ዛሬ ዓለም “ትክክል” የምትልህ ስሕተቶች

ሳተናው!

ብዙውን ጊዜ ሚስቶቻችንን እንዴት ብንወዳቸውና ብንንከባከባቸው ከእነርሱ የምንጠብቀውን አክብሮት እንደምናገኝ ግራ እስኪገባን ድረስ ትዳራችን በፈተና ይናጣል።

እንዲኹም ያስከብሩናል ብለን ያሰብናቸውንና ትላንት ስናደርጋቸው የነበሩትን “መልካም” ነገሮች አብዝተን ስናደርግማ ከአክብሮቱ ይልቅ ንቀቱ እያየለ ይመጣል፤ ጽድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ እንዲሉ።

ዛሬ ታዲያ ከሚስትህ ከምትጠበቀው አክብሮት ፈንታ ንቀት የሚያስታቅፉህን የእርሷን ሳይኾን የራስህን የተሳሳተ አመለካከቶችና ድርጊቶች ልጠቁምህ።

እነዚኽን እኔ ከራሴ የትዳር ሕይወት የተማርኳቸው፣ ያስተካከልኳቸውና ለውጥም ያመጡልኝ ናቸው። እንዲኹም ደግሞ ሌሎችም የሕይወት ታሪካቸውን ካካፈሉኝ የቀሰምኳቸው ምናልባትም ዓለም የማትነግርህ እውነቶች ናቸው።

አንተ ጣፈጠህም መረረህም እኔ እነዚህን ሐቆች አስቀምጣለሁ። የሚጠቅምህን መምረጥ በመረጥከውም መንገድ መሄድ ያንተ ምርጫና ውሳኔ ቢኾንም ለምታገኘው ውጤት ግን ኃላፊነት መውሰድ(በሚስትህ አለማሳበብ) ይገባሃል።

ሲመክሩት እምቢ ብሎ ችግር ሲያገኘው ግን በሚስቱ የሚያላክክ መለወጥ የማይፈልግ ንክር ምስኪን ብቻ እንደኾነ አትርሳ!!!!

ሳተናው ንሳ! የወንድምህን ምክር!

ከዚኽ በታች የማቀብልህ ምክሮች ላለፉት ኹለት ዓመታት በተለያየ ጊዜ በተለያየ ርዕስ የዳሰስኳቸው ናቸው። አንዳቸውም ያልተነኩና ዐዲስ የኾኑ አይደሉም። እጥር ምጥን አድርጌ አንድ ቦታ ላይ ላስቀምጥልህ ብዬ እንጂ።

በምትኖርበት ማሕበረሰብ ውስጥ ተቀባይነት ያለውን የአባወራ ድርሻ ከሞላ ጎደል ትወጣለህ እንበል፤ ይኹን እንጂ በምትኩ ሚስትህ የምትንቅህና የማታከብርህ ከኾነ ከሚከተሉት ዝርዝሮች ውስጥ በአንዱ ሰልጥነህ አልያም በሁሉም ተክነህ እንደኾን ራስክን ፈትሽ፦

ዓለም ትክክል ነው ብላህ የምትፈጽማቸው ነገር ግን ከሚስትህ ንቀትን የሚያመጡብህ ነገሮች

፩ኛ ቤቱን፣ ትዳሩን፣ ልጆቹን እንድትመራ ስትተውላት
፪ኛ ለእርሷ እንደምትኖር ስትነግራት/ ስታደርገውም
፫ኛ ካለእርሷ መኖር እንደማትችል ስታውቅ

፬ኛ ካንተ እርሷን ስታስቀድማት
፭ኛ ብዙውን ጊዜ እሺ ስትላት
፮ኛ ለወሲብ ስታስፈቅዳት
፯ኛ ጥፋቶቿን ኢ-ስነስርዓታዊም ኾነ ኢ-ስነምግባራዊ ድርጊቶቿን በፍቅር ስም ስታልፋት(ስትታገሳት)

፩ኛ ቤቱን፣ ትዳሩን፣ ልጆቹን እንድትመራ ስትተውላት

ወዳጄ ትዳር መኪና ቢኾን ሚስትህን በጭራሽ ሾፌር አታድርጋት!!!

ጀግናው ሚስትህ ምን ተማረች፣ ከበረች(በማዕረግ)፣ ቆነጀች፣ ተሾመች ብለህ ትዳርህን የምትመራበት ስልጣንህን አሳለፈህ አትስጣት። ፈጣሪ ማንነታችሁንና ምንነታችሁን ሲያውቅ የሰጣችሁንም ጸጋ ሲያጠይቅ አንተን መሪ/ራስ ቢያደረግ ከእርሱ አውቄያለሁ ብለህ ሚና አትለዋውጥ።

ከፈጣሪህ የተሰወረ ጥበብ፣ ከእርሱ የጎደለም ፍቅር አንተ ጋር የለም። ስለዚህም ዓለም የምትነግርህን የእኩልነት ወሬ አትስማ እርሱ በውሸት የተሞላ የትዳር፣ የቤተሰብ፣ የትውልድም ጠንቅ ነው።

አቅም የለህ እንደኾን ራስህን አብቃ፣ ጥበብ ጎድሎህ እንደኾን እውነተኛዋን ጥበብ ፈልግ። እነዚህንም ተራና ተርታ ቦታ በመዋል ሳይኾን ቁርጥ ውሳኔ፣ ጽናትና ዓላማ ካላቸው ሰዎች ጋር በመዋል ተማር ራስህንም ቅረጽ።

በተረፈ ግን ለአባወራነት የተሰጠህን ስልጣን ጸጋው ላልተሰጣት ሚስትህ ሰጥተህ ትዳርህን፣ ሀገርህን እና ትውልድን አታክስር። ከምንም በላይ ደግሞ ማዕረግህን አትጣል፣ ክብርህን አትጣ፣ ራስህንም አታስንቅ። እምቢ ካልክ ግን ንቀትን ትጋታለህ በሽታንም ትሸምታለህ ከዚያማ በቀቢጸ ተስፋ የመኖርህ ነገር ሳይታለም የተፈታ ነው።

፪ኛ ለእርሷ እንደምትኖር ስትነግራት/ ስታደርገውም

ሳተናው! የተፈጠርክበትን ዓላማ ብታውቅ “የምኖረው ላንቺ ነው” ባላልክ ነበር። አንተ ልታሳካው የሚገባ ጉዳይ ሲኖርክ እርሷ ደግሞ ልታግዝህ ተሰጥታሃለች። ይኼንንም እርሷ በአፏ ባትመሰክርልህም(ባታስተውለውም) ሰውነቷ ግን በዚህ መልክ የተቃኘ ለዚህም የተሰጠ ነው።

ስለኾነም ምንም እንኳ “ላንቺ ነው የምኖረው” እያልክ በዘፈን፣ በግጥም ስታሞካሻት በአፍኣ(ከፊት በሚታየው ገጿ) ደስ ቢላትም ይኼነው ብላ በቃላት በማታስቀምጠው ምክንያት ግን ላንተ ያላት አክብሮት ይቀንሳል። ትክክለኛው ምክንያት ታዲያ አንተ በአፍህ ያወጅከው፣ እርሷም በጆሮዋ የሰማችው ፈጣሪ በውስጧ ካስቀመጠላት ሚና ጋር ይጋጫልና ነው።

ይኸውም ውስጧ ዓላማ ያለው በዓላማውም የማይደራደር ወንድ ሲናፍቅ፤ ልታግዘውና የስኬቱም አካል ለመኾንም በመጓጓት ነው (ምንም እንኳ አፏ ሌላ ቢያወራም)። ይኹንና አንተ እርሷን ዓላማ ስታደርጋት ዓላማ የለሽ እንደኾንክ ደመነፍሷ(ቀልቧ) ይነግራታልና እርሷም በማታውቀው “ይኽ ነው” በማትለውም ምክንያት እያደር ትንቅሃለች።

አስቀድመህ ይበጀኛል ብለህ ከያስከው ወደ ርዕይህ ከሚወስድህ መንገድ ለእርሷ ስትል አትውጣ። መንገዱ የማይጠቅምህ አልፎ ተርፎም የሚጎዳህ መጨረሻውም መጥፊያህ ከኾነ እርሷ መጣችም ቀረችም ይጎዳሃልና ተለይ። ሴት ልጅ(ሚስትህም ብትኾን) የሕይወት ዓላማህ አይደለችምና እርሷን ማሳደድ ትተህ ርዕይህን ፈልግ እርሱንም ለመጨበጥ ለማሳካትም ትጋ ያንጊዜ ብቻ ታተርፋታለህ።

የቀሩት ለሳምንት ይቆዩን…

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *