የዛሬ ወንድ አልጋ(ንገስ) ሲሉት…..

ሳተናው!

አንተ በቤትህ ያለህ ቦታ፣ በትዳርህ ያለህ ሚና፣ በሚስትህ ልብ ውስጥም ሊኖርህ የተገባው ስፍራ ለአንተ በስነፍጥረት(በከፈጣሪህ ዘንድ) የተዘጋጀ ነው። አንተ የሚጠበቅብህ ራስህን ማወቅ፣ ስሜቶችህን መግዛት፣ ዓላማህን መስቀልና ሚናህን መያዝ ብቻ ነው።

ይኽን ቦታ ወይንም ሚና መንግስት የሚሰይምልህ፣ ሚስትህ የምትሰጥህ፣ አንተም በብዙ ድካምና እንግልት የምታገኘው ሳይኾን ራስህን ስታውቅና ስትኾን ብቻ የምትወርሰው ነው። ይኽንንም ስፍራህን ስትይዝ ብቻ ትዳርህን፣ ቤትህን፣ ሚስትህን፣ ልጆችህን፣ ትውልድንና ሀገርህን መምራት ይቻልሃል።

አለበለዚያ ግን ይኽን በሚስትህ ዘንድ የሚያስከብርህን ከእርሱም የተነሳ የሚያስወድድህን ሚና ትተህ በቤትህ የአገልጋይነትን፣ የተላላኪነትን እና የትሕትናንም ስፍራ ብትይዝ እርሱው ባንተ ይጸናል። ከዚያ በኋላ ሚስትህ አንተን መልሳ በልቧ ማንገስ፣ ማክበር፣ ላንተ መሸነፍ ያቅታታል።

????????????????????

አንድ ደረቅ እውነት ልንገርህ ሚስትህ ልቧ ላንተ መሸነፍ፣ መማረክ ካልቻለ ያንተ በምንጣፍህ ላይ መንፈራገጥ ወገብህን ይቀጭ ይኾን እንጂ በእርሷ ዘንድ መልዕክት የለሽ፣ እርካታ ቢስም ከንቱ ውዝዋዜ ነው።

????????????????????

አንተ በቤትህ፣ በትዳርህ “ንግስቴ ነሽ?..” ያልካት ሴት ብታዛት ድፍረት፣ ብትልካት ውርደት፣ ብትመራት ንቀት፣ ብትተኛት ስንፈት በእርሱም የሚኾነውን እርካታ ሽንፈት አድርጋ ትቆጥረዋለች። ምስጋናው ይቅርና በስርዓት እንኳ ጎረበጠኝ አትልህም። ይኽንንም የሚቀበል ዝግጁነት የላትምና ዘወትር መጋጨታችሁ አይቀርም።

????????????????????

ከዚኽም የተነሳ አንተን በቤቷ የትዳር አጋሯ፣ አጋዧ፣ ረዳቷ፣ ታዛዧ፣ የልጆቿ አባት አድርጋ፤ ልቧን የምትሰጠው፣ ቀና ብላ የምታየው የምትሸነፍለት፣ ራሱን ገዝቶ ልቧንም የሚማርክ ንጉስ መፈለጓ አይቀርም!

????????????????????

ስለዚህም አንዴ መሪውን አስጨብጠሃታልና እንዳስጀመርካት አንገትህን ደፍተህ “ለልጆችህ” ስትል ትኖራለህ። በዚህም በትዳር የቆየህበትን እድሜ ትቆጥራለህ እንጂ እርሷም ኾነች አንተ በትዳራችሁ ማረፍም ኾነ መርካት አትችሉም ከተፈጥሮ ስርዓት ውጪ እየኖራችሁ ነውና።

በዚኽም ሕይወት በግጮቶቻችሁ ኹሉ አጥፊ አንተ፣ በዳይ አንተ፣ የሚፈረድብህ አንተ፣ ይቅርታ ጠያቂ አንተ፣ የቤቱ አባወራ ግን እርሷ ኾና ትኖራላችሁ። ምክንያቱም እርሷ “ንግስት?” ናትና ብታጠፋም ከሳሽ፣ ነቃሽ፣ ወቃሽ አይኖርባትምና። አንተ ደግሞ “ሁሉን ቻይ”፣ “ታጋሽ”፣ “ክንፍ ቀረሽ መልኣክ” ነህና ይኽ ይጸናል።

እመነኝ ይኽ አካኼድ ትዳርህን ከመጉዳቱ የተነሳ ልጆችህን ሊኖራቸው የሚገባቸውን ስርዓትና ምግባር አሳጥቶ ያሳድጋቸዋል። አዎን! ልጆችህ አንገታቸውን የደፉ፣ “ጨዋ” ሊባሉ ይችሉ ይኾናል።

ነገር ግን ካንተ ዓላማ ቢስነት፣ ሚና መሳት፣ ግዴታህን ካለመወጣት የተነሳ ወንዶቹ ልጆችህ በጭምተኝነታቸውና በታጋሽነታቸው ውስጥ ስሜታዊነት፣ ግንፍልነት የሚያይልባቸው ምስኪኖች ይኾናሉ።

ከዚኽም በተጨማሪ አቋም የለሽ፣ ሙልጭልጭነታቸውን ከሰው ጋር አብሮ ለመኖር የተጠቀሙበት ዘዴ አስመስለው ፍርኃታቸውን ይደብቁበታል። ልብ አድርግ! ይኼንንም ካንተ የተማሩት እንጂ ከየትም አያመጡትም።

ሴቶቹ ደግሞ ልባቸው ለፍቅር የማይሸነፍ ደንዳኖች በትምሕርት፣ በስልጣኔ እና በቁሳዊ ኃብት የሚመኩ፣ ይኽንንም በአፋቸው በሚያንበለብሉት “መንፈሳዊነት” ከለላ ሰጥተው ተፈጥሮኣዊ ሚናቸውን አሽቀንጥረው ያለልካቸው ያንተን አባወራነት የሚላበሱ ወንዲሎች ይኾናሉ።

እነዚህ ሴቶች ታዲያ  እንደእናታቸው የሚንበረከክላቸው፣ “የሚታገሳቸው”፣ የሚታዘዝላቸው፣ ለልጆቻቸው አባት የሚኾን ስለ “ትዳሩ” ሲል አንገቱን ደፍቶ ልጆቹን የሚያሳድግ ወንድ ይፈልጋሉ እንጂ በጭራሽ በሴትነታቸው ስለሚኖራቸው ትሕትና ቦታ አይሰጡም፤ የት አዩትና?

ይኹን እንጂ ለእንደዚህ ዓይነቱ ወንድ ልባቸው እንደማይሸነፍ ሲያውቁት በባላቸው ላይ ለመሄድ ብሎም ትዳራቸውን ለማፍረስ ዐይናቸውን አያሹም። ይኽን ሲያደርጉም የትኛውም አመክንዮ አይመልሳቸውም፣ ምንም ዓይነት “መንፈሳዊነትም” አያቆማቸውም። ምክንያቱም ምን ቢማሩ ከምክንያታዊነታቸው ይልቅ ከልጅነት ጀምሮ በእናት ባባታቸው ቤት(በአንተ ዘንድ) የቀረጻቸው ልምምድ ይኽ ነበርና።

ሳተናው!

ይኽ እንዳይኾን ከፈለግክ አስቀድመህ ያንተንም ኾነ የሴትን ልጅ ተፈጥሮ መርምር እወቀውም። ከዚኽም የተነሳ የምታገባት ሴት ካንተ ጋር የአባወራነትን ሚናህን የማትሞግት  እንዲሁም በቤታችሁ በትዳራችሁም ሁለት አባወራ ኖሮ ሕይወታችሁም ዘወትር በአምባጓሮ፣ ጸሎትህም ምስጋና የራቀው በእሮሮም የታጀበ እንዳይኾን አስቀድመህ ምርጫህን አስተካክል። 

ተፈጥሮህን ካለማወቅህ፣ ሚናህን ካለመረዳትህ ግዴታህንም ካለመወጣትህ በተለይም ደግሞ የሴት ምርጫህን ካለማስተካከልህ የተነሳ ለሚመጣብህ ፈተናም ዘመኑን፣ ሴቱን፣ ሀገርህን፣ ፖለቲካውን እና ሌሎችንም አትውቀስ።

አስተውል!
ቦታህን እወቅና የሚስት ምርጫህን አስተካክል እርሷም ጠባይዋ እንደመልኳ ያማረ፣ እንደ እናቷ ትሕትናን የተላበሰች ልቧም አባቷን ለመሰለ አባወራ የተነጠፈ ትውልድን(ልጆቿን) በእነርሱም ሀገርን ለመገንባት ከአባወራው ባሏ የተባበረች እርሷም፦

የ  አ  ባ  ቷ   ል  ጅ   ትኹን!

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *