የምትኖርለት፣ የምትሞትለትም ርዕይ

፩ኛ እንኳን ለጌታችን፣ ለአምላካችንና ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል አደረሰህ።

፪ኛ የምትኖርለት፣ የምትሞትለትም ርዕይ ስላለህ ደስ ሊልህ ይገባል።

ሳተናው!

በወራሪ የማይቆም፣ በወረርሽኝ የማይገታ፣ በጊዜ ማጣት የማይቀር፣ በጤና መጓደል የማይጣል፣ መንግስት ሲቀያየር የማይቀየር፣ በሐዘን ብዛት የማይዘነጋ፣ ገንዘብ የለኝም ብለህ የማትተወው፣ ሰዎች አቃቂር ቢያወጡም የማታፍርበት፣ ፈተናዎችን የሚሻገር ርዕይ ስላለህ ደስ ይበልህ።

ከራስህ አልፈህ ቤተሰብክን፣ ትውልድንና ሀገርክን የምትጠቅምበት አንተ እንኳ ብታልፍ የማያልፍ ዘመናትን የሚሻገር ርዕይ ስላለክ ደስ ይበልክ።

አለበለዚያ ግን ወንድሜ እንደ ቤት-እንሰሳ ሠርተህ ለመብላት፣ በልተህም ለመሥራት፤ ወጥተህ ለመግባት፣ ገብተህም ለመተኛት፤ ተኝተህም ለመዋሰብ፣ ተዋስበህም ለመራባት፤ ብቻ አትመላለስ።

ይኼ ከኾነ ኑሮህ በፈጣሪ አርኣያ የተፈጠርከው አንተን ክቡር ከኾነው የሰውነት ተፈጥሮህ አውርዶ ከበሬና ከአህያ፣ ከፈረስና ከበቅሎ፣ ከውሻና ከድመትም ጋር ያመሳስልሃልና ውለህ ሳታድር የምትኖርለትን ርዕይ አግኝ።

ሳተናው!
ርዕይ ያለው ሰው በመከራ/በፈተና ውስጥ ተስፋ አለው። ተስፋ ደግሞ ሕይወትን/ትውልድን እንዲቀጥል የሚያደርግ አንዳች ኃይል አለው። በዐይነ-ሕሊናህ ያየኸውን ርዕይ ከፍጹም እምነት የተነሳ ልትጨብጠው ስትራመድ ከፍተኛ የኾነ የተስፋ ግለት በውስጥህ ይቀጣጠላል።

ይኽ የተስፋ፣ የመኖር፣ የዛሬን ፈተና እና ተግዳሮት ተሻግሮ የማየት ትኩሳትህ ደግሞ ወደ ሌሎችም(በተለይም ደግሞ በሥርህ ወዳሉት ወደ ሚስትህና ልጆችህ) ይጋባል። ይኹን እንጂ የብዙዎቻችን ጥፋት ለዚህ ርዕያችን ከፈጣሪያችን ጋር ከመማከር ይልቅ የሚስታችንን ይኹንታ የሌሎችን ጭብጨባ እና ድጋፍ ስንሻ ተራ የቀን ቅዠት ወደ መኾን ይቀየርብናል።

ሳተናው!

ልብ አድርግ! እንዳንተ ዓይነት ሳተናዎች ኢትዮጲያ ሀገራችን ብዙ ነበሯት፤ እንዲህም ስለኾነ ነው የመንፈሳዊ ሕይወት ትሩፋታቸው ለሰሚው የረቀቀ፣ ለመረዳትም የራቀ የሚኾነው። ታሪካቸውንም መለስ ብለህ ብትቃኝ በብዙ ፈተና ውስጥ አልፈዋል፦ በሽታው፣ የእርስ በእርስ ጦርነቱ፣ የውጪ ወራሪ ጠላቱ፣ ረሃቡ፣ ሌላም ሌላም…። ይኹን እንጂ ርዕይ ነበራቸውና ዛሬን(እኔና አንተ ያለብነትን) በዐይነ-ሕሊናቸው ያዩ ነበርና ብዙ “ተዓምር” ሊባል የሚችሉትን ሠርተውልን አልፈዋል።

ወንድምዓለም!
ልብ አድርገህ ተከተለኝ ፈተና በምንም ዓይነት መልኩ ይምጣ፤ ትውልድ ይቀጥል ዘንድ ሀገራችን እንዳንተ ያሉ ጀግኖችን ትሻለች። ይኼ ጀግንነት ደግሞ በፈንታው ቁርጥ ውሳኔንና፣ በፍጹም እምነት የታሸ ወኔን፣ ጥንቃቄንና እና አስተዋይነት የተሞላበትንም እርምጃን ይሻል።

ይኼን ስታደርግ ደግሞ እባክህን የማንንም ጭብጨባ፣ ቲፎዞና ይኹንታ አትጠብቅ። አንተ በተለይ በዚህ ወሬው ሁሉ በሽታ፣ ሞትና እልቂት በኾነባት ዓለም ውስጥ ስትኖር ከራስህም አልፎ ለትውልድና ለሀገር የሚበጅ ርዕይ ሲኖርህ የተግዳሮቶቹ መብዛት ቢያጠነክረህ እንጂ ሊያርዱህ (ሊያስፈሩህ) አይገባም።

እሳት ከአፈር ውስጥ ወርቅን አንጥሮ እንደሚያወጣ በሰው ልጅ ላይ የሚጋረጡ ፈተናዎችም ከትውልዱ ውስጥ ፈሪውን በቁሙ ደጋግመው ሲገድሉት ርዕይ ያለውን ጀግና ግን አንጥረው፣ አበጥረው እና አጠንክረው ያወጡታል።

ሳተናው!

ስለዚህም በተለይ በዚህ ወቅት የምትኖርበትን ርዕይ የተፈጠርክበትንም ዓላማ ደግመህ ደጋግመህ ከልሰው፣ አስታውስው፣ እንዴት እውን እንደምታደርገውም አስብ። ዓለም በየዕለቱ ሙታኑዋን ስትቆጥር አንተ ግን ወደ ሰቀልከው ዓላማ ለመድረስ ስትጣደፍ ሚስትህና ልጆችህ ባንተ ውስጥ ተስፋን፣ ሕይወትን ያያሉና ይጽናናሉ፤ ይጠነክሩማል።

በፈተና አለመናወጥ ለራስህም ኾነ ለሌሎች የጽናት ተምሳሌት መኾን ፈተናም ካለፈ በኋላም ባሉበት መገኘት የጀግና ጠባዩ ነው። ይኼም ደግሞ የአባወራ ትልቁ ሚና፣ ኃላፊነት፣ ጸጋም እንጂ ነውና ተጠቀምበት፤ ስታደርገውም ደስ ይበልህ።

ለሀገርህ፣ ለትውልድ፣ ለቤተሰብህ፣ ለልጆችህ፣ ለሚስትህ የሚተርፍ የተፈጠርክለት ዓላማ ፣ የምትኖርለት ርዕይ አለህና ደስ ይበልህ። ይኼን ደስታህን ግን ምን እየሠራህ ትጠብቀዋለህ መሰለህ………….

ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *