የአባወራው ሚስት እማወራ ናትን?

ሳተናው!
በተለያዩ ጊዜያት የአባወራው ሚስት “እማወራ” ተብላ ስትጠራ ትሰማለህ። እውን ግን የአባወራው ሚስት በቤቷ እማወራ ናትን?

የአባወራው ሚስት፦
============
👉 ስነምግባር

የአባወራው ሚስት ባሏ በቤቷ፣ በትዳሯ ያለውን ቦታ ታውቃለች ይኸውም መሪነቱን፤ የራሷን ልከኛ ቦታዋንም እንዲሁ፤ የትዳሩ መስመሪያ እርሱ ነውና። ይኽ ምግባሯ መለያዋ፣ መወደጃዋ፣ ጌጧ፣ የአባወራውንም ልብ የምትገዛበት ገንዘቧ ነው።

እርሷን ከየትኛዎቹም ጠባዮቿ በላይ ከጓደኞቿም በተለየ የሚለያት አንድ ማንነት አላት እርሱም ለባሏ ያላት ትሕትና ነው። ለእርሱ የምታሳየው ትሕትና ስታገባ የጀመረችው፣ አቅም (የገንዘብ፣ የጉልበት፣ የዕውቀት) ስለሌላት ያመጣችው፣ ኃይማኖት ግድ ስላላትም የኾነችው አይደለም። ይልቁንስ ከአባወራው አባቷ እና ከትሑቷ እናቷ ቤት የወረሰችው መልካም ምግባር እንጂ።

👉 ሥነ-ስርዓት

የአባወራው ሚስት በእናት በአባቷ ቤት የነበረን ስርዓት(አባቷ ለዘረጋው) የመከተል ልምድ አላትና ይኽንንም እናቷ አርኣያ ኾና አሳይታታለችና፤ በትዳሯ ውዷ (አባወራው) የሚያስቀምጠውን ስርዓት የመከተል ምንም ዓይነት ችግር አይኖርባትም።

አባቷ የቤቱን ስርዓት በመወሰን እና በማስጠበቅ የቤቱን ሚና እንደሚወጣ፣ ይኸውም ተፈጥሮኣዊ ቦታው እንደኾነ፣ እናቷም ይኽንኑ በመከተል እንደምታግዘው ታውቃለች። እርሷም ይኽንን ተፈጥሮኣዊ ሚናውን እንዲወጣ ባሏን ትተወዋለች።

👉 ልጆቿን በመመገብ ፩ (ምግብ ስጋዊ)

የአባወራው ሚስት ለልጆቿ ምርጥ እናት ናት። እርሷ ተፈጥሮ የለገሰቻትን መጋቢነት ተጠቅማ ልጆቿ እንደ ቤቷ አቅም የተመጣጠነ እና ጤንነቱ የተጠበቀ ምግብ ተመግበው እንዲያድጉ ታደርጋለች።

ይኼንንም ራሷ በመሥራት አልያም የምትሠራ ሠራተኛዋን በመቆጣጠር ታደርገዋለች። በዚኽም ጤንነታቸው የተጠበቀ፣ ጠንካራና ብሩህ ልጆችን ታፈራለች።

👉 ልጆቿን በመመገብ ፪ (ምግብ መንፈሳዊ፣ ልቦናዊ)

የአባወራው ሚስት አባቷ በእርሷ የሕይወት ምርጫ፣ በሰከነ ጠባይዋ፣ በራስ መተማመኗ እና ለራሷ በምትሰጠው ዋጋ ላይ የተጫወተውን ከፍተኛ ሚና ታውቃለች። ከዚህም ተነስታ ልጆቿ ከአባታቸው ጋር ዛሬ ላይ ያላቸው ጤናማ ግንኙነት በነገ ስነልቦናቸው፣ የሕይወት ምርጫና ውሳኔያቸው፣ ለራሳቸው በሚሰጡት ዋጋ፣ የማደግ እና የመሥራት ወኔያቸው ላይ ከፍተኛ ሚና እንዳለው አውቃ ይኽን እንዲወጣ እንዲያወርሳቸውም ታበረታታለች።

👉 ሙያ

የአባወራው ሚስት በቤቷ ስንዱ እመቤት ናት። ስንዱነቷ አኹንም በአያሌው ከእናት ከአባቷ ቤት የወረሰችው ቢኾንም በቤቷ ግን ይኽንኑ ከሚጠብቀው፣ ከሚያበረተታታው እና ከሚሸልመው ባሏ ዘነድ ይልቃል። ይኽ ደግሞ በፈንታው ከባሏ ዘንድ መወደድን የሚያተርፍላት እርሷም ሐሴት የምታተርፍበት ነው።

👉 ብርታት

የአባወራዊ ሚስት ባሏ ደፋር፣ ቀና ብሎ የሚሄድ፣ ላመነበት አቋምም ጽኑ እና ቆራጥ መኾኑን ታደንቅለታለች፣ እንዲኾንም ታበረታታዋለችም። የእርሱ አንገት መድፋት የእርሱ እርሷን ፈርቶ መኖር ኢ-ተፈጥሮኣዊ፣ መጨረሻው ራሷን የሚያስንቅ፣ የሚያስደፍርም  እንደኾነ ታውቃለችና።

በተጨማሪም የልጆቿን አስተዳደግ የሚያውክ፣ ትውልድን የሚያመክን(የሚሰልብ)፣ መረንም የሚያወጣ፣ ሀገርን የሚያስደፍር የሚያፈርስም በመኾኑ ትጠነቀቃለች። ከዚኽም ተነሳ በምንም ዓይነት መልኩ፣ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ባሏ ከተፈጥሮኣዊ ልዕልናው ወርዶ በትሕትና ከስሯ እንዲቀመጥ እርሷ ደግሞ በልዕልና በእርሱ ላይ ልትሰየም አትፈልግም።

ቀድሞውኑ የወንድ ልጅ ግርማ ሞገሱ፣ የመወደዱ ምስጢር እርሷንም የሚማርካት ይኸው ጀግንነቱ፣ በራስ መተማመኑ፣ ቆራጥነቱ ነውና ዘወትርም በልኩ እንዲገኝ ብርታት ትኾነዋለች።

ማጠቃለያ
=======

ሳተናው!
የአባወራው ሚስት እንዲህ ነች። የፍላጎቶቿ ጥግ፣ የትዳሯ ስምረት፣ በልጆቿ ውጤታማም መኾን፣ በዚኽም የሚኾነው የትውልድና የሀገር ስኬት የእርሷ በትሕትና ከባሏ ጋር ተሳልጦ መኖር ነው።

ይኽንንም ለማድረግ ተፈጥሮዋ እራሱ ያግዛታልና ትሰለጥንበታለች። ስለኾነም እርሷ ትሕትና ጌጧ የኾነ የአባወራዊ ሚስት ብትባል እንጂ እማወራ አትባልም።

================================

ነገር ግን በእምቢተኝነት እርሱን ከሚናው ገፍታ፣ ዓላማውን አስታ፣ ወኔውን ሰልባ ከአባወራነቱ ይልቅ ከልጆቿ እንደ አንዱ ብታደርገው፤ ቀጥላም የቤቱ አዛዥ ናዛዥ የኾነች ዕለት፣ ወይም ልኹን ያለች ዕለት ትዳሯ መፍረስ የሚጀምርበት ዕለት ይኾናል።

አስተውል! አብረው እየኖሩ በርካታ ዓመታት የሚቆጥሩ ፍቺያቸው ፍርድቤት ሳይደርስ ትዳራቸው ግን በልባቸው የፈረሰ ብዙዎች እንዳሉ።

እንዲህ ስትኾን ለእርሱ ያላት ስሕበት እየደበዘዘ፣ በውሃ ቀጠነ እየተጋጨች፣ የእርሱ በሕይወቷ ውስጥ መኖር ትርጉሙ አልገባሽ እያላት፣ ለልጆቿ እርሷ ብቻ የምትበቃ እየመሰላት ወይ በአካል በቤቱ እየኖረ በስነልቦናው ስልብ (ፈሪ)ታደርገዋለች አልያም ወደ ፍቺ ታመራለች።

ከዚኽም በኋላ የራሷንም የእርሱንም ሚና ጠቅልላ ራሷን፣ ቤቷን፣ ልጆቿን፣ ኑሮዋን “ለመምራት” ትደክማለች። ይኽ እንግዲህ ከሞላ ጎደል የእማወራዋ መገኛ ይኾናል።

እማወራ….ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *