ዕጩ አባወራ

ልጄ፣ወንድሜ፣ወዳጄ እስከዛሬ አጉል ምስኪንነትህን (ምስኪንነት እኛ ባነሳነው አገባብ) እንድትተው ፤ ራስህን፣ ቤትህን፣ ሚስትህንና ልጆችህን ማስተዳደር የምትችል አባወራ እንድትሆን ስንጨዋወት ቆይተናል። ዛሬ ደግሞ በተለይም ላንተ ላላገባኸው እንዴት አድርገህ አባወራነትህን የምትመጥን እጮኛ መምረጥ እንዳለብህ አወጋሃለሁ።
መግባቢያ
ሁልጊዜም እንደምናደርገው ሁሉ በእጮኝነት ምርጫህም ቢሆን የዓለምን ተራ እና ተርታ የእኩልነት ጩኸት እንዳትስማ እመክርሃለሁ። ይልቅስ ተፈጥሮህን፣ ፈጣሪህ ባንተ ላይ ያለውን ዓላማ፣ ለዚህም ዓላማ ማስፈጸሚያ የሰጠህን አካላዊም ሆነ አእምርአዊ ጸጋ አስተውል፤ ልብም በል። ተፈጥሮአዊ ከሆነ እውነት በሚነሳ አመክንዮ እንጂ በስሜት እና በጭብጨባ ብዛት ለውሳኔ አትነዳ። ዓለም ለጥፋቷ አንድን ጽንሰ ኃሳብ ተፈጥሮአዊ እውነትነቱን መርምራ ሳይሆን ጭብጨባ (ብዙ ድምጽ) ያገኘውን ውሸት (ኢተፈጥሮአዊ ቢሆንም እንኳ) ከማጽደቅና ከመፈጸምም ሆነ ከማስፈጸም ወደኋላ አትልም።
ማስጠንቀቂያ!
ጽሑፌ ጠንከር ቢልብህ ሆድ አይባስህ። ፈጣሪህ በዓላማ ለዓላማ ኃላፊነት ሰጥቶ ፈጥሮሃልና፤ አባቶችህም የሀገርና የኃይማኖት አደራ ጥለውብሃልና ከፊትህም ረጅምና አድካሚ መንገድ ይጠብቅሃልና ትጠነክር ብዬ እንጂ ላሳዝንህ ፈልጌ አይደለም። የገንዘብ፣የቁስ፣ የወገን ደሃ (ድህነትህ በስንፍና ሳይሆን)፣ የአፍንጫ ጎራዳ፣ጎሳዬም አናሳ፣ ሰውነቴም ኮሳሳ አፌም ኮልታፋ እያልክ ተፈጥሮህን አታማር። በዚህ ውስጥም ፈጣሪህ አንተ ላይ ዓላማ አለውና አባወራነትህ አይዛነፍብህም፣ አይጓደልብህም።

በመጀመሪያ አንተ አባወራ ለመሆን እና ቤትህን በሥርዓትና ግብረገብ ለማስተዳደር አንተ ራስህ በእነዚህ ላይ የታነጽህ መሆን አለብህ(እስከ ዛሬ በተወያየነው መሠረት)። ሲቀጥል በሕይወትህ ላይ ከምትወስናቸው ውሳኔዎች ውስጥ በክብደቱም ሆነ ከውሳነው በኋላ በሚፈጥረው ተጽዕኖው አቻ የማይገኝለት የትዳር አጋር ምርጫህ እና ውሳኔህ ነው። አንተ ተፈጥሮህ ገብቶህ ራስህን አውቀህ መኖር ጀመርክ፤ የትዳር አጋርህ አንተ በግልህ ከምትፈልጋቸው የእርሷ ፀባዮች በቅድሚያ ዕጩ አባወራ በመሆንህ መስፈርት ልታደርጋቸው የሚገቡትን ለጥቂት ሳምንታት እናያለን።
1ኛ የአባቷ ልጅ ነች (አባቷ ገስጾ እና ቆንጥጦ ያሳደጋት ለማለት)?
2ኛ ቃልህን ታከብራለች ክብርህንስ ትጠብቃለች?
3ኛ ትታዘዝሃለች?
አንደኛ አባቷ ያሳደጋት ነች?
ይህች ልብህ የከጀላት፣ አይንህ የሚከተላት፣ ደምግባቷን የወደድክላት ልጅ ያሳደጋት ማነው? እውን አባቷ(አባት ባይኖር ወንድሟ) ነውን ወይስ እናቷ ብቻ ናት ያሳደገቻት? ወይስ አባቷ በእቤቱ ውስጥ ቢኖርም እኛ ምስኪንን በገለጥንበት መልኩ አንገቱን ሰብሮ የኖረ ፣የቤቱ አዛዥ ናዛዥ ሚስቱ(እናቷ) የሆነችበት ነው? ወይስ ከጭንቅላቱ ቀና ከደረቱ ነፋ ያለ ኩሩ ኮርቶ የሚያኮራ አባወራ ነው። ይህንን እንድታጣራ የምልበት በቂ ምክንያት አለኝ እርሱም እንደሚከተለው ነው፦ አየህ ለሴት ልጅ የነገ ስብዕና ዛሬ ላይ አባቷ እርሷን ያሳደገበት መንገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል። ፍቅር እና እንክብካቤ ከመስጠት ጀምሮ እርሱ ከዘረጋው ሥርዓትና መመሪያ ስትወጣ መምከር አልያም መገሰጽ አልመለስ ስትልም እስከ መቅጣት የሚደርሰው አስተዳደጉ ለእርሱ ልዩ እና ተወዳጅ ቦታ እንድትሰጠው ያደርጋታል።
ከሁሉ በላይ ደግሞ የወደፊት ሕይወቷን ከባል ጋር ስታስበው ጠባዩ ብቻ ሳይሆን ቁመናውና የሰራ አካላቱ ጭምር ያባቷን ቢመስልላት ትመኛለች። በቀደመ አስተዳደጉም አባቷ እርሷን ትዕዛዝ ተቀባይ፣ ቃሉን አክባሪ፣ በዚህ ምክንያት ለእርሱ ልዩ ቦታ እንዲኖራት አድርጎ አሳድጓታል። ታዲያማ እቅፉን የማትጠግበው፣ ጠረኑ የሚናፍቃት፣ ትንፋሹ የሚርባት፣ ደምጹን ስትሰማ ውስጧ ጮቤ የሚረግጥባት፣ እንኳን ከሳቁ ከቁጣው ፍቅር የሚይዛት(ቢሆንም ሆን ብላ አታናድደውም)፣ ጥንካሬው ብርታት የሚሆናት፣ ገዢ ቃሉ አስተዳዳሪ ስልጣኑ የሚያንበረክካት ፣ በቁልምጫ ሲጠራትማ ልቧክፍል፣ ትንፋሿ ስውር የሚልባት ……ብቻ ምን አለፋህ አባቷ ለእርሷ ከገለጥኩት በላይ ልዩ ነው። አባቷ ከለላዋ፣ ጥላዋ፣ መሸሸጊያዋ፣ ብርታቷ፣ መውደድን እያረሰረሰ የሰጣት የፍቅር ምንጯ፣ መሠናክሎችን የምትሻገርበት ድልድዯ፣ ፍርሃትን የምትረሳበት ጀግንነቷ ነው።
እንግዲህ ይህችን ሴት ማግኘት ምን ማለት ነው?…..የሳምንት ሰው ይበለን…… ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *