የአባቱ ልጅ

(ላላገቡት እህቶቼ)

የዛሬው ርዕስ ለመጀመሪያ ጊዜ የማነሳው ይኾናል። ከዚህ ቀደም በእርሱ ትይዩ “የአባቷ ልጅ፣ የአባቷ ልጅ” እያልኩ መጻፌን ልብ ይሏል።

ቃላትና አገባባቸው
ከአሁን በኋላ አባት እና የአባቱ ልጅ ስል እንደሚከተለው ነው፡
አባት የምለው፦ ወላጅ ፣ አሳዳጊ(የእንጀራ አባት፣ ታላቅ ወንድም፣ አጎት… ወ.ዘ.ተ.) ልጁን በስርአትና በስነምግባር ኮትኩቶ ከአጉል ዐመል ጠብቆ መክሮ፣ ገሶጾና ቀጥቶ የሚያሳድገውን ነው።

እንዲሁም ፈሪሃ እግዚአብሄርን፣ አዛውንትን ማክበርን፣ ሰውን መውደድን፣ የሀገር ፍቅርን፣ ማንነትን፣ ጀግንነትን፣ ድል አድራጊነትን፣ ቆራጥነትን፣ አሸናፊነትን፣ ትጋትን፣ ኃላፊነትን፣ መሪነትን፣ ወንዳወንድነትን….. …. እየኖራቸው የሚያሰለጥን ነው። (አባት ቢሞትም እናት እርሱ እያለ በሚያስተዳድርበት መንገድ ስርዓቱ ሳይፋለስ “አባታችሁ እንዲህ ያለውን አይወድም” እያለች በባሏ መንፈስ ልጆቿን ታሳድጋለች። ልጅም ቢኾን ያባቱ ፍቅር ያደረበት ምክሩና ተግሳጹ አኹንም ከገነት በእናቱ በኩል ይደርሰዋል፤ ይወደዋል፣ ያከብረዋል ፈለጉንም ይከተላል ፣ የአባቱ ልጅ፦ ከላይ የተዘረዘሩትን ያባቱን ፈለጎች የሚከተል ይኾናል( ለዚች እናትም አድናቆቴ ታላቅ ነው)።

ውዷ እህቴ ዛሬ የማወጋሽ ያባቱ ልጅ ከሌሎች ወንዶች ይልቅ ምርጥ የሕይወትሽ አጋር፣ የልጆችሽ አባት፣ የቤትሽም መሪ-ራስ፣ የጥምሽም ቆራጭ እንዴት እንደኾነና እርሱንም ከብዙኃኑ እንዴት እንደምትለይው ነው።

የአባቱን ልጅ ጥያቄ መቀበልሽ አበጀሽ አበጀሽ

የሥራን ትጋትንና ኃላፊነትን ከአባቱ እያየ ያደገው ልጅ በተቻለው አቅም ጥሮ ግሮ ቤትሽን ለመሙላት ይይደክማል እንጂ ቀምቶ፣ ሠሮቆ፣ የመንግስት/የሕዝብ ብር ዘርፎ አያሳፍርሽም። በተሰጠው ጸጋ ሠርቶ ማትረፍ ባተረፈው መደሰትና ማመስገን ሀብት የኾነለት ነው።

ቃሉን መጠበቅ የሚያውቅበት በትንሽ በትልቁም መሐላም የማያበዛ ነው። የተናገራት ጠብ የማትል (ሳይፈጽማት አትቀርም) ካልቻለም በጨዋ ደንብ ይቅርታ ይጠይቃል እንጂ የእናቴ መቀነት…. አያበዛም።

በኼድሽበት ኹሉ እንዳስከበረሽ በደረሰበትም እንዳከበረሽ ይኖራል። በልቡም ኾነ በሰው ፊት እንዳንቺ ቆንጆ፣ ስንዱ ባለሙያ እንዴሌለ መስካሪሽ ነው።

ለልጆችሽ የስነስርአት እና የስነምግባር መምሕራቸው እርሱ ነው። ባሕላቸውን እንዳይለቁ፣ ሃይማኖታቸውንም እንዲያጠብቁ፣ አዛውንቱን እንዳይንቁ፣ ሀገራቸውን እንዲያውቁ፣ አንቺን እናታቸውን(ሀገራቸውን) እንዲጠብቁ፣ ከክፉ እንዲርቁ፣ ከጠላት እንዲጠነቀቁ መምከር ብቻ አይደለም ከቃሉ ቢወጡ በአባታዊ ግሳጼው ብሎም በቅጣቱ ይመልሳቸዋል።

የቤትሽ መሪ/ራስ ይኾንልሻል። የትዳር መሪው የቤት አስተዳዳሪው ወንድ ነው። የአባቱ ልጅ ደግሞ በትዳሩ የማይደራደረው በቤቱ የማይደፈረው አባት አሳድጎታልና ዋጋው ውድ ነው። እህቴ ዐለም በቴሌቪዥን መስኮት አልያም በሕይወት መስክሽ እየመጣች “በእኩልነት” ስም የምታልልሽን አትመኚ፤ አንቺስ የሚሠራውንና የሚሄድበትን የሚያውቅ ወንድ ስታገኚ በእምነት ተከተይው ልብሽ አርፎ ፈቃድሽም ይፈጸም ዘንድ።

የጥምሽ ቆራጭ(ፈጻሜ ፈቃድ) ነው። ለምን መሰለሽ ወንድ በመኾኑ፣ በወንድነቱ ደስተኛ ሲኾን የወንድነቱን ጠባይና ኃይል እርሱንም ማበልጸጉን ደግሞ ይወደዋል። ይኽ ሲኾን ታዲያ በአባትሽ እንክብካቤና ጥበቃ በእናትሽም መልካም አርአያነት ተኮቶኩቶ ካደገው በውስጥሽ ካለው ሴታሴትነት ጋር ጠንካራ ተፈጥሮአዊ አንድነትን ይፈጥራል። ቁመና፣ ገንዘብ፣ ዝና፣ ዘር፣ ትምሕርት፣ የወሲብ ልምምዱ ኹሉ ይቅሩብሽና ያባቱ ልጅ ይኹን ያሳርፍሻል።

የአባቱ ልጅ የመኾኑ ምልክት
፩ኛ ስላባቱ ጠይቂው ጀግናው፣ አርአያው፣ አስተማሪው፣ አሰልጣኙ ….. እንደኾነ አውሮቶት አይጠግብም።

፪ኛ ስነስርአትን ከነምግባሩ፣ ቃሉን ከነተግባሩ፣ በራስ መተማመንን ከነድፍረቱ፣ የሚሠራውን ከእነ እውቀቱ አስተባብሮ ታገኚዋለሽ።

፫ ለድርጊቱ ኃላፊነት ይወስዳል ሰበብ አይደረድርም

፬ ስሜታዊ አይደለም የጥፋትን ሂሳብ እዛው በቦታው ያወራርዳታል እንጂ አያጠራቅማትም።

፭ ቀጠሮውን ያከብራል እንድታከብሪውም ግድ ይላል እንጂ “ወዶኛል” ብለሽ ሰዓቱን እንድትንቂ አይፈቅድም።

፭ “ሕይወቴ፣ እስትንፋሴ፣ ነፍሴ” እያለ አንቺን ማዕከል አድርጎ ጊዜውን አያባክንም ይልቅስ የሚመራው ሕይወት፣ የሚያሳካው ዓላማም አለው።

፮ ድንበር፣ አጥር ፣ ቅጥር፣ ገደብ ሲኖረው እርሱንም ሲያስከብር የሰውንም ያከብራል

ያባቱ ልጅ ካልኾነ
፩ እርሱ ብቻ አዋቂ ነው
፪ አይሳሳትም፤ ከተሳሳተም ስህተቶቹ ኹሉ ሰበብ አላቸው
፫ ድንበር ገደብ የለውም
፬ የኑሮው ምክንያት ዓላማውም ትኾኛለሽ፤ አንቺ ከሌለሽ የሚሞት ይመስለዋል፤ ይኽንንም በለቅሶ “በፍቅር ቋንቋ” ይነገርሻል።
፯ ኃላፊነትን ይሸሻታል በእኩልነትና በሥራ ብዛት አስታኮ ኃላፊነትን ወዳንቺ ያሻግራል።
፰ “እናቴ እንዲህ ብላ፣ እንዲህ አድርጋ፣ እርሷ ብትኖር፣ እርሷም…..” ያበዛል
፱ አኩራፊ ነው
፲ ወጥ አቋምና የታወቀ ፍላጎት የለውም
……ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *