼስ እንደምን ትውልዱን ወንዱን ይጎዳል ቢሉ፦ ሴቶቹ መምሕራን ተማሪዎችን አወዳድረው አሸናፊዎችን ለይተው ሲያበቁ መልሰው ደግሞ “ኹላችሁም አሸናፊዎች ናችሁ” ይሏቸዋል። በእነርሱ ዘንድ ውድድር፣ ፉክክር፣ መጣጣል፣ አሸንፎም መውጣት ከሌላው ተለይቶ ከፍም ማለት “ተሸናፊዎችን የሚበድል፣ የሚያሳዝንም፣ ሲኾን ጤናማም ያልኾነ” ነው

     ምሳሌ፦ አንድ ጊዜ ከልጆቼ ጋር ኾኜ ለልጆች በተዘጋጀ ትርዒት ላይ ልንታደም ኼድን። በትርዒቱ መካከል ወላጆች የሚወዳደሩበት ሰዓት ደረሰና ልጆቼ መድረክ ላይ ካልወጣህ አሉኝ። እኔም ወጣሁ፤ ሌላም አንድ አባት ወጣ። ከእናቶችም ሁለት ወጡ። ውድድሩን ስንጨርስ በማያሻማ ኹኔታ አባቶች አሸነፍን መድረክ መሪዋም ይኽንኑ መስክራ ስታበቃ መልሳ ደግሞ “ሁለቱም አሸናፊዎች(አባቶችም እናቶችም) ናቸው” “ሁለቱም ይሸለማሉ” አለች።

     ይኽ መንገድ ሴቶችን ቢጠቅም(መጥቀሙን እጠራጠራለሁ) ወንዶችን ግን የመወዳደር፣ የማሸነፍ ወኔያቸውን ይሰልባል። ወንዶች የማደግ፣ የመለወጥ፣ ኃላፊነት የመውሰድ እና ሌሎችም ተፈጥሮኣዊ ጸጋቸውን በፉክክር ያበለጽጋሉ። ነገር ግን የተሳታፊዎችን ሞራል ለመጠበቅ ተብሎ ኹለም ሰው “አሸናፊ”፣ ኹሉም ሰው “ጎበዝ”፣ ኹሉም ሰው “ስኬታማ” ሲባል ወንዳወንድ ወኔያቸውን አውቀውትም ይኹን ሳያውቁት ይሰልባቸዋል።

ይህ በእንዲህ እያለ ታዲያ በሰውነት ውስጥ ካለው ተፈጥሮኣዊ ከኾነው ንጥረ ነገር(hormone) የተነሳ ወንዶች ልጆቻችን ኃይለኛ፣ ደፋር፣ ጉልበተኛ ቢኾኑ ሊሸማቀቁበት አይገባም። 

ይልቁንስ ይኼን ኃይለኝነታውን፣ ድፍረታቸውን፣ ጉልበታቸውን የት፣ መቼ፣ ማን ላይ እና እንዴት መጠቀም እንደሚገባቸው ማስተማርና አርኣያ የሚኾናቸውም አባት እንዳያጡ ማድረግ ነው።

አለበለዚያ ግን ዛሬ ኃይለኝነቱን፣ ድፍረቱን እና ጉልበተኝነቱን ካንቋሸሽንባቸው ነገ ስንፈልግባቸው የማናገኝባቸው አልጫዎች መኾናቸው አይቀሬ ነው። እንዴት ቢሉ እኛ ወላጆቻችው ጸጋቸውን “አርክሰንባቸዋልና” እነርሱ ራሳቸው እየናቁት፣ እየተጠየፉት፣ እየራቁትም ይኼዳሉ። 

የዚኽ ውጤት ምን እንደሚኾን ታውቃላችሁ? ኾዱ ከሞላ፣ ፍላጎቱ ከተሳካ ስለሀገር፣ ስለወገን፣ ስለትውልድ፣ ስለኃይማኖት፣ ስለትዳሩ(ስለሚስቱ) የማይገደው ስሜታዊ፣ አልጫ፣ ምስኪን ወንድ ነው።

ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *