የ”አንድ አለኝ” ደዌ

ሳተናው!
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከመገናኛ ብዙኃን መስፋፋትና ከኪነጥበባዊ ሥራዎች ማበብ ጋር ተያይዞ አብዛኞቻችን የእነዚህ ውጤቶች ምርኮኛ ኾነናል። አኹን አኹን ደግሞ የማሕበራዊ ትስስር ድረ ገጾች መፈጠር ጭርሱኑ ትውልዱን ተፈጥሮኣዊ እውነትንና ማንነቱን እንዳይመረምር፣ ማሕበራዊ እሴትን እንዳያጠነክር፣ የጋራ የኾነ ሀገራዊ ርዕይን እንዳይጨብጥ ይልቁንስ በእንቶ ፈንቶ እና ግልብ በኾኑ ወሬዎች ጊዜውን እንዲያጠፋ ዳርገውታል።

ከእነዚህ መገናኛ ብዙኃንና ማሕበራዊ ትስስር ገጾች በኪነጥበብ በተለይም በዘፈን፣ በፊልም፣ በግጥምና “እያዝናናን እናስተምራለን” በሚሉ መርሃ ግብሮች የተለያዩ ሥራዎች ይወጣሉ። እነዚህ ሥራዎች ደግሞ በአብዛኛው ትውልዱን “ደስ” አሰኝተው አስቂኝ ሥራ ሠርተው፣ አሳዝነው(አሳዛኝ ኪነጥበባዊ….) እና አዝናንተው(አስጨፍረው) ሀብትን ያከማቻሉ።

በዓለማችን ላይም ይኸው በመገናኛ ብዙኃኑ የሚሠራጨው “መዝናኛ” በሕዝቦች ላይ አንዳች ዐዲስ ልማዳዊ አንድምታ የመፍጠር እና የማስለመድ አቅሙ እንዲኹም ተጽዕኖ ፈጣሪነቱ ከፍተኛ ነው። ከዚህ ሥራ የሚገኘው ገቢ ደግሞ ከፍተኛ የኾነ የሀብት ምንጭም በመኾን የተቋማቱን ባለቤቶች ከከበርቴዎቹ ጎራ ያሰልፋቸዋል።

ከዚህ ተጽዕኖ ፈጣሪነቱ የተነሳ ታዲያ በግዴለሽነት የሚዘጋጁ አልያም ደግሞ የአንዲትን ሀገር ትውልድ ለማኮላሸት(ለመስለብ) ታስበው የሚሠሩ አሉ። እኔ እና አንተ ግን “በኪነጥበብ” ስም የምንፈርጃቸው ዝግጅቶች ተፈጥሮኣዊ ማንነትህን ሳታውቀው የሚሸረሽሩ፣ አቅምህንም የሚያሳጡህ የጠላት ዓይነተኛ መሣሪያ ናቸው።

ከዚህም የተነሳ ምናባዊ በኾነና እነርሱ ደርሰው በሰጡህ ኢ-ተፈጥሮኣዊ ሕይወት ውስጥ የማይጨበጥ ዓላማ ሰቅለህ፣ ምግባር የተለየው እምነት ተሸክመህ፣ ደስታና ሰላም በራቀው ሕይወት እየዳከርክ፣ በማይሞላ ኑሮ የምዕራባውያንን እጅ እየጠበቅክ፣ በማያሳርፍ ትዳር እየቆሰልክ አንተንም ኾነ ፈጣሪን የሚያሳዝኑ ልጆች አፍርተህ ትኖራለህ።

ሳተናው ወንድሜ
እነዚህ በመገናኛ ብዙኃኑ ውስጥ ከምትሰማቸው ከብዙ ብዙዎቹ ትርክቶች ውስጥ ዛሬ ጠቆም ላደርግህ የወደድኩት በየዘፈኑ የምትሰማውን በዓለም ውስጥ “ለእኔ የምትኾን አንድ ፍቅረኛ አለች” የሚለውን ነው።

ብዙዎች ይኼንን “ተረት ተረት” በዘፈኑ፣ በፊልሙ፣ በልብ ወለዱ፣ በግጥሙ እና በመሳሰሉት ደግመው ደጋግመው ስለተጋቱት ተዋሕዷቸዋል። ልባቸውም አምኖበት እውነትና ልክ አድርጎም ተቀብሎታል።

አንተ ግን በሠራህና እንዴት ልትኖር እንዳለህ መመሪያ በሰጠህ ፈጣሪህ ዘንድ ግን አንዲትን ሴት ሚስት አድርገህ እንድትይዝና ኑሮህንም ከእርሷ ጋር እንድትመሠርት ስርዓት ተሠርቶልሃል። ይኹንና “ለእኔ የምትኾን ሴት አንድ ጥግ አለች” ብለህ በፍለጋ እንድትኳትን “ስታገኛትም” ካለ እርሷ መኖር እንደማትችልና ብታገባህ ደስታህ ሙሉ እንደሚኾን መሬት ላይ ወድቀህ እንድትለምን አይደለም። አልያም ደግሞ “ካላንቺ መኖር አልችልም”፣ “ካላንቺ ሕይወቴ ባዶ ነው”፣ “የምኖረው ላንቺ ነው” እያልክ “ፍቅሬን ይገልጻሉ” ብለህ ራስህን የሚያስንቁናና ባዶ በሚያደርጉ ቃላት እንድትሞላ አይደለም።

እነዚህ በ”ፍቅር” ስም ኪነጥበብን ታከው የመጡት ትውልዳችንን ፈሪ(ወኔ ቢስ)፣ ደካማ፣ ዓላማ ቢስ፣ ተጨባጭ ላልኾነ ምናባዊ (የቅዠት) ሕይወት እየዳረጉትና ለዘመናዊ ባርነትም አሳልፈው እየሰጡት ነው። እርሱም በ”ፍቅር” ስም ለዓላማው የማይቆም ፈሪ፣ ከዘመን ተሻጋሪ ሀገራዊ ርዕይ ይልቅ “ዛሬን ካንቺ አድሬ ነገን ልሙት” በሚል የቀን ቅዠት የባከነ አድርገውታል።

ሳተናው ወንድሜ! እኔ የምመክርህ በምድራችን ላይ በአንዱም ጥግ “ለእኔ የምትኾን አንዲት ሴት አለች” እያልክ እንዳትታለል እንጂ ብዙ ምርጫ አለኝ ብለህ እንድትማግጥ አይደለም፤ ይኽ ካንተ ይራቅ!

ነገር ግን አንተ አባትህ ቀጥቶና ገርቶ በስነምግባርና በስነስርዓት እንዳነጸህ እደግ፣ በርዕይና በአመክንዮ መጓዝም ጀምር። ያንጊዜ ስርዓትህን ተቀብላ፣ ምግባርህን ተከትላ የርዕይህን መሳካት የምታግዝ፣ ቃልህን የምታከብር፣ የምትታዘዝህም ሴት ስታገኝ ከሌሎች መርጠህ አባቷን(ያሳደጋትን) አስፈቅደህ አግባት።

በጭራሽ ሴትን ልጅ ወይም ሚስትህን “ካላንቺ መኖር አልችልም”፣ “ካንቺ ውጪ መኖር እፈራለሁ” አትበላት። አልያም ደግሞ ራስህን ከእርሷ ውጪ በማሰብ ልብህ አይድከም፣ ሰውነትህ አይራድ(አይንቀጥቀጥ)፣ አትፍራም ክፉኛ ት..ን..ቅ..ሃ..ለ..ች..ና..!!!

ሴትን ተንበርክኮ ለጋብቻ መለመን (የትዳር ጥያቄ ማቅረብ) ተገቢ ነውን? በemail እና በ”የአባወራዎቹ ወግ” group ጠብቁኝ

ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *