የወንድ ያለህ!!!

 

ይህ ጽሑፍ አሁን ያለውን የወንዶች መልፈስፈስ (ወንዳወንድ ሆኖ ያለመገኘት ችግር)እየዳሰሰ ወደፊት ስለ ምንወያየው የወንድነት መገለጫዎች እና ወንዳወንድ ቁም ነገሮች የጋራ የሆነ የመግባቢያ ሀሳብ እነድንይዝ በቃላት ድርድር ይዞን ይዘልቃል፡፡
እኛ ሰዎች በኑሮአችን የሚያስፈልገንን አግኝተን ደስተኛ ሆነን ለመኖር በብዙ መልኩ እንጥራለን፣ እንማራለን፣ እንሠራለን፣ ደግሞም እየሠራንም እንማራለን፡፡ በዚህ ሂደት ራስንም የማሳደግ ዑደት ውስጥ ደግሞ በማሕበራዊ ህይወታችን ወዳጅ ዘመድ እናፈራለን፣ የትዳር አጋር እንይዛለን፣ ልጅ እንወልዳለን፣ እናሳድጋለን፣ እናስተምራለን ወዘተርፈ..፡፡ይህ ሁሉ ሲሆን አካባቢያችንን ለማወቅ፣በዙሪያችን ያሉትን ሰዎች ለመረዳት፣እንደምናደርገው ጥረት ራሳችንን ተፈጥሮአችችንን ለመረዳት፣ ከተፈጥሮአችን ጋረ ስምም የኾኑ ተግባሮችን የኑሮ ልምምዶችን ለማወቅ አወቀንም በተረዳነው መጠን ለመኖር የምናሳየው ጥረት እጅግ አናሳ ነው፡፡

ራስን ያለማወቅ ጣጣ

ለዚህም ይመስለኛል ዛሬ ዛሬ ሰው ከተፈጥሮው ጋር የማይስማሙ ተፈጥሮውን ያላገናዘቡ ከእንሰሶችም ዘንድ እንè የማይገኙ ባዕድ ዐመሎችን አምጥቶ ሲለማመድ በእነርሱም ከአድካሚውም ኑሮው ተዝናንቶ፣ተጽናንቶና ልቦናው አርፎለት ለመኖር የሚጥረው፡፡
ይሁን እንጂ የተፈጥሮ ልኩ አይደሉምና ልቡናውን አያሳርፉለትም ልቡናው ያለማረፉ ታዲያ አንዱን ሲጥል ሌላውን ሲያንጠለጥል ደግሞም ሌላ …….ብቻ ከድጡ ወደ ማጡ ያዘግማል፡፡ ከሰውም ተርታ ወጥቶ ከእንሰሳ ገባ ብለን ስንገረም ተገርመንም ሳናበቃ ይብሱኑ እንሰሳት የማይሠሩትን ሥራ እየሠራ ከእንሰሳትም ተራ እየወጣ ይገኛል፡፡

ባሕርያችን በዓላማ ስለመሰጠቱ

ፈጣሪያችን እኛን ሰዎችን በዐላማ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጥረን፡፡ ይህን ዐላማ ለማሳካት መሣሪያ እንዲሆነን ደግሞ ወንዳወንድ ባሕሪን በወንድ ውስጥ ሴታሴት ባሕሪን በሴት ውስጥ አካቶ ባሕሪያችንን ሳንለቅ ልዩነታችንን እንደጠበቅን፤ ግን ደግሞ ልዩ እና ሚስጥራዊ በሆነ አንድነት ደግሞ ተዋደን እና አንድ (ባልና ሚስት) ሆነን እንድንኖር፤ ወደደ ፈቀደ፡፡ ወዶም ፈቅዶም አልቀረ ዕድሜው ከሥነ ፍጥረት ጀምሮ የሚቆጠረውን የመጀመሪያውን ትዳርን መሥረቶልናል፡፡
• ልብ በሉ በእርሱ ዕቅድና ዐላማ ሥር ብቻ ሆኖ መኖር ልባችንን የሚያሳርፍ ነፍሳችንን የሚያድስ ሥጋችንንም የሚያስደስት ይሆናል ማለት ነው፡፡

እርሱ ይኽን ካደረገ እኛ ደግሞ የተፈጠርንበትን ዐላማ የተሰጠንን ባሕርይ ይኽም ወንድ ከሆንን ወንድነታችንን ሴት ከሆንን ሴትነታችንን መረዳትና በዚህ ዐላማ ሥር ሆኖ መኖር ይጠበቅብናል፡፡ እንጂማ አርነት ወጥተናል ነፃነትም ተሰጥቶናል ብለን ልቅ ልንሆን፤ አልያም አንዳንድ ግለሰቦችም ሆነ አንዳንድ መንግስታት መብታችሁ ነው ስላሉን እኛም በተለያየ አጋጣሚ ፍላጎት ስላደረብን ከባሕርያችን ጋር የማይስማማ ባዕድ ጠባይ ብናመጣ ከጾታ አቻችን ጋር መተባበርን ትተን ብንፎካከር በአንድነት መኖር አንችልም፡፡ አብሮነታችን በፍቅር ማሸብረቁ ይቀርና ጥርጥርና ፉክክር ይናኙበታል፡፡ወደፊት ገፍተን ትዳር መመስረት ይከብደናል፤ ብንመሰርትም ለችግሮቻችን መፍትሔ ስናስብ ፍቺ ይቀናናል ልጆች ያለ አባት ወይም ያለ እናት ያድጋሉ፤ሥርዓት አልባም ይሆናሉ፡፡

ይህ በትዳራችን ውስጥ የጠፋው ፍቅር ታዲያ ወደ ማሕበረሰባችን ከዚያም ወደ ሕብረተሰባችን ሲቀጥልም ወደ ሕዝባችን ይጋባና የሀገር ፍቅር ይላላል ወይም ይጠፋል፡፡ ይህም ዛሬ ላይ ዐለማችችንን መልኩን እየለዋወጠ ሠላማን የሚነሳት፤ሰውን እርስበርሱ እየከፋፈለ ሕዝብን በመንግስት ላይ እያሳመጸ የሚታየው ፍቅር መጥፋት ምንጩ ይብዛም ይነስም በትዳር ውስጥ የጠፋው ፍቅር ነው፡፡ ሰዎች በዘር ጎሳ ተከፋፈሉ ሲባል ሰምተናል፤ዛሬ ግን ከዚያ አልፎ አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት ከየትኛውም የሰው ልጅ ከኖረባቸው ዘመናት በበለጠ መስማማት እያቃታቸው ሽኩቻቸው ለትውልድ ፣ ለሀገርም እየተረፈ ነው::

ወቅታዊው እውነታ

አሁን ያለንበትን ዘመን ደግሞ ግምት ውስጥ ስናስገባ ሴቶች እህቶቻችን በኑሮዋቸው የሚያስፈለጋቸውን ቁሳዊ ፍላጎት አሳክተው ለመኖር የግድ ወንድ (ባል) ማግባት አይጠበቅባቸውም ባገኙት የመማር ዕድል ተጠቅመው፣ተምረው ሥራ መያዝ ሲቀጥልም ቤት ተከራይተውም ሆነ ሠርተው ብቻቸውን መኖር የተለመደና እየተለመደም፣እየተዘወተረም ያለ እውነት ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ታዲያ እኛ ወንዶች እንደዚህ በመሰለ የኑሮ “ነፃነት” ውስጥ ያሉ ሴቶችን በፍቅረኛነት በትዳር አጋርነት ስንይዝ ወንድ ሆነን ነውና የሚያዩን የሚያገኙን እኛም ወንድ ሆነን መገኘት አለብን፡፡ ያገናኘን የጾታችን ልዩነት፣የተቃራኒ ጾታዎች ስበት ተፈጥሮአዊና ጤናማ፣በተቃራኒ ጾታዎች መካከል የሚጠበቅ፣ሲገኝም የማይደንቅ ክስተቱም ከመሆኑ በፊት ተናፋቂ ሲሆንም አስደሳች ከፈጣሪም የተለገሰ እንጂ ሰው በችሎታው እና በዕውቀቱ ያላገኘው ነውና ወንድነታችንን አጽንዖት ሰጥተን ልንይዘው፣ልንከባከበው፣ልናሳድገው እና ልንገልጸው (ልንለማመደው) ይገባናል፡፡

ነገር ግን ዛሬ እየሆነ ያለው ይህ አይደለም፡፡ ብታምኑም ባታምኑም ዛሬ ወንድ የሆነ ወንድ ማግኘት ይቸግራል፡፡ያ ሴቶች የሚማረኩበት፣ ሴቶች የሚመኩበት፣ ለሞገደኛው ስሜታቸው ወደብ፣ ለጥርጣሬያቸው ገደብ፣ ለብዙ ምርጫቸው ወሰን፣ ለስጋታቸው ዕረፍት፣ ለድካማቸው ብርታት፣ ለኑሮዋቸው መሪ፣ ለቤታቸው አስተዳዳሪ፣ ለሴትነታቸው ወንድ፣ ልካቸውን የሚያቅላቸው እርሱንም የሚሰጣቸው፣ ዕርካታን የሚያጎናፅፍ፣ የወንድ ልኩ፣ የፍቅር ምንጩ፣ከወንድም የወንድ ጌታ፣የኔጌታ የሚባልለት፣ ለልጆቻቸው አባት ለእነርሱ ባል “ባሌ” ብለው የሚመኩበት ወንድ በከፍተኛ ሁኔታ እየተመናመነ ነው፡፡

ምነው አገር ምድሩን የአዳም ዘር ሞልቶት ብትሉኝ ወንድ ሁሉ ለሴቶች ወንድ አይደለም እላች=ለሁ፡፡

ብታምኑም ባታምኑም ፈጣሪ ከፈጠራቸው ፍጥረታት ውስጥ ከተፈጥሮአዊ ባሕሪው ውጪ እንዲኖር በመገደድ በከፍተኛ ሁኔታ የቀደመ ማንነቱን በመልቀቅ እየጠፋ ያለው የሰው ወንድነቱ ነው፡፡

ወንድነት ሲደበዝዝ

ይህ የጠፋ ወይም እየጠፋ ያለ ወንድነት ታዲያ ዛሬ ላይ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሴቶች ከትዳራቸው ደስታ እንዲያጡ፣ እንዲሰላቹ፣እንዲማረሩ፤ባላቸውም ላይ እንዲነጫነጩ፣ እንዲነዛነዙ፣ እንዲጨቃጨቁ እያደረገ ነው፡፡በዚህም ላይ ከባላቸው ጋር በሚፈጽሙት ወሲብም ዛሬ ላይ ደስተኛ ስላልሆኑ(ወንድነት የለውምና) ለነገው ያላቸውን ተነሳሽነት እየገደለ ነው፡፡ ይሁንና ለጣፋጭ ወሲብ ፍላጎት የሌላቸው ከወለዱማ እንዳውም ከነመኖሩ የረሱት ተደርገው በእኛ በወንዶች ብዙውን ጊዜ ባለማወቅ ይወነጀላሉ፡፡

ታዲያ በባላቸው ወንድነት ላይ ለውጥ ያጡት ሴቶች ለራስ ወዳድ ባላቸው ፍላጎት ብቻ መንጋለላቸው፣መጠቀሚያም መሆናቸውን ሲያስቡት በውሃ ቀጠነ ትዳራቸውን ይፈታሉ፡፡ለፍቺውም የሚሆን ምክንያት የተለያየ ዓይነት የዳቦ ስም እየተሰጠ የት ይደርሳሉ የተባሉት ጥንዶች ባጭር ሲቀሩ መታዘብ በከተሞቻችን የተለመደ ክስተት እየሆነ ነው፡፡

ይቆየን……………………………….

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *