ወዳጄ ዓላማህን አትርሳ!!!

በአጠገብህ ያለውን ትልቅ ህንፃ ስታስብ ቦታቸውን ጠብቀው በመቆም እርሱን ያቆሙትን በቁጥር አንድ ተብለው ተጀምረው የትዬሌሌ የሆኑትን ጡቦች አስተውል።ትልቋን ሀገርንም ስታስብ የገነባትን እያንዳንዱን ቤተሰብ(ትዳር) አስተውል።ይህ ቤተሰብ(ትዳር)ተፈጥሮአዊ ቦታቸውን በያዙ የቤተሰብ አባላቶች(ባልና ሚስት) የተገነባ መሆኑን ልብበል።ህንፃውን የገነቡት ጡቦች በተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ አደጋ ከቦታቸው ሲዛነፉ ህንፃው መነቃነቅ መሠነጣጠቅ ብሎም መፈራረስ እንዲጀምር በትዳር ውስጥም ያሉት አባላት ቦታቸውን ሲስቱ ትዳር፣ ቤተሰብ፣ ማሕበረሰብ፣ ሕብረተሰብ፣ ሀገር መናጋት ይጀምራሉ። ስለዚህ ትልቅ ዓላማ አንግበህ ሳለ ለሆድህ እና ለወሲብ ተገዝተህ የአባወራነት ሚናህን አትሳት።
ብዙ ባሎች ከበሉ ከጠጡ በሚስታቸው ፍላጎት መሠረት ወሲብ ከፈጸሙ ወይም ካገኙ በምንቸገረኝ ወይም ከአቅሜ በላይ ነው በሚል ምክንያት የቤቱን አባወራነት ለሚስት ትተው ግብረገብ እና ስነ-ሥርዓት አስተማሪ ከመሆን ይልቅ “እርሱ ምስኪን ነው”እየተባሉ መኖርን ይመርጣሉ(ወደው ባይሆንም) ኋላ ላይ ታዲያ በቃላት ለመግለጽ የሚከብዱ ፈተናዎች ይገጥማቸዋል የማይቀለበስ የሕይወትም ዋጋም ያስከፍላቸዋል።
እነዚህ ወንዶች አደራ በሎች(የፈጣሪን)፣ ለሆዳቸው ያደሩ፣ ዓላማቸውን የዘነጉ፣ወይንም ወኔ ቢስ ፈሪዎች፣ አደራን ከሙሉ ስልጣን ጋር ከሰጣቸው ፈጣሪ ይልቅ በፍቅር ካባ “ተሸንፌያለሁ” ለሚሏት ሴት የተንበረከኩ፣ ውስጣቸው እውነቱን ቢነግራቸውም እነርሱ ግን በአፍአ(በውጭ) ላለው ውሸት የተገዙ ናቸው። እንዲሁም በሚጠፋ እህል፣ በሚከስም መልክ፣ በሚሻር ዓለማዊ ስልጣን፣ በይስሙላ ትዳር፣ በማያሳርፍ የወሲብ ፍላጎት ተማርከው ከተፈጠሩለትን የዓላማ መንገድ የሳቱ የእውር ድንብር ህይወት የሚገፉ ናቸው። በኋላ ዘመናቸውም በሚስቶቻቸው በሚደርስባቸው ልብን ዝቅ የሚያደርግ ጭቅጭቅ፣ ደምን ከፍ በሚያደርግ ንዴት፣ሰውነትን ለሁለት በሚሰነጥቅ ክህደት፣ ወኔን በሚሰልብ ንቀት፣……ከቆዩ በሽተኛ አልያ ግን አህያ እንኳን የማትችለውን የክስ ፋይል ተጭነው ለፍቺ ይዳረጋሉ። አንተ ግን ፈጣሪህ የጣለብህን ዓላማ አትረሳ ለዓላማው ማሳኪያም የሰጠህን የወንድነት ስጦታ አትጣል አለማወቅ ትልቅ በሽታ ነውና እነዚህን ሁለቱን በሚገባ እወቅ። እኒህን አስረግጠህ ስትረዳ አባወራነትህን አትሸቅጥም እርሱን ሸቅጠህ የምታተርፋት ሴትም ለቁጭት፣ ለጸጸጥ እንጂ አንተ እንዳሰብከው ለሕይወት አትሆንህም።ዔሳው የተፈጠረበትን ዓላማ ዘንግቶ የተሰጠውን ስጦታ ለጊዜያዊ ጥቅም ጥሎ ዘመኑ እንዴት እንደባከነ አስብ።
በተጨማሪም፦
ሁልጊዜም እንደምነግርህ አንተ አባወራ ነህ ግዴታህን፣ ሚናህን አበጥረህ እወቅ። ዓለም ደርሼበታለሁ የምትለውን ወንድነትህን የሚገፍ ማንነት፣ሁን የምትልህን “ለማዳ አንበሳ”፣ በጭራሽ አትሁንላት በጭራሽ እልሃለሁ፤ምንም እንኳ ሚስትህ(ለጊዜው) ቢቆረቁራትም። እርሷ(ሚስትህ) በዓለም ቅጥ ያጣ የእኩልነት ስብከት ተወስዳ የአንተን አባወራነት በግልጽ አልቀበልም ብትልም መልሳ ደግሞ (በዚሁ መርዘኛ እኩልነት) አንተ ውስጥ ያጣችውን ወንድነት በህቡዕ(በድብቅ) ታማርራለች። ታዲያ ከሁለቱ ችግሮቿ ለየትኛው መፍትሄ ታገኛለች? ለጊዜውም ቢሆን ለመጀመሪያው፤ምክንያቱም ብሶቷን በግልጽ ታቀርባለችና። ቢሆንም ግን መፍትሄው ብዙውን ጊዜ ወንድነትህን የሚሰልብ ይሆንና ሁለተኛው ችግር ላይ ይደረባል እርሱ(ሁለተኛው ችግር) ደግሞ ከቀድሞው በተቃራኒው (በግልጽ አይነገርምና) መፍትሄ ሳያገኝ ከዕለት ዕለት እየተባባሰ ይሄዳል። ወደድክም ጠላክም ታዲያ መጨረሻው ምንም ይሁን ምን እርሷ አንተን ከመውቀስም፣ ከመክሰስም፣ተጠያቂም ከማድረግ ወደኋላ እንደማትል ነው።
ስለዚህ ለሆድህ አድልተህ፣ ባለትዳር ለመባል ከጅለህ፣ ልጅ ለመውለድ ጓግተህ፣ ለገንዘብና ብዕል(ሀብት) ሳስተህ፣ በማያሳርፍህ ወሲብም ተደልለህ፣ ለሚጠወልግ መልክም ጎምዥተህ፣ በአጉል “ፍቅር” (ስሜት) ተወስደህ፣ በዘመናዊነት ድንቁርና፣ በስልጣኔ ኋላቀርነት ተተብትበህ ……. አባወራነትህን አትሸቅጠው(ለድርድር አታቅርበው)።ጀግን እልሃለሁ…..ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *