የትዳርህ ስኬት ሙሉ ለሙሉ ያንተ እና የ…አ…ን…ተ ኃላፊነት ነው!

ወንድሜ! የሚስትህ ኃላፊነት አይደለም። ስለኾነም ስህተት ሠራች ተብላ የምትወቀስ ወይንም በራሷ ስሑት(የተሳሳተች) አይደለችም። ይኼን ስልህ ግን ፍጹም ነች ማለቴ አይደለም፤ “እንዴት?” ለሚለው ጥያቄህ ና ተከተለኝ።

ይህ አቀራረብ ምናልባት ዘመናዊ ትምህርት ተምረናል፣ እኛም ዘምነናል ለምንል ሰዎች ውሃ የማያነሳ ፍሬ ከርስኪ ወሬ ነው። ለአንተ እና ለእኔ እውነቱን በመመርመር ተፈጥሮን ለማወቅ ለምንጓጓ ሰዎች ግን በሥልጣኔ እና በዘመናዊነት ስም የሚጫንብንን ከንቱ አመለካከት ጥሎ የሚሄድ ነው። ከንቱው አመለካከት ግን በትዳራችን ውስጥ ጭቅጭቅ፣ ንዝንዝ፣ ጥርጥር፣ ተራክቦ-አልባ ሕይወት(ካለ የማይቆጠር)፣ ሲቀጥልም ወደ ፍቺ የወሰደን ካተረፍንበት ይልቅ ጉድለታችንን እና ኪሳራችንን ያበዛ እንደሆነ መታዘብ እንችላለን።

እስከዛሬ ልናይ በሞከርነው ሁለቱ ጾታዎች በተሰጣቸው ተፈጥሮአዊ የዓላማ፣ የጥበብ እና የሚና ጸጋ መሠረት የትዳርህ ስኬት አንተ ትከሻ ላይ መሆኑ እሙን ነው። ትዳርህን ከጥንስሱ(ከምሥረታው) ጀምሮ ያለውን ሂደት እስቲ ቆም ብለህ አስተውለው ጓደኝነትን የምትጀምር አንተ ነህ፣ ጓደኝነቱን ወደ ትዳር የምታመጣ አንተ ነህ፣ የምታጫት አንተ ነህ፣ ለጋብቻ የምትጠይቃት አንተ ነህ፣ ሽማግሌ የምትልከው አንተ ነህ(ቤተሰብ የምታስፈቅደው አንተ ነህ)፣ ቤትህ ስትገባም የሚስትህ ራስ፣ የትዳርህ ጉልላት፣ የቤትህ መሪ፣ የኑሮአችሁም አስተዳዳሪ አንተ ነህ!!!!

አንተን በምንም አይነት አስተምህሮ፣ ስልጣኔ፣ ዘመናዊነት ተጠቅሞ ከእነዚህ ከጠቅስናቸው ውጪ የሚያደርግህ ሁሉ ትዳርህን ቁልቁል የሚጥሉ፣ ሕይወትህን የሚመሰቃቅሉ፣ ቤተሰብህን የሚያሳጡ፣ ትውልድን የሚገድሉ፣ ሀገርን የሚያጠፉ ምናልባትም ስውር አጀንዳ ይኖራቸዋልና ተጠንቀቅ።

ይህ የማወጋህ ቁምነገር በዘመናት ፈተና ነጥሮ የወጣ፤ ወንድ እና ሴትን ያቀራረበ ትዳራቸውንም ሽቅብ በስኬት ያመጠቀ ነው። በአፍኣ በወሬም የተካበ ሳይሆን በተግባራዊ ፈተና የተሸለመ የሕይወት ባለቤትም ያደረገ ነው። ከዚህም ሕይወት(ትዳር) እናት አባትን አክባሪ፣ፈጣሪን ፈሪ፣ ለወገን ራሪ(የሚራራ)፣ ለሀገሩ ሟች የሆነ ትውልድ የወጣበት፣ የበቀለበት፣ የፈራበት ነው።
በአንጻሩ ግን እኔ እና አንተ የደረስንበት ዘመን ላይ ያለው የትዳር አመለካከት መጥቋል ተብሎ ነገር ግን ምን ያህል የዘቀጠ መሆኑን ለመመስከር ፍሬዎቹን ማየት ብቻ በቂ ነው። ራስ ወዳድ ትውልድ፣ ቤተሰቡን የማያከብር፣ ሰውን የማያፍር፣ የፈጠረውንም የማይፈራ፣ ከሀገር የአንድነት ስሜት ይልቅ ግለኝነት የሚያጠቃው በአጭሩ ትውልዱን ያቀለለ ነው።
ይህን መራራ ፍሬ እያየን ግን አሁንም ከእኛ በስልጣኔ ብዙ እርቀውናል የምንላቸው አገሮች ያላዋጣቸውን የከሰረ የቁልቁለት መንገድ ከስልጣኔ ቆጥረነው ተከትለናቸዋልና ልቦና ይስጠን!

እኔ ግን ያስተዋልኩትን ከመጽሐፍም፣ ከሰዎች ከራሴም ሕይወት ተሞክሮ እነግርሃለሁ።እንዲህም እልሃለሁ፦
አንተ ሰው የትዳርህ ስኬት ሙሉ ለሙሉ አንተ ትከሻ ላይ ነው፤ አለቀ ደቀቀ። ከዚህ በዝቶ የሚቀነስ አንሶም የሚጨመር የለም። ይህ የሚስትህ ጉዳይ አይደለም ፤የአንተና የ…አ…ን…ተ ብቻ እንጂ። እርሷ ይህን ስህተት ሠራሽ ተብላ፣ ስሁት(የተሳሳተች) ሆና ወይም ራሷ ስህተት ሆና የምትወቀስ አይደለችም። ልብ አድርግ!! ፍጹም ነች እያልኩህ አይደለሁም፤ ነገር ግን የዓለምን የእኩልነት የሥልጣኔ ድንቁርና ተወውና ውደዳት፣ ተንከባከባት፣ ጠብቃት፣ ድካሟንና ጥንካሬዋን ለይተህ ተረዳላት እልሃለሁ። ይህ ደግሞ ወደድክም ጠላህም፣ ጣፈጠህም መረረህም፣ ከበደህም ቀለለህም ለእኔ እና ላንተ ከላይ የተሰጠን ትዕዛዝ፣ ኃላፊነት፣ ግዴታ ነው።

ከምናቀርበው ሰበብ በላይ ተጠያቂነት ያለበት ኃላፊነት አለብን! አይዞህ ወንድሜ! ጊዜው የረፈደ ቢመስልህም ተመካክረን በድል እንኖራለን። ሔዋን በተሳሳተች የአዳም ሰበብ ከተጠያቂነት እንዳላዳነው ብሎም እንዳስቀጣው አስተውል።
አሁን ምናልባት እኔንና አንተን ከቀረጸን ማሕበረሰብ አንጻር…….ይቆየን።

፨፨፨ላለፉት 8-9 ወራት በጽሑፍ እንደተወያየነው አሁን ደግሞ በግንባር አባወራነትን የምንሰብክበት፣ የምንማማርበት መድረክ(ሴሚናር) እየመጣ ነው። ከተለመደው መንገድ ውጪ ትዳርህን ለመለወጥ ዝግጁ ነህ? የቤትህ አባወራ መሆን ትሻለህ? ወይስ ከሰጡኝ በልቼ ካጣሁ ተደፍቼ አድራለሁ ትላለህ?ይሄስ ደስታ አልባ፣ ወሲብ አልባ ሕይወትህ ተስማምቶሃል?፨፨

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *