የአባወራው በራስ መተማመን

ሳተናው!
አብዛኛው (99% እና ከዚያ በላይ )ምስኪን በኾነበት ሕብረተሰብ በአባወራ የፌስቡክ ገጽ ላይም ኾነ በአባወራ ድረ ገጽ ላይ የሚለጠፉት ጦማሮች ለተደራሲው (ምስኪኑ ወንድ) መራር ናቸው።

እስከዛሬ ባሉት ጦማሮች ምስኪንነትን ከነመገለጫው አይተናል ዛሬ ደግሞ የአባወራውን በራስመተማመን ከምሰኪኑ ጋር በንጻሬ በመጠኑ እንይ።

በራስመተማመን፦
በጠቅላላው ስናየው ለራሳችን እንደምንሰጠው ዋጋ ኹሉ በይበልጥ በአስተዳደጋችን ይወሰናል (ምንም እንኳ መቀየር ቢቻልም)። በተለይም ደግሞ ልጆች ከአባታቸው ጋር ያላቸው ጤናማ ግንኙነት ለራሳቸው ለሚሰጡት ዋጋ እና በራሳቸው ለሚኖራቸው በራስ መተማመን ከፍተኛውን ድርሻ ይወጣል።

ብዙዎች በዓለማዊ ትምሕርት ስለበለጸጉ(ማስተሬት፣ ዶክትሬት) ስላላቸው አልያም በሀብትና በስልጣን ስለናጠጡ፣ ታዋቂነትና ተሰሚነትም ስላገኙ በራስ መተማመናቸውም ኾነ የራሳቸውን ዋጋ የሚያገኙት የሚጨምሩትም ይመስላቸዋል። ይኽ መሻታቸው በራሱ በራስመተማመናቸው እጅጉን ዝቅተኛ ከመኾኑ የተነሳና የእርሱን ክፍተት “ይሞላልናል” ብለው በያዙት የተሳሳተ ግንዛቤ ነው።

አንድ ንግግር ተናግረህ እንዲጨበጨብልህ ስትቆም፣ አንድ ሥራ ሠርተህ ስለሥራህ አስደናቂነት ከሰዎች አፍ ስትጠብቅ፣ አንድ ጽሑፍ ለጥፈህ(በሶሻል ሚዲያም ቢኾን) በቲፎዞው ብዛት “እውነትነቱን” ካረጋገጥክበት….. አንተ ጭብጨባ ምግባቸው፣ ምስጋና ልብሳቸው፣ ቲፎዞ አጀባቸው ከኾኑት ወገን ትኾናለህ።

ጭብጨባ ለምስኪኖች ቀለባቸው ነው!
=========================
አኹን በዓለማችን ላይ የምናየውም ይኼንን ነው። በራሳቸው መተማመን የማይችሉ ሰዎች ድጋፍን፣ ጭብጨባን፣ ቲፎዞን ሲፈልጉ ታያላችሁ። ሊሠሩት ለተገባቸው ሥራ ውዳሴን እና ምስጋናን ይጠብቃሉ። ውሸታሟ ዓለምም እንደዚኽ ዓይነት ሰዎችን ታበረታታለች፣ ትወዳለችምና ድጋፏን ትሰጣቸዋለች።

ለእነዚህ ምስኪኖች የሚፈልጉትንና ቀለባቸው የኾነውን ቲፎዞ፣ አጨብጫቢም ዓለም ታበዛላቸውና ከተፈጥሮ የራቀን እውነት፣ ከሰውነት ጋርም የማይስማማ ጽንሰ-ኃሳቧን ለትውልዱ ትግትበታለች።

እነዚኽ ውዳሴ እና ጭብጨባ ፈላጊ ምስኪኖች ኹልጊዜ የሚታዩት ከራሳቸው አልፈው ለሰው አሳቢ፣ አዛኝና ተቆርቋሪ መስለው ነው(የምስኪንን ትርጉም ልብ ይሏል)። ነገር ግን እነርሱ የሚመሩት ትዳር፣ ቤተሰብ፣ ተቋም፣ ሀገር ተፈጥሮን የሚቃረን፣ ከሚጎረብጠው እውነት ይልቅ ለሚመቸው ውሸት ያደላ፣ ፍትኃዊነትም የጎደለው ይኾናል።

በተጨማሪም በሐቅ ከሚያቆሙት(ከሚሠሩት)ሥራቸው ይልቅ በዙሪያቸው ካሉ ሰዎች ለሚያገኙት ምስጋና ትልቁን ቦታ ይሰጡታል። ስለዚህም ስጦታቸውን፣ ቸርነታቸውን፣ ሥራቸውን አጨብጫቢ ካለበት ውዳሴ ከሚሸመትበት ምስጋናንም ከሚያጭዱበት መስክ(አደባባይ) ይፈጽሙታል።

ሳተናው!
ልብ አድርግ! ለምስኪኖች ውዳሴው ከሥራቸው ይልቅ ይመዝንባቸዋል። ይኼም በአብዛኛው ከአስተዳደጋቸው ይመነጫል። በልጅነት አስተዳደጋቸው እውነትን እንዲሹ፣ በእውነት እንዲቆሙ፣ ስለእውነትም እንዲሞቱ ሳይኾን ይበልጡን ሰውን እንዲሰሙ፣ ለሰው ስሜት እንዲጨነቁ፣ ሰውን እንዲያስደስቱ፣ ሰው እንዳይከፋባቸውም(በተለይም ሴቶች) ተመክረው፣ ሰልጥነውም አድገዋልና ነው።

እንዲህ ያደገው ምስኪን የሰውን ፊት ያያል፣ ብዙኃኑን ይሰማል፣ ብዙኃኑን ያምናል፣ ብዙኃኑን ይከተላል፣ ከብዙኃኑ ጋርም ይነጉዳል። የብዙዎቹ አስተሳሰብ ልክ ለመኾኑ ጽንሰ-ኃሳቡን ብዙዎች በመከተላቸው ብቻ ያረጋግጣል። ከዚኽም የተነሳ በራሱ መንገድ ተፈጥሮን መርምሮ ከሚረዳው እውነተኛ እውቀት ይልቅ ስሐተትም ቢኾን ከብዙኃኑ ጋር መሳሳትን ይመርጣል።

እርሱ አውቆና መርምሮ ያገኘው እውቀት እውነት ቢኾንም ባወቀው ልክ ባመነበትም ነገር ለብቻው መቆም ይፈራል። በውስጡ ያደገ፣ ውስጡ የበቀለ የሚመካበትም የራስ መተማመን የለውም ከውጪ፣ ከደጅ ከሰውም እጅ ይፈልገዋል እንጂ። ይኽም ለሠራው ሥራ እውቅና፣ ለአቋሙም ይኹንታን ፈላጊ እንዲኾን ይዳርገዋል።

ሳተናው! ጭብጨባ ለአባወራ ምኑም አይደለም!
=========================
አባወራ ከምስኪን የሚለየው መሠረታዊው ነገር በራስ መተማመኑ ነው። አባወራ ሊሠራ ላሰበው ሥራ ርዕይ ሰንቆ፣ ዓላማን ሰቅሎ፣ በውሳኔው ቆርጦ፣ ፈተናን ታግሶ ይሠራል። ለጭብጨባ የሚቆምበት፣ ውዳሴ የሚያማትርበት፣ ምስጋና የሚያዳምጥበት ምክንያት የለውም፤ ይኼም ቀረብኝ ብሎ አይቆጭም ሊሠራ ካሰበው ነገርም አይከለከልም፤ አይቀርምም።

አባወራ በራስመተማመኑ በእጁ የራሱም ዋጋ በደጁ የኾነለት እንጂ ለይኹንታና ለልኬት የሰው ሚዛን ሊፈልግ ከሰው መንደር አይቀላውጥም። እርሱ እውነትን ይፈልጋል፣ ላመነበት እውነት ይቆማል፣ ባመነበትም እውነት ይገኛል በእርሱም ቤቱንም ይመራል። ይኼንንም ሲያደርግ ከሰዎች የሚገኝ ጭብጨባን፣ ሙገሳን ሳይጠብቅ በበራሱ ለራሱ ይኾናል።

ለእርሱ በእውነት ላይ የተመሠረተው እውቀቱ፦ ሚና ለይቶ፣ አቋም ይዞ ለመኖር በቂው ነው። ምንም እንኳ ይኽ ጸባዩ አኹን ላይ በአፉ “ሰለጠንኩ”፣ “ዘመንኩ”፣ “ፍቅርም” ገብቶኛል ከሚለው ትውልድ ዘንድ “ግትር”፣ “ወግ አጥባቂ” ቢያሰኘውም።

….ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *