የሚወዱህና የምትተኛቸው ሴቶች መብዛት አባወራ አያደርግህም!

ሳተናው!

በዚኽ ሴሰኝነት እንደ ጀብድ በሚቆጠርበት ዘመን እኛን ወንዶች ከምንታለልባቸው ርዕሰ ጉዳዮች አንዱ ይኼ ነው። ከብዙ ሴቶች ጋር መተኛት ጀብድ በድርጊቱ ውስጥም ማለፍ አባወራ(ወንዳወንድ) የምንኾንበት(የሚያደርገን) መላ ያለ ይመስለናል።

በዙሪያህ ያሉ ሴቶችን ለማወቅና ሴትንም ለመረዳት ከእነርሱ መተኛት አይጠበቅብህም። እንዲሁም ደግሞ አንተ የወንድነትህን ልክ እንድታገኝ በራስ የመተማመንህንም ከፍታ ታውቀው ዘንድ ሴቶች ከትዳር በፊት ድንግልናቸውን ሊሰዉልህ አይገባም።

ከትዳር ውጪ በምትፈጽመው ወሲብ ከሴት ጓደኞችህ ዘንድ ግርማ በወንዶቹም ዓይን ሞገስ አገኝበታለሁ ብለህ አታስብ።

በራስ መተማመንህም ቢኾን በተፈጥሮ እውነት ላይ የተመሠረተ እውቀት ሲኖርህ እርሱንም እንደየደረጃው፣ በቦታው እና በወቅቱ ስትፈጽመው ገንዘብ ይኾንሃል እንጂ ገንዘቡ፣ ስልጣኑ፣ ዝናው፣ የተኛሃቸው ሴቶችም ብቻ  ቢኖሩ ባዶነት የሚሰማህ ስጉ መኾንህ አይቀርም።

ሳተናው!
አባወራ ትኾን ዘንድ ከሴቶች ጋር ከመተኛት ይልቅ የሚከተሉትን ፈጽም፦

፨ በስሜት አትነዳ፣ አታድርግም
፨ ተፈጥሮኣዊ፣ አማናዊ(እውነተኛ) እውቀትን ገንዘብ አድርግ
፨ አስበህና አመዛዝነህ ምክንያታዊ ውሳኔ ስጥ
፨ ለወሰንከው ውሳኔ በመዳፍህ ሥር ላለፈውም ድርጊት “እኔ ነኝ” ስትል ኃላፊነት ውሰድ

እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው አንተን አባወራ የሚያሰኙህ መሠረታዊ እሴቶች ናቸው። በአእምሮህ ያለው እውቀት፣ በልብህ የያዝከው እምነት እና ከእነርሱም የተነሳ ከመዳፍህ የሚገኘው ሥራ አንተን ይገልጽሃል።

ከብዙ ሴቶች ጋር በመተኛት ምንም ጀግና አያሰኝም ከአባወራነት ማማም አያደርስም። ተፈጥሮኣዊው የሥነ-ጾታ (የሁለቱም ጾታዎች ተፈጥሮኣዊ ፍላጎትና ጠባይ) እውቀት ካለህ ይኽ በጣም ቀላል ነው።

ዐለም ደግሞ ይኼንን ቀላል ነገር በተለያዩ የኪነጥበብ ውጤቶቿ እና ሸቀጦቿ አማካኝነት እንደ ትልቅ ስኬት፣ ተወዳዳሪ የሌለው መዝናኛ አድርጋ ታሳይሃለች።

ሳተናው! ዐለም በማር እየለወሰች በቅቤ አፏም እያጣፈጠች የምትነግርህ ይኼ ነገር ተራና ቀላል ጉዳይ እንደኾነ ንቃባት። ሴቶችን መተዋወቅ፣ ማወቅ፣ ከእነርሱም ጋር ተቀራርቦ አብሮ መሥራት ተገቢ ኾኖ ሳለ “ብዙዎቹን ስትተኛቸው ታውቃቸዋለህ” ማለት ግን ለክብር የተሰጠህን ለውርደት ማዋል ነው።

አንተ ተፈጥሮኣዊ የኾነ የሥነ-ጾታ እውቀትህ ላለህ ግን ይኼን ላድርግ ብትል ቀላልና ኢምንት ነገር ነው። እንደ አባወራ ደግሞ ቀላልና በሕይወት ውስጥ ኢምንት ለኾነው ነገር መኖር ከተፈጠርክበት ዓላማ አንጻር የወረደና ተራ ሕይወት መኖር ነው።

ስሜቶችህን መግዛት ካልቻልክ እነርሱም የሚነዱህ መድረሻህንም የሚወስኑብህ ከኾነ ብዙ ሥራ እንደሚጠበቅብህ አስተውል። በሕይወትህ በሚፈጠሩ ክስተቶች ቶሎ ቱግ፣ ግንፍል፣ ደግሞ ክፍት፣ እዝን፣ ስብር፣ ደግሞም ፍንድቅ አትበል ከእነዚህ ስሜቶችም የተነሳ ለውሳኔ አትቸኩል።

ልብ አድርግ! ስሜት የለሽ ለመኾን ሞክር አላልኩህም። እርሱ ኢ-ተፈጥሮኣዊና የማይቻል ሲኾን ራስህን መግዛት ስሜትህንም መቆጣጠር ግን በመዳፍህ ሥር ነው። ይኹን እንጂ የምትሸነፍባቸው የምትወድቅባቸውም ቀናት መኖራቸውን አትዘንጋ ሲከሰቱም ብዙ አትደነቅ(ሰው ነሃ)።

ራስህን ባለመግዛትህ ምክንያት በተሸነፍክባቸው ስሜቶችህ በሠራሃቸውም ስህተቶች ላይ አትቆዝም፣ ስትቆጭም አትኑር። ይልቅስ ተማርባቸው፣ ሰልጥንባቸውምና እለፍ።

ተፈጥሮህን ስታውቅ ራስህን እና ሌላውንም ፍጥረት ስትመረምር ስትረዳም በራስ መተማመንህ ይጨምራል፤ አወዳደቅህም ለጊዜውም ቢኾን እንኳ(መነሳትህ አይቀርምና) ጉዳትህን መቀነስ ትችላለህ።

ግን እንዴት አባወራ ልኹን? ከምንስ ልጀምር? ….. ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *