የወንድ ምስኪንነት በትዳር

 

ምስኪን የነበረው ወንድ ትልቅ የምስኪንነት ብቃት(ብቃት ከተባለ) ላይ የሚደርሰው ምስኪን ያልነበረው ደግሞ ምስኪን መሆን የሚጀምረው ትዳር ውስጥ ነው። በተለይ የምስኪንን ትርጉም በትክክል አለመረዳት ወንዱን ሁሉ ትዳር ውስጥ ምስኪን እንዲሆን ይጋብዛል። ምስኪን-ወንድ ፍቅር መሰጠት ፣መንከባከብ መስሎት ተፈጥሮአዊ ወንድነቱ ውስጥ ያለውን ባሕርይ ወደ ጎን ይገፋዋል።

በወንድነት ፦ሚስቱ በሴትነቷ የምትጠብቀውን የምትፈልገውንና የሚያስፈልጋትን አስቦ፣ አቅዶ እና መጥኖ (እንደ ምስኪኑ-ባል ለምኖ፣ ተለማምጦ፣ማባበያ ሰጥቶ ሳይሆን) መፈጸም(በተለይ የወሲብን ፍላጎት)
በባልነት፦ አቋም መያዝ፣ በአቋም መጽናት፣ በወቅቱ መወሰን፣ መምራት፣
በአባትነት፦ ማስተዳደር፣ መገሰጽ፣ አስፈላጊ ሲሆንም መቅጣት፣ ……..እና ሌሎችም ወደፊት ብንኖር የምናነሳቸው አባወራውን የሚገልጹ ጠባዮች አይሞክራቸውም(ፀረ-ትዳር የመስሉታል)። ምናልባትም እነዚህ ነገሮች የሚስቱን ተፈጥሮአዊዉንም ሆነ ህገ መንግስታዊዉን መብት ይጥሳሉ ብሎ ያስባል፤ ምስኪን ነውና።

ምስኪን-ወንድ (ከዚህ በኋላ ምስኪን-ባል እያልን የምንጠራው አግብቷልና) የወንድነት ሚናው ላይ ፍዝ(ሲፈዝ) ሲሆንና እንዲያም በመሆኑ ተያይዞ የሚመጡ ችግሮችን እስቲ እናንሳ።

ልብ አድርጉ ምስኪን-ባልን ሚስቱ ከሰዎች(ከሴትም ከወንድም) መካከል እንድትመርጠው ያደረጋት መጀመሪያ በጾታ ወንድ መሆኑ ነው። ይህ እንግዲህ በተቃራኒ ጾታዎች መካከል ያለ ተፈጥሮአዊና ጤናማ ስህበት ነው። ነገር ግን የምስኪን ባል ትልቁ ስህተት ይህንን ያስወደደውን ያስመረጠውን እና ቀሪ ዘመኗን የእርሱ እና ከእርሱ ጋር ለመኖር እንድትወስን ያደረጋትን የእርሱን ወንድነት ጠብቆ አና አበልጽጎ ከመገኘት ይልቅ እንዳውም ያቆረቁዘዋል።

ይህ ለሚስቱ እንዳትቀበለው የሴትነቷን ጥያቄዋን የማይመልስ እንዳትተወው የተጨበጨበለት ምስኪን-ባል በመሆኑ ሀዘንተኛ እና ድብርተኛ ያደርጋታል የትዳሩንም ጥንካሬ ወይም ጥብቅነት ያላላዋል። ዛሬ ላይ ከዋነኞቹ የትዳር መፍረሻ ምክንያቶች አንዱና ግንባር ቀደሙም ነው።

ነገር በምሳሌ…….

እስቲ የቁስ አካል እና የኃይል ጥናት(physics) ስለ electricity እና magnetism ምን ይላል? እኛ ካነሳነውም ሀሳብ ጋር ያላቸውን ዝምድና ባጭሩ እንይ።
Magnetism(ማግኔጢሳዊ ኃይል)፦ ማግኔት ብረትን የመሳብ ኃይል ያለው ብረት ነው። እንዲሁም ማግኔት ሁለት ዋልታዎች ሲኖሩት ስማቸውም የሰሜን ዋልታ እና የደቡብ ዋልታ ይባላሉ። ማግኔት ከሌላ ማግኔት ጋር በተመሳሳይ ዋልታዎቹ ሲገናኝ ይገፋፋል(ሰሜን ዋልታ ከሰሜን እንዲሁም ደቡብ ዋልታ ከደቡብ) በተቃራኒ ዋልታዎቹ ሲገናኝ ደግሞይሳሳባል(ሰሜን ዋልታ ከደቡብ እንዲሁም ደቡብ ዋልታ ከሰሜን)።

የሁለት ማግኔቶች ማግኔጢሳዊ ኃይል (የመሳሳብም ሆነ የመገፋፋታቸው ኃይል) በዋልታዎቹ ጥንካሬ እና በሁለቱ ማግኔቶች መካከል ባለው ርቀት ይወሰናል።የማግኔቶቹን ዋልታዎች ደግሞ ሌላ ኃይል በመጠቀም ማጠንከር ይቻላል።ለእኛ ንጽጽር እዚህ ድረስ ይበቃናል ለበለጠ ግንዛቤያችሁ ስለ electricity ማንበብም ትችላላችሁ።

ከላይ ያቀረብኩትን ምሳሌ ወደ ተነሳንበት ጽንሰ ሀሳብ ላምጣው። ወንድንና ሴትን ተፈጥሮአዊ የሆነ ጾታዊ መሳሳብ ያቀራርባቸዋል…… ልብ አድርጉ ይህ መሳሳብ ተፈጥሮአዊ ነው። ይህ የተፈጥሮ ስበት ምን ያክል ጠንካራ እንደሆነ የምትረዱት ሁለቱን ከወለዳቸው፣ ካሳደጋቸው፣ካስተማራቸው ….ብዙ ዋጋ ከከፈለላቸው ቤተሰብ ለይቶ ቤተሰባቸውን ከሚያውቁበት ዕውቀት አንፃር ሲታይ ኢምንት ሊባል በሚችል ዕውቀት ከሚያውቁት ሰው ጋር ያቆራኛቸዋል። አይደንቅም? እኔ ሁል ጊዜ ይህን የፈጣሪ ሥራ ሳስበው ይገርመኛል ይደንቀኛልም።

አሁን አስተውሉ ፈጣሪ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጥሮ ሲያበቃ ወንድ እንዲሆን ባበጀው ሰውነት ውስጥ የወንድነትን ባሕርይ በሴቷ ውስጥም የሴትነትን ባሕርይ አካቶ ነው። ይህ ወንድነትና ሴትነትም ነው በሁለቱ መካከል የመሳሳብን፣የመከጃጀልን ፣የመፈቃቀድን ኃይል የሚያጭረው። ይህን በማግኔቱ ዋልታ የመሰልነው ወንድነትና ሴትነት ታዲያ መጀመሪያ እንዳገናኛቸው ኃይሉ ሳይቀንስ(ፍቅራቸው ሳይቀንስ) እንዲቀጥል ወንዱም ወንድነቱን ሴቷም ሴትነቷን አጥብቀው መያዝ በመካከላቸውም በኑሮ የተነሳ የሚፈጠረውን መራራቅ ማጥበብ ነው።

በማግኔቶቹ መካከል ያለውን የመሳሳብ ኃይል ሳይደበዝዝ እንዲቀጥል ለማድረግ ደግሞ ትልቁ መፍትሔ ሁለቱንም ዋልታዎች ከበፊቱ የበለጠ ጠንካራ ማድረግ መሆኑን ልብ ይሏል። በዚሁ መልክ በሁለቱ ፍቅረኛሞች መካከል ያለውን የመዋደድ ስበት ለማስመር(ለማሳካት) ትልቁ መፍትሔ ጾታዊ ተፈጥሮአቸውን እና ሚናቸውን ማወቅ መረዳትና ማጎልበት ነው። ባጭሩ ግንኙነታቸው ባል ወንድ ሲሆን ሚስትም ሴት ስትሆን ይጠብቃል ይጠበቃልም(ምንም እንኳ ይህ ብቻ ባይሆንም) ማለት ነው።

ዛሬ ላይ ወንዳወንድ ወንድ መሆን ለፍቅር ግንኙነት እንቅፋት ለትዳርም ጋሬጣ ከዘመኑም ጋር አብሮ አለመዘመን ተደርጎ በተለያየ መንገድ እንድንቀበለው እየቀረበ ነው። ምስኪን-ወንድም የዚህ ሰለባ ነው። ይህ ምናልባት ለግብረ-ሰዶማዊነት መስፋፋት ምክንያት ይሆን? ሌላ ጊዜ እንመለስበታለን።

ግን ወንዳወንድነትን ማን ይሆን ከዱርዬነት(bad boy) ጋር ያስተካከለው?

የምስኪን-ባልን ምስኪንነት በመግፈፍ ፍዝ(ደካማ) የነበረውን የወንድነት ዋልታ(polarity) ጥንካሬን በመጨመር(ይህ ሴቶችንንም ወደ ሴትነት ዋልታቸው ይመልሳቸዋል) ሴቶች ለሽምግልና እና ለዳኝነት መግለጽ የሚቸገሩበትን የፍቅረ ግንኙነት መሻከር ወይም መቀዛቀዝ ያለሰልሰዋል ያሟሙቀዋል።

ስለዚህም አባወራ ይጽፋል ወንድ ሁሉ ሴቶች እርፍ የሚሉበት አባወራ ይሆን ዘንድ። እናንተስ ኃሳብ አስተያየታችሁ እንዴት ነው? ሴቶችስ(ሚስቶችስ) እውነት እኛ ወንዶች(ባሎች) የምንናፈቅ አባወራ ወይስ የምናሳዝን አንዳንዴም ………ኧረ ብዙ ጊዜ የምናናድድ ምስኪን ነን?

ሙሉ ደስታና እርካታ ተወዳጅ ለሆኑት ሴቶች፣ ላፈቀርናቸው ሚስቶች፣ ቁርጥ እኛን ለወለዱልን እናቶች ይገባል እውነት በእውነት አሜን። ይገባል……ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *