ወንዶች ልጆቻችንን ስለመታደግ

ሳተናው!

(ይኽ ጽሑፍ እንደተለመደው የሕክምና ባለሙያዎችንም ኾነ የኃይማኖት አባቶችን ምክር የሚተካ ሳይኾን የራሴን በተግባር የተፈተነ ልምድ ላካፍልህ ፈልጌ የተጻፈ ነው።)

ወንዶቻችንን የማሳደጉን ነገር ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ ጽፌበታለሁ። ይኹን እንጂ ልጅ ማሳደጉ የአንድ ሰሞን ሥራ አይደለም። በተጨማሪም በዙሪያዬ ያሉ ወዳጆቼ ወንዶች ልጆቻቸውን እንደ ሴቶቹ አድርገው ሲያሳድጉ አያለሁና ይኽ ቢቃና ብዬ ከሌሎችም ኾነ ከራሴ የተማርኩትን፣ የሞከርኩትንም እያዳበርኩ እከልሰዋለሁ።

ልጆቻችንን ምንም እንኳ ያለማበላለጥ በእኩል ዓይን እያየን ብናሳድጋቸውም አጽንዖት ሰጥተን ልናስተውለው የሚገባን ጉዳይ ቢኖር ግን ወንዱ እና ሴቷ ልጆቻችን ፍጹም አንድ እንዳልኾኑ ነው።

ይኼስ ምን ማለት ነው? ወንዱ ልጅህን የምትመክርበት፣ የምታዝበት፣ የምትቆጣበት፣ የምትቀጣበት፣ የምትመግብበት፣ የምታጫውትበት መንገድ ከሴቷ ፍጹም የተለየ መኾን አለበት።

ወንዱ ልጅህ ሲያድግ ከአልጫነትና ምስኪንነት ርቆ ቆፍጠን ያለ አባወራ ይኾን ዘንድ፦

፩ኛ በከፍተኛ ሥነ-ስርዓት አሳድገው

ሳተናው! ልብ አድርግ በሥነ-ስርዓት አላልኩህም በከፍተኛ ሥነ-ስርዓት እንጂ። ይኽም ምን ማለት ነው፦ የጥናት፣ የንባብ፣ የጨዋታ፣ የአመጋገብ ሥርዓትን ሥራለት እንዲፈጽመውም ግድ በለው፣ ካልፈጸመውም ቅጣትህ ተግባራዊ ይኹን። (አንተ ራስህ ግን ምን ያክል የስርዓት ሰው መኾን እንደሚጠበቅብህ አስተውል)

ስርዓትህ “በፍቅር” ሰበብ የሚተጣጠፍ ከኾነ ግን ልጅህ “ቢወድህ” እንጂ አያከብርህም። ነገር ግን ጠንካራ ስርዓትን በቤትህ ገንብተህ፣ ያዝ ለቀቅ ሳታደርገው፣ አፈጻጸሙም ሳይዛነፍ ግድ ብትል ይኼንንም ከልብ በመነጨ ፍቅር ስትፈጽመው መልካም ዜጋ ሳተናም ትውልድ ታፈራለህ።

አልያ ግን ለስላሳ ነገር ግን ስሜታዊ፣ አንገት ደፊ ነገር ግን ሀገር አጥፊ፣ አፈ ቅቤ ነገር ግን ኾዱ ጩቤ የኾነ ትውልድ ታፈራለህ።

ሥነ-ስርዓት መቼ?(የራስ ተምክሮ)

? ከሁለት ዓመቱ ጀምረህ ማታ በተቀመጠበት፣ እንደታቀፍከውም ከሚተኛ ይልቅ የእንቅልፍ ሰዓቱ ሲደርስ ወደ መኝታው ሄዶ ወይም ወስደኸው እንዲተኛ አስተምረው።

? መኝታው ላይ ከወጣም በኋላ የሚያንጹትን ተረት በቃልህ ወይም በመጽሐፍ ንገረው።

? ጥረቶቹን ማድነቅ፣ ስሕተቶቹን ማረም፣ ጥፋቶቹን መቅጣት አትስነፍ።

? ላጠፋው ጥፋት ቀጪው አንተ እንጂ “አያ ጅቦ”፣ መምሕሩ፣ አልያም ሌላ ሰው አይኹን፤ መፍራት እና ማክበር ያለበት አንተን ይኹን።

? በአራት ዓመቱ ጠዋት አሥራ ሁለት ሰዓት መነሳት አስለምደው።

? ሙገሳዎቹ እና ቅጣቶቹንም ጨምርለት።

? ስድስትና ሰባት ዓመት ሲኾነው ከእናቱ ይልቅ ወደ አንተ አቅርበው፤ ወደፊት ሰው የሚያደርጉትን መራር እውነቶችና ፈተናዎች ደረጃ በደረጃ ካንተ ጎን ኾኖ መማር አለበት።
(ከዚህ እድሜው በኋላ ግን ከእናቱ ጋር ቢያሳልፍ ስሜታዊ፣ ምስኪን፣ ግንፍል፣ ሞገደኛ እና የመሳሰሉት የመኾን እድሉ ሰፊ ነው)

?በዚህ እድሜው ከወቀሳዎችህ ይልቅ ሙገሳዎችን አጽንዖት ስጥ፤ እነርሱም ላይ እንዲያተኩር አበረታታው።

፪ኛ ጊዜህን ስጠው

ሳተናው!
ለልጅህ ውዱ ስጦታ ውድ ትምሕርት ቤት፣ ብዙ አልባሳት፣ ውድ መጫወቻ… ሳይኾን አንተ ነህ። አንተ በስርዓትና በገደብ የታጠረ ነገር ግን ምርጥ ጊዜን አብረኸው አሳልፍ።

? በተለይም ሰባት ዓመት ከሞላው በኋላ ካንተ ጋር የሚያሳልፍበትን ጊዜ፣ ቦታ እና መንገድ አዘጋጅለት። ልጆችን የሚከለክሉ ካልኾኑ በስተቀር ቤተሰባዊና ማሕበራዊ ጉዳዮችህን ስትፈጽም በፀሐዩም፣ በዝናቡም፣ በጭቃዉም…. ካጠገብህ አታርቀው ሥራንም ስጠው ፈለግህን ይከተል ዘንድ።

? አንተ የምትሠራውን ነገር ይከተልህ ዘንድ ግድ በለው እንጂ ከእናቱ እቅፍ እንዲውል አትፍቀድለት።(እናቱን አያግዝ ሲዞርም ይዋል ማለት ግን አይደለም)

? ስለ ውሎው ዝርዝር ጠይቀው፣ ስማው፣ አስጨርሰውም ጥረቱን አበረታታ ስሕተቱንም አርምለት።

? አብረኸው የምታሳልፈው ጊዜ ከቴሌቪዥን፣ ከሞባይል፣ ነጻ የኾነ ቢቻል በጋራ የምትሠሩት የጉልበት ሥራ ቢኖር ጥሩ ነው።

፫ኛ የውጪ(የሜዳ) ላይ ጨዋታ

ሳተናው!
ወንድ ልጅህ ውጪ ከሌሎች ልጆች ጋር የመጫወቱ አስፈላጊነት የግድ ነው። “ትምሕርት ቤት ይጫወት የለ?” አትበል። ትምሕርት ቤት(በተለይ የግሎቹ) ለተማሪዎች የእውነተኛው ዓለም ማሳያ እና ማንጸሪያ አይኾኑም።

ትምሕርት ቤት ጨዋታዎቹ፣ ስርዓቶቹ፣ ጠቦቹ ምን አለፋህ ያሉት የተማሪዎች የእርስ በእርስ ግንኙነቶቹ ለሴት ተማሪዎች “ምቹ” እንዲኾን በሴቶች መምሕራን የተቀረጹ ናቸው። ይኽ ደግሞ ወንዶቹን ፈሪ፣ ሰነፍ ያደርጋቸዋል።

ስለዚህም በመኖሪያክ አካባቢ ከልጆች ጋር የሚውልበትን መንገድ አመቻችለት። ይውጣ፣ ይቆሽሽ፣ ይሩጥ፣ ይዝለል፣ ይውደቅ፣ ይጣላ፣ ይደባደብ። ከጓደኞቹ ጋር ለተፈጠረው አለመግባባት ኹሉ አትድረስለት። ችግሮቹን ይጋፈጥ፣ ይከራከር፣ ይጨቃጨቅ ማሳመንም ይማር። ከዚያ ባለፈ ግን ተደባድቦም ራሱን ያስከብር።

ይኽም በራስ መተማመኑን ሲጨምር፣ የማሕበራዊ ግንኙነት ክሕሎቱም ያድጋል። የራሱን(የጉልበት፣ የእውቀትና የስነልቦና) ጥንካሬ እና ድክመት ያውቃል፣ የጓደኞቹንም ይታዘባል።

ይህ እኔ ልጄን የማሳድግበት መንገድ ነው.. ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *