የሴታቆርቋዡ (Feminism) የባርነት እሳቤ

ብዙ ጸሐፍት በእኛ እና በሰዎች መካከል ስለሚኖረን ማሕበራዊ መስተጋብር በንድፈ ኃሳብ(Theory) ደረጃ ብዙ ብለዋል። ኾኖም ግን ተሳክቶላቸው በሕይወታችን ላይ ለውጥ መፍጠር የቻሉት ጥቂቶች ናቸው።

ምክንያቱን ስንመረምር ደግሞ የእነሱ አቀራረብ ችግር ብቻ ሳይኾን የአብዛኞቻችን እውነትን የምናይበት እና የምንረዳበት መንገድ የተሳሳተ መኾኑ ነው። ይኽም እንዲኾን ሴታቆርቋዡ (Feminism) ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።(የጋሽ ተክለጻዲቅ መኩሪያን “የሰው ጠባይና አብሮ የመኖር ዘዴ” አንብብ)

በዚኽ ሰለጠነ በምንለው፣ ግልጽነትም ከየትኛውም ሰዎች ከኖሩባቸው ዘመናት ይልቅ የሕይወታችን ልምምድ ነው በምንልበት ዘመን ሰዎች እውነትን የሚፈሩ፣ በእውነት የሚደነግጡ፣ በእውነት የሚሳቀቁ ጭርሱንም ጸረ-እውነት ኾነዋል። የሚገርምህ ግን ወንድሜ ይኽን ኹሉ ሲኾኑና ሲያደርጉ ግን ስለ”እውነት” ቆመናል ብለው ነው።

ብዙዎች እውነት ተገልጣ “ክብራቸው” ፣ “ሰላማቸው” ከሚደፈርስ በእነርሱ “እውነት” (በውሸት) ተሸፍነው “በክብር” ቢመላለሱ ውስጣቸውም እያረረ “ሰላማዊ” ቢመስሉ ይመርጣሉ። ስለዚህም ምንም እንኳ እነርሱን የሚለውጥ ጽሑፍ ቢያነቡም ተፈጥሮኣዊውን፣ አርነት የሚያወጣውን፣ ዋጋ የሚያስከፍለውን እውነት ግን አይቀበሉም።

ከዚህ ይልቅ ግን አኹን በምቾት የሚያስቀምጣቸውን “ክብራቸውን”፣ ሰላማቸውን” የማያናጋውን “እውነት” ውሸት ተቀብለው እነርሱ “ነጻነት” ለሚሉት ነገር ግን ለባርነት ኑሮ ራሳቸውን ያጫሉ፤ አጭተውም አይቀር እነዚህን የውሸት ጥርቅሞች በሕግ አጸድቀው ይሞሽራሉ ይሞሸራሉም።

ይኽ በእንዲህ እንዳለ ሕብረተሰባችን በእውነት ላይ የተመሠረተ ጠንከር ያለ ሂስም(ትችትም) ኾነ በልማዶቻችን ላይ የሚታዩ ሕጸጾችን ለሚያርቅና ለሚያስታርቅ ኃሳብ ዝግጁ አይደለም፤ ይጠየፋቸዋልም። ስለኾነም በአብዛኛው የሚታተሙ ጽሑፎችም ኾነ በራዲዮና በቴሌቪዥን የሚቀርቡ መርሃግብሮች(programs) የሕብረተሰቡን “ክብር” (self-esteem) የጠበቁ እንዲኾኑ ይደረጋል።

ደፍሮ ማሕበራዊ ሕጸጾችን በመንቀስ፣ ተፈጥሮኣዊ እውነቶችን በመግለጥ፣ጣፈጠም መረረም ሐቁን ለሕበረተሰቡ ከማድረስም ይልቅ ሰው ቢሰማው ደስ የሚለውን “እውነት” ጉንጭ-አልፋ ወሬ እየተፈለገ ይሰናዳል። ይኼ ታዲያ ትውልዱ ለያዘው አውዳሚና ስርዓተ-ቢስ ጠባዩም ኾነ ዐመሉ አውቆትም ኾነ ሳያውቅ መሸሸጊያ ወይም ሽፋን እንዲያበጅ ያግዘዋል፤ “ልክ”ነቱንም ያጸድቅለታል።

ብዙውን ጊዜ የምንነጋገርባቸውን እነዚህን እውነታዎች ኃሳባችንንም የምንገልጽባቸው ጠንካራ ቃላች ሴታቆርቋዡ (Feminism) የፓለቲካ ልብስ አልብሶ እናም አስወንጅሎ ያስወግዳቸዋል። ይኽም ስርዓት አልባነትን የምንገልጥበት ራስወዳድነትን የምንወቅስበት ቃላት እስክንቸገር ድረስም ይኾናል። መሠረታዊ ፣ተፈጥሮኣዊ፣ ገሃዳዊ እውነታዎችን እንኳ መግለጽ እስክንከለከል ድረስ የሕብረተሰቡን “ክብር”(self-esteem) “ስሜት” አትንኩ እየተባለ በርካታ እውነቶችን ሳናውቃቸው ቀረን፤ ተጎዳንም።

ሲጀመር በቋንቋችን ውስጥ ባሉ ቃላቶች፣ ምሳሌዎች፣ ተረቶች፣ አባባሎች፣ ቅኔዎች ወዘተርፈ የምንጠቀመው ነባራዊውን እውቀት፣ ገሃዳዊውንም እውነት እንዲገልጹልን ነው። አንድም ደግሞ ልንጠነቀቃቸውና ልናወግዛቸው የተገቡትን ሥርዓት አልባና ቅጠቢስ ጠባዮችንም ኾነ ምግባሮችን ለመግለጥ፣ ለማስረዳትና ለማስወገድም ነው። የራሳችን ጠባይና ምግባሮችም ቢኾኑ ልናስወግዳቸው ፣ የማይወገዱ ተፈጥሮኣዊ ባሕርዮች ቢኾኑ ደግሞ (ኹሉ በዓላማ መልካም ኾኖ ተፈጥሯልና) የምናተርፍባቸውን ፈሊጥ እናበጅላቸው ዘንድ ነው።

በተለይ ደግሞ የእኛ የኹልጊዜ የመወያያ አጀንዳ የኾነው የወንድና የሴት ባሕርይና ጠባይ፣ ግንኙነት፣ ትዳር… በተመለከተ በሚደረገው ውይይት ከእኛ የቀደመው “መሃይም” ነው የምንለው ሰው ሐቀኛ(እውነተኛ) ነው። ቋንቋውንም በተፈለገው ቦታና ጊዜ በአግባቡ ይጠቀማልና መልእክቱም ግልጽ ነው።

“ዘመንኛው” ሴታቆርቋዥ እሳቤ(Feminism) ሲመጣ ግን ብዙዎቹን ቃላቶች፣ ምሳሌዎች፣ ተረቶች፣ አባባሎች፣ ቅኔዎች ከንግግርም ኾነ ከጽሑፍ ውጪ አደረገብን። ይኽን ተከትሎም በኹለቱ ጾታዎችና በመካከላቸው ስላለው ግንኙነት አንድነትና ልዩነት በተፈጥሮኣዊ እውነት ላይ ተመሥርቶ የሚደረግ ግልጽ ውይይት አብሮ ገደል ገባ።

ዛሬ ዛሬ “ግልጽ ውይይት” እንበለው እንጂ ተፈጥሮኣዊውን ባሕርይ ተንትነንና ተከትለን ሳይኾን በፓለቲካ አስታከን በድምጽ ብልጫ ባጸደቅነው አልያም በጀታችንን ከሚደግፉ ለጋስ ሀገራት በተሰጠን ንድፈ-ኃሳብ ዙሪያ የሚደረግ ነው። ይኽ ደግሞ ችግራችንን ከመፍታት ይልቅ ከድጡ ወደ ማጡ ይሰደዋል።

ወንድሜ! አንተ ግን ሰዎች በሸንጎ ላጸደቁት ላንተም ምቾት በልክህ ላሰፉልህ “እውነት” ሳይኾን ለተፈጥሮኣዊው እውነት ተገዛ። ይኼንንም እውነት ተሸክመው ራስህን እንደመስታወት የሚያሳዩህን ቃላት ምሥጢራቸውን መርምር፣ ጥበባቸውንም ቅሰም። ከትላንት ዛሬ፣ ከዛሬም ነገ ብርቱ ሰው ያደርጉሃል። ምቾትህን ከሚጠብቁ ደላይ ቃላት ግን ራቅ እድገትህን የካሮት ያደርጉታልና።

ስንፍናህን፣ ድክመትህንና ድንቁርናህን በትክክለኛውና ግልጽ በኾኑት ቃላት ሲገለጹልህ መብቴ ተነካ፣ ተሰደብኩ ወይም ጾታዊ ጥቃት ተሰነዘረብኝ ከማለት ይልቅ ትርጉሙንና እውነቱን ጠይቀህ ተረዳ። ደረሰህ ኾደባሻ አትኹን።

በአባወራ ገጽ ላይ ያንተን ምቾት የሚጠብቅ ደላይ ጽሑፍ አታገኝም። እየመረረህም ቢኾን እውነትን ትጎነጫለህ፣ ከበረታህ ብዙኃኑ ተስማምቶ ከተጫነበትና ከሚከተለው ቀንበር አርነት ወጥተህ በተፈጠርክበት ልዕልና ትኖራለህ። እምቢ ካልክ ደግሞ ላልተፈጠርክለት የባርነት ምቾት በውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ኑሮ ታኗኑራለህ።

ሳምንት ብንኖር…..

ግን ለመኾኑ….. ……. …. አኹን አንተ ወንድ ነህ? እርግጠኛ? አልተጭበረበርክም? እስቲ ዝቅ ብለህ እየው… … … …. …. ማለቴ ጽሑፉን

አንተ ወንድ ከኾንክ! … ….. ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *