የልዕልና ድንበርህን አስከብር

የልዕልናህን ምንጩን ስታውቅ ይኽ ልዕልናህ ሚስትህን፣ ልጆችህን፣ ቤተሰብህን፣ ማሕበረሰብን፣ ትውልድን ብሎም ሀገርን የምታንጽበት መኾኑን ትረዳለህ። ይኼን ያህል ኃላፊነት ደግሞ ስለእነዚህ ኹሉ የሕብረተሰብ አካላት እድገትና ስኬት ስትል የሚጠበቅብህና ልትወጣው የሚገባ፣ የምትወጣውም እንደኾነ በፍጹም ልብህ ያለጥርጥር ልታምን ይገባል።

በተፈጥሮአዊ እውቀት እና እውነት የገነባኸው ይኽ የልዕልና እምነትህ ታዲያ ታተርፍበት፣ ለትውልድም ኾነ ለሃገር ይበጅ ዘንድ ልትንከባከበው እና ልትጠብቀው ይገባል። አለበለዚያማ የልዕልና ድንበርህ አንድም በፍቅር፣ አንድም በዘመናዊነት፣ ባንተም በ”ትሩፋት” ስም የሚናድ ከኾነ በምንም ዓይነት መንገድ የተፈጠርክበትን ዓላማ ከዳር ማድረስ አትችልም።

የኃላፊነት የልዕልና ድንበርህን ማንም ሰው እንዲያፈርስ አትፍቀድለት። ሚስትህን ልጆችህን አልፈህ ተርፈህ ትውልድንና ሀገርን እንድታንጽበት በተሰጠህ የልዕልና ድንበር ከማንም ጋር እልሃለሁ ከማንም ጋር አትደራደር።

ይኽ ልዕልናህን ተጠቅመህ ባንተ ሥር ያሉትን የቤተሰብ አባላት መክረህ፣ ገስጸህ፣ ቀጥተህ በአንተ ፊት በስርዓት በፈጣሪያቸውም ፊት በፍርሃት መኖርን ልታስተምራቸው ይገባሃል። ይኽን ለማድረግ ደግሞ በመጀመሪያ አንተ ራስህን ፈትሽ። አንተ ራስህ ምን ያህል ግብረገብ፣ ቅጠኛ በስነስርዓትህም የተመሰገንክ፣ ልዕልናህንም የጠበቅክ ነህ? ምግባርህ ልከኛ አካሄድህም ደንበኛ ከኾነ እንግዲህ በእውቀት ጀምረህ በእምነት አጠንክረህ በተግባር የተለማመድኸውን እና የምትኖረውን ታስተምራቸዋለህ።

ስታስተምራቸውም ሚስትህን በትዳርህ ገና ከጥንስሱ ልጆችህንም ገና ከጅምሩ መኾን አለበት። ልዕልናህና ፍቅርህ በምንም ዓይነት መልኩ የማይጣረሱ ነገር ግን ትይዩ ኾነው የሚሄዱ ለትዳርህም ኾነ ለቤተሰብህ ሕልውና አስፈላጊ ግብዓት ናቸው።

ብዙውን ጊዜ የልዕልና ድንበራችንን ከሚንዱት ነገሮች ከብዙዎቹ መካከል በፍቅር፣ በቀልድ፣ በጨዋታ፣ በዋዛ ፈዛዛ፣ በኪነጥበብ ስም እየተመካኙ የሚሰነዘሩት ንግግሮች ናቸው። ወንድሜ ፍቅርና ልዕልና ትይዩ ኾነው ይኼዳሉ እንጂ አይጣረሱም ብዬሃለሁ። “ለእርሷ(ለሚስቴ) የማልኾነው የለም እያልክ ልታስከብር የተገባህን ድንበር በፍቅር ስም አታፍርሰው ወይም አታስፈርሰው። አለበለዚያ ግን መጀመሪያ ድንበሩን ያፈረስክላት ወይም ያፈረሰችው ይህች ሴት ልዕልናህን ከሚንቁት የመጀመሪያዋ ትኾናለች። ይህ ንቀቷም ለሌሎች በተለይም ለልጆችህ አርአያ ይኾናል። ከሚንቁህም የትኞቹም ሰዎች ታዲያ የእርሷን በአፋጣኝ መፍትሔ ካላመጣህለት ትዳርህን፣ ቤተሰብህን የማፍረስ እና የመበተን አሉታዊ ድርሻ ይናረዋል።

የልዕልና ድንበርክን ከሚያፈርሱት በቤትህም ንቀትን ከሚያተርፉት መካከል አንዱ ከልጆችህ ጋር የምታሳልፈው በሰዓት ያልተገደበ፣ በመርሃ-ግብር ያልተመራ፣ በስርዓት ያልቃኘ ጨዋታ ነው። ይህን ሴት አያቴ ሲተርቱ ምን ይላሉ መሰልህ “ከልጅ አትጫወት ያወጣሃል በእንጨት”። ይህ ማለት ልጆች ጨዋታቸውን መጫወታቸውን እንጂ አንተ በአባትነት ያለህን የልዕልና ድንበር አያውቁትምና ነው። ጨዋታህ በጊዜ የተወሰነ እና ስርዓትን የጠበቀ መኾኑን ልጆቹ ሳይኾኑ አንተ ልብ ልትል ይገባል።

ሌላኛው የልዕልና ድንበርክን ከሚንዱ ነገሮች አንዱ የመገናኛ ብዙሃኑን ተገን እያደረጉ የሚወጡት የኪነጥበብ ውጤቶች ናቸው። እነዚህ የ”ጥበብ” ውጤቶች ብዙውን ጊዜ ሕብረተሰቡን እያዝናናን ቁምነገር እናስጨብጣለን በሚል ተለጣፊ ስም ይተላለፋሉ። በዚህም ፈር ያጣ ቀልዳቸው አባወራው መቀለጃ፣ የልጆች መጫወቻ፣ አይደለም የእድሜ እኩያው ሚስቱ ትላንት የተወለዱት ልጆቹ ከእርሱ የተሻለ የሚያስቡ፣ የስሕተት፣ የመሃይምነት ተምሳሌ ተደርጎ ገጸ-ባሕሪው ይሳላል። እነዚህ እና እነዚህን የመሳሰሉ የኪነጥበብ ውጤቶች ምንም እንኳ “ተወዳጅ” ናቸው ተከታይም አላቸው ቢባል አንተ ግን ራስህንም ኾነ ቤተሰብህን ከእነዚህ አርቅ።
ምክንያቱም ያንተን እውቀትና እምነት የሚሸረሽሩ፣ ድንበርህን የሚያፈርሱ ኃላፊነትህን እንዳትወጣ የሚያደርጉ የዛሬን ጥቅም እና ርዕሰ-ጉዳይ እንጂ ነገን ያላሰቡ ናቸውና።

ሳምንት ብንኖር ….***ሚስቴ ልጆቼ አይሰሙኝም*** ስለማለት
አባቶቻችን ነገር በምሳሌ ጠጅ በብርሌ እንዲሉ እንመስለው እስቲ የአንድ ሃገር መራሔ መንግስት(ንጉስ፣ ፕሬዝዳንት፣ ጠቅላይ ሚንስቴር) ሲሾም ሀገር እንዲያስተዳድር ሰላም እንዲያሰፍን ነው። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ሰላም ይደፈርስና የተወሰኑ ክፍሎች ቢያምጹ ይህ መራሔ መንግስት ምን ያደርጋል? አንተስ?….. ይቆየን።

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *