የትዳርህ ስኬት… (ካለፈው የቀጠለ)

አሁን ምናልባትም እኔን እና አንተን ከቀረጸን ማሕበረሰብ አንጻር ባለፈው ሳምንት የተናገርኩት ነገር ምን ያክል እንደሚያወዛግብህ እረዳለሁ። ወንድሜ ልብአድርግ ግን! እውነትን በመፈለግ፣ በማንበብ፣ በመርመር፤ መርምረህ ባወቅኸውና በተረዳኸው እውነትም ቤተሰብህን የማኖር ኃላፊነት አለብህ። ስለዚህም በአስተውሎት ተከተለኝ።

አንተ ዛሬ ያገባኃት ሚስትህ ትላንት አንተው ራስህ የመረጥካት ናት። ዛሬ ላይ ችግሮች ቢኖሩብህ እንዳሰብከውም መኖር ባትችል ሰዎችን(ሚስትህንም ጨምሮ) ጥፋተኛ ተጠያቂም ከማድረግ ይልቅ ራስህን ጠይቅ ፈትሽ። አልያማ የመፍትሄ ሰው ሳይሆን ሰበበኛ እና ብሶተኛ ሆነህ ታርፈዋለህ። በዘመኑ፣ በሰው፣ በተፈጥሮህ(በተክለ-ሰውነትህም ሆነ በጾታህ) በደሞዝህ፣ በጤናህ፣ አታመኻኝ ይልቅስ ዛሬ ለማትፈልገው የሕይወት ውጤት የዳረገህን የትላንት የአላዋቂ (የመሃይም) ወሳኔህንና ድርጊትህን ንቀስ።

በእርሱም ቦታ ብዙኃኑ የተስማሙበትን ሳይሆን እውነት የሆነውንና ከተፈጥሮህ ጋር ስምምነት ያለውን እውቀት ገንዘብ(ጥሪት፣ ሀብት) አድርግ። ይህን እውቀት የግልህ ስታደርግ ትክክለኛ ውሳኔ ወስነህ፣ ቀጥተኛ አቋም ይዘህ፣ ውጤታማ ሥራን ትሠራለህ በእርሱም ደስ ይልሃል። በአሁኑ ወቅት ዓለም ስለ ወንድነት የምትነግርህ ነገር አንተን ከመስለቡ፣ ከማቀዝቀዙ፣ ሕይወትህን ጥገኛ ከማድረጉ ባሻገር ሴቶች የማያርፉበት፣ የማይደሰቱበት፣ የማያከብሩት እና ለንቀት የተፈጠረክ እስክትመስል ድረስ ይጎዳሃል።

አሁንማ ረፍዷል፣ እድሜዬም ገፍቷል፣ ካሁን በኋላስ ለውጥ አምጥቼ……. ይኼንና ይኼን የመሳሰሉትን ተስፋ አስቆራጭ ኃሳቦች ከውስጥህ አውጣ። እውነቱን ተረድተህ እውቀትንም ጨብጠህ በእነርሱም ላይ ተመሥርተህ ለመኖር ጊዜው መቼም አይረፍድም።

ወንድሜ! ትዳርህ ሙሉ ለሙሉ አንተ ትከሻ ላይ ነው!!!
ወደር የለሽ ትዳር፣ የሚጣፍጥ ፍቅር፣ በተራክቦ ምሉዕ የሆነ ሕይወት በተለይ ሴቷን የሚያረካ(ዛሬ ላይ ብዙ ባሎች ከብዙ ልምምጥ እና ደጅ ጥናት በኋላ ወሲብ እንደሚያገኙ ብዙም ሳትርቅ ራስህን ተመልከት) ፣ ደስተኛ ቤተሰብ፣ ዘውድ የሆነች ሚስት፣ የወላጆች ጌጥ፣ የቤተሰብ ፈርጥ፣ የወገን አለኝታ፣ የሀገር መከታ የሆኑ ልጆች የሚገኙት አ…..ን……ተ…. በ..ቦ..ታ..ህ በኃላፊነትህ ስትገኝ ብቻ ነው።

ወንድሜ! የፍቅር ግንኙነትህን ሙሉ ለሙሉ እደግመዋለሁ ሙሉ ለሙሉ የምትመራው አንተ ነህ። ይህ የሴቶችን መብት የሚገፋ፣ ጨቋኝም የሚባል ሳይሆን ይልቅስ ለማይናገሩትና ውስጣዊ ለሆነው ጥያቄያቸው መልስ የሆነ እና ውጤታማ ተፈጥሮአዊ ሂደት ነው። ሴቶች(ከጥቂቶች በስተቀር) በተፈጥሮዋቸው ለዚህ ድርጊትህ ግብረ-መልስ ይሰጣሉ፣ ይከተላሉ፣ ያጣጥማሉ፣ መሆኑን ሳያውቁትም ሳያስቡበት ይረካሉ፣ ይፈካሉ፣ ይደሰታሉ፣ ይነጠቃሉ(በእርካታ) እንጂ አይመሩም(ላልቶ ይነብብ)።
አስረጅ፦
1 ወንዶች ከተለመደው ግንኙነት ውጪ ለፍቅር ጨዋታ (date) ሴቶችን ይቀጥራሉ፣ ይጋብዛሉ። ሴቶቹ ደግሞ ጊዜ ወስደው ከተስማሙ ግብዣውን ይቀበላሉ፣ አምረውና ተሸልመውም ይመጣሉ። አልያ ግን ምክንያት ፈጥረው ይቀራሉ።
2 ወንዶች ሴቶችን ለጋብቻ ይጠይቃሉ። ሴቶቹም የጠየቃቸው ወንድ ሲመኙት የነበረ ከሆነ የደስታ እንባ ያነባሉ ወይም በደስታ ይዘላሉ ወንዶቹም ላይ ተጠምጥመው እሺታቸውን ይገልጻሉ። አልያ ግን ምክንያት ፈልገው ይርቃሉ።
እነዚህ በሴቶች እና በወንዶች የፍቅር ግንኙነት ውስጥ መሠረታዊ ከሆኑ ክስተቶች የምንረዳው የወንዱን መሪነት ነው(የምስሉ የሳልሳ “ዳንስ”ጭፈራ ወንዱ ሲመራ ሴቷ የምትከተልበት ልዩ ሕብረት(አንድነት) ነው)። ሴቷ ወንዱ ያቀረበላትን ግብዣ እርሱን በመከተልም ሆነ ባለመከተል ምርጫዋን ትገልጻለች። ይህ የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ዕለት አንስቶ የነበረ፣ አሁንም ያለ፣ ወደፊትም የሚኖር(እየደበዘዘ ቢመጣም) እውነት ነው። ትዳር ውስጥ ስትገባ ታዲያ ይሄን ድርሻህን፣ ይሄን ሚናህን፣ እርሷን ደስ ሲያሰኛት የነበረውን መሪነትህን ለምን ትተዋለህ?

እንግዲህ ጣፈጠህም መረረህም ትዳርህ ሙሉ ለሙሉ አ..ን..ተ ትከሻ ላይ ነው! የ..አ..ን..ተ..ም ኃላፊነት ነው!!! ወንድሜ! ሚስቴ እኮ፣ ደሞዜ እኮ፣ ቁመቴ እኮ፣ምን እዚህ አገር እኮ….እያልክ ሰበብ አታብዛ ይልቅስ…….ይቆየን።

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *