የሚስትህንና የልጆችህን ደረጃ ከፍ ስለማድረግ

ሳተናው!

አንተ የቤትህ መሪ እንደመኾንህ መጠን ለሚስትህና ለልጆችህ ጥረትን፣ ትጋትንና ስኬትን ልታስተምራቸው ይገባል። ቤተሰቡ የሚተዳደርበትን ስርዓትም የምትቀርጸው አንተ ነህና የጥረታቸውን ፍሬ ኺደቱንም መገምገም፣ እውቅና መስጠትና ማረም ያንተ ሥራ ነው።

ይኽ እንዲሳካ ግን ከሁሉ አስቀድሞ  ኹለት መሠረታዊ ነገሮች ያስፈልጉኃል እነርሱም፦

1ኛ አንተ ብርቱ የሥራና የስነስርዓት ሰው መኾን ይጠበቅብሃል(አባወራ)

2ኛ ያንተን መሪነት አምና በእሺታ የምትከተልህ ሚስት(የአባቷ ልጅ) ታስፈልግሃለች

እነዚህ ሁለቱ ተሟልተዋል ብለን እንቀጥል

አንተ ደረጃህን ከፍ በማድረግህ የምታተርፈውና ለሌላውም የምትተርፍበት ዘርፍ ብዙ ነው። ይኽንንም በመጠኑም ቢኾን ዐይተነዋል ዛሬ ደግሞ እንዴት ሚስትህንንና ልጆችህን ደረጃቸውን ከፍ በማድረግ ራሳቸውን ማሳደግ የሚችሉበትን ነጥቦች እናያለን።

በአንተ እንዳደረግከው ኹሉ ራስህን በማሻሻሉ ኺደት በራስህ ላይ እንደጨከንክ ነገር ግን ደረጃ በደረጃ እንዳደግክ ሚስትህንና ልጆችህንም እንዲሁ አስለምድ። 

በዚህም መሠረት፦
1ኛ ከእነርሱ የምትጠብቀውን ውጤት ከፍ አድርግ
2ኛ ሙከራቸውን ከዚህም የተነሳ መውደቃቸውን፣ መሳሳታቸውን አበረታታ
3ኛ ጥረታቸውን እና የደረሱበትንም አድንቅ
4ኛ በጭራሽ ከንዝህላልነት ከሰበብም ብዛት ለኾነ ደካማ ውጤት እድል አትስጥ ገስጽም

ለልጆችህ
1ኛ ከእነርሱ የምትጠብቀውን ውጤት ከፍ አድርግ
በትምሕርት፣ በመንፈሳዊ ሕይወት፣ በስፖርት፣ በስነምግባር እና በሌሎችም ከልጆችህ የምትጠብቀውን ከፍ አድርግባቸው። ምንጊዜም የተሻለ ብቃት እንዲኖራቸው ከትላንት ዛሬ መሻሻላቸውን አረጋግጥ ዘወትር እድገታቸውን እንደምትፈልግም አሳውቃቸው ይኼንንም ጠብቅ።

ለምሳሌ ጠዋት የመነሳት ልምድ ከሌላቸው አኹን ከሚነሱበት ሰዓት አስራ አምስትና ሀያ ደቂቃ እየጨመርክ ዘወትርም ይኼንን እየጠበቅክ በስቅሳቸው። ዘወትር አስራሁለት ሰዓት እንዲነሱም ከኾነ ዓላማህ ዕለት ዕለት እየተከታተልክ ንቃታቸው የሚፈለገው ሰዓት ላይ እስኪደርስ ግድ በላቸው።

ይኼን ሲጠብቁትም ቻልነው ብለው እንዳይዘናጉ በጠዋት ከመንቃቱ በተጨማሪም ነቅተው የሚሠሩትን መጠነኛ ሥራ ስጣቸው(ጸሎት፣ ስፖርት፣ ጥናት…)

2ኛ  ሙከራቸውን ከዚህም የተነሳ መውደቃቸውን፣ መሳሳታቸውን አበረታታ
ልብ አድርግ! የምታበረታታቸው እሳሳታለሁ እወድቃለሁ ከማለት የተነሳ መሞከርን እንዳይፈሩ እንጂ ስሕተቱ በራሱ ተፈልጎ አይደለም። እንዲሁም ከራስ ስሕተት መማር እንዲችሉ ጭምር እንጂ።
ስለዚህም ልጆችህን ዘወትር መሥራት የሚፈልጉትን፣ የሚጠበቅባቸውን ሲሠሩ “እሳሳት ይኾን?” “እወድቅ ይኾን?” የሚለው ጥያቄ ከአእምሮኣቸው እስኪወጣ ድረስ መሳሳታቸውን ሳይፈሩ እንዲሞክሩ አበረታታቸው። ከዚህ ሞክረው ሲወድቁ እየተማሩ መኾኑን አስረግጠህ በመንገር ወደፊት ሊያሳኩት የፈለጉት ዓላማ ሕልም ብቻ ኾኖ እንዳይቀር ታግዛቸዋለህ።

3ኛ ጥረታቸውን እና የደረሱበትንም አድንቅ
እያንዳንዷን ጥረታቸውን የጥረታቸውንም ውጤት አድንቅላቸው። ይኼን ስታደርግ ለሌላ ለላቀ ደረጃ ብርታት ስንቅም ይኾናቸዋል። ውጤቱ ምንም ይኹን ምን ከልባቸው የሠሩት ከኾነ ለጥረታቸው ሊበረታቱ ይገባል። ምክንያቱም ይኼ ጥረታቸው ወደፊት ለሚጨብጡት ስኬት በር ከፋች ነውና።

4ኛ ለንዝህላልነት እድል አትስጥ 
በጭራሽ ለንዝህላልነትና ለስንፍናቸው ቦታ አትስጥ መምከር መገሰጽ መቅጣትም ይገባሃል። ልጆች በተዘረጋ የሕይወት ስርዓት ውስጥ ካላለፉ ንዝህላል መኾናቸው አይቀርም። ከዚህም የተነሳ በዚህ የሚመጣን ስንፍናን አጥብቀህ ተቃወም፤ እነርሱም እንዲጠየፉት አድርግ።

ለሚስትህ
1ኛ ከእርሷ የምትጠብቀውን ከፍ አድርግ 
በመንፈሳዊ ሕይወት፣ በቤት አያያዝ፣ በልጆች አስተዳደግ፣ በእንክብካቤ ከእርሷ የምትጠብቀውን ከፍ አድረግ። ሴት ልጅ በበኹሉ ነገር ከእርሷ የተሻለ፣ የድርጊት ፍጻሜውም የላቀ ወንድን ትሻለች(ጀግና ወንድን) ። ይኽ ምናልባት ብዙዎቻችን በ”መንፈሳዊነት” እና በ”ዘመናዊነት” ሽፋን ያልተረዳነው የሴቶች ጠባይ ነው።

ስለዚህም ራስህን በጥረት ከከፍታ ላይ ከሰቀልክ በኋላ ከእርሷ ይኽንኑ ጠብቅ። 

2ኛ ሙከራዋን እና ጥረቷን ከዚህ የተነሳም ስህተትን(ውድቀትን) አበረታታ

ይኽ አንተ ፍጹም አለመኾንክን እና እርሷም እንዲሁ እንደኾነች የሚረዳ ባል እንደኾንክ ሲገልጥ በተጨማሪም ለመሻሻል እድል የምትሰጣት ጥረቷን አሞጋሽ እንደኾንክ ትረዳበታለች።

ካለመታዘዝ የተነሳ አለመሞከሯን እንጂ ታዛህ የተሳሳተችውን አትንቀፍባት። ይኹን እንጂ ከውድቀቷ የምትነሳበትን ስህተቷንም የምታርምበትን ጊዜም ኾነ ኃሳብ ስጣት። 

3ኛ በጥረቷ የደረሰችበትን አድንቅ

በጥረቷ የደረሰችበትን አድንቅላት። ቃልህን ማክበሯን፣ መታዘዟን አድንቅላት በዚህም በልከኛው ሕግ በቅጠኛው ስርዓትህም እንዳለች ታውቅ ዘንድ። ለልጆቿም የጥረት፣ የታዛዥነትም ቀዳሚ በመኾን ምሳሌ ትኾናቸዋለችና።

4ኛ ለንዝህላልነቷ ቦታ አትስጥ
ሚስትህ ከንዝህላልነትም ኾነ ከንቀት የተነሳ የምትሠራውን የስንፍና ሥራም ኾነ የሚያስከትለውን አላስፈላጊ ውጤት በጭራሽ አትቀበል አትታገስም። አለመቀበልህ እርሷን ቢያስከፋትም እንኳ ትዳርህን የኋሊት ቢያንሸራትት እንጂ አንድም ዐይነት ጠቃሚ ፋይዳ ለሌለው ሥራ እውቅና አትስጥ። 

ለምሳሌ፦ ቡና አፍልታ የምታጠጣህ ቢኾንና የአንተ ፍላጎት ወፍራም ቡና ቢኾን በምንም ዐይነት መልኩ ቀጭን ቡና ለመጠጣት አትቀበል። 

ቁምነገሩ አንተ ከንቀቷም ኾነ ከንዝህላልነቷ የተነሳ የሠራችውን ሥራ በፍቅር ስም በትዕግስት ስም እና በሌሎችም ስሞችም ምክንያት አድርገህ ብትቀበላት ከዚያ በኋላ ላንተ አክብሮት አይኖራትም ት..ን..ቅ..ሃ..ለ..ች!!!! ምክንያቱ ደግሞ አስቀድመህ የሰቀልከውን ደረጃ መጨበጥ እየቻለች ንቃህ ስትተወው ፈርተሃት(ባንተ ቤት ግን ታግሰሃት) አላስጠበቅክምና።

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *