የ”የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” መዘዝ

ጀግናው ወንድሜ!
ልብ አድርግ ጀግንነት ውስጥህ ነው። በምንም ዐይነት መልኩ እንኳን ሌሎች ሰዎች ራስህም ለራስህ የስንፍናን ቃላት አትናገር። ስንፍናህን ካወቅከው ወደ ጉብዝና የሚወስዱህን መጽሐፍት አንብብ ለጉብዝና አርአያ ከሚኾኑህም ጋር ተወዳጅ።

ብዙዎች አንተን ከማጎበዝ ከማጀገንም ይልቅ ስለስንፍናህ ማውራት በስሕተትህም መሳለቅ ይወዳሉ። አንተ ተለውጠህ ጀግና እንድትኾን ቢሹም ከምስኪንነትህም ኾነ ከስንፍናህ የሚያገኙት ጥቅም ሲቋረጥ መልሶ ይከፋቸዋል።

ጀግና እንድትኾን ይፈልጋሉ ነገር ግን …

እናት(የዚህ ዘመን አብዛኞቹ እናቶች)
ልጇን “ጀግና ኹን እህትህን አንደሰው እንዳይመታት ጠብቃት ደግሞም አትፍራ” ትላለች። ነገር ግን ልጁን የሚያጀግኑ ድርጊቶች ላይ ማዕቀብ ትጥላለች። አፏ ጀግና ኹን እያለው ልጅነቱን በፍርሃት ትመርቅለታለች። እርሱም ቁም ነገር መስሎት ዶሮ በጮኸ ቁጥር እየፈረጠጠ “ፈሪ ለናቱ” ይላል ሲፎክሩ አይቶ።

ጓደኞች
ቆራጥ ኹን፣ አትልፈስፈስ ይሉሃል። መለማመድ ስትጀምርና የቆራጥነትህ ሰይፍ እነርሱንም ሲነካቸው ግን የሌለበትን “ዐመል አመጣ” ይሉሃል። ትላንት በምስኪንነት ጥላህ ሥር የምስጋና ዜማ ቋቅ እስኪልህ እንዳላንቆረቆሩልህ ዛሬ ደግሞ ምሬቱን ይግቱሃል። አንተም እነርሱን ላለማጣት ስትል ምስኪን ኾነህ ትቀራለህ።

ሚስት
ጊዜህን ገንዘብህን እርሷን ያስደስታሉ ባልካቸው ነገሮች ታጠፋለህ(እርሷን፣ቤተሰቦቿን…. ትንከባከባለህ)። ነገር ግን “ለቤቱ አይኾንም”፣ “ኑሮኣችንም አልተሻሻለም” ተብለህ ደግሞ ትታማለህ። ራስህን ሰብስበህ፣ ተምረህ፣ ሠርተህ መለወጥ ስትፈልግ ደግሞ “ጠባዩ ተለወጠ”፣ “ትቶኛል” ትባላለህ። የኼን ስትፈራ ምስኪን ኾነህ ትቀራለህ።

ማሕበረሰቡ
ማሕበረሰባችንም የዚሁ አስተሳሰብ ተጠቂ ነው። አንድ ቀን ኹሉን የሚቀይር መሪ፣ አንድ ቀን ከድኽነት የሚያወጣን፣ ፍትህ የሚያሰፍን መሪ፣ አንድ ቀን ምርጥ ብሔራዊ የእግርኳስ ቡድን፣ ይመጣል ብሎ በተስፋ ይኖራል። የለውጡ አካል በመኾን ያለችውን ሸክም ግን አይነካትም። ልጆቹን በስነስርዓትና በፈሪሃ እግዚአብሄር ከማሳደግ ይልቅ ወደ መረንነት ይነዳቸዋል።

“የሴቶች መብት…. ባዮች”(Feminists)
ሴትን ልጅ የሚያከብር፣ የሚንከባከብና ጥቃቷን የሚጠየፍ ወንድ እንዲኖር ይፈልጋሉ። እነርሱ ግን ባሎቻቸውን ባለማክበር፣ ለወንድ ያላቸውን ንቀት ባሎቻቸው ላይ በማንፀባረቅ ለልጆቻቸው እያሳዩ ያሳድጋሉ። ትዳራቸውን ያፈርሳሉ፣ የፍርድ ቤትን አድሎአዊነት በመጠቀም ልጆችን ያላባት(ያለ ስነስርዓት) ያሳድጋሉ። ልጆችን ቀጥቶና ቆንጥጦ ማሳደግ ለእነርሱ መብት ረገጣ (ጥቃት) ነው፣ ምክንያቱም እነርሱ ራሳቸው ስርዓት አልባ ናቸውና። ልጆቻቸው (ትውልዱ) እንዲለወጡ ቢፈልጉም እነርሱ ግን ዋነኛ የለውጡ እንቅፋት ናቸው።

ጀግናው ወንድሜ!
ምን አለፋህ? ብዙዎች የሚፈልጉት ነገር በአንድ ሌሊት ተለውጦ ማየትን እንጂ የለውጥ ኺደቱ አካል መኾንን አይደለም።

ሚስትህ፣ ማሕበረሰቡ፣ ሕዝቡ፣ ሀገርህ ጀግናን ይሻሉ አንተ ወደ ጀግንነት የምታደርገውን ጉዞ እና በውስጡም ያለውን ውጣውረድ ግን ማንም መታገስ አይፈልግም። አንተ ግን በመጀመሪያ ደረጃ ራስህን ፈልገህ የምታገኘው፣ የምታሳድገውም ለራስህ መኾን አለበት። ከተራ ምስኪንነት ወደ ጀግና አባወራነት ተለውጠህ ሲያዩ ማድነቃቸው፣ መደመማቸውም ኾነ መከተላቸው አይቀርምና።

ስለዚህ ዐለም ደስም ብሎ ደስ ላይላት (ለጊዜው ደስ ቢላትም ኋላ በድምር ውጤት ልታማርርህ) ከተፈጥሮህ ሚና፣ ከተፈጠርክበትም ዐላማ እና ከተሰጠህም ጸጋ ውጪ አትኑር። በዚህ ውሳኔህ የሚገጥሙህ ተግዳሮቶች ቢበዙም አንተን የሚያጠነክሩ፣ በራስመተማመንህን የሚጨምሩ፣ እውቀትንም የሚሰጡህ ናቸው።
ዐለም ዱቄትን ስትሻ ዐይኗ እያየ ግን የመፈጨቱን ኺደት አታደንቅም፣ አትሳተፍምም።

ማስታወሻ!
በጉዞህ ላይ የጀግኖች ብርቱ ክንዳቸው እንድትዘረጋልህ እንደፈለግከው ኹሉ፤ አንተም ሌሎች እንደፈለጉትና እንደቻልከው መጠን ዘርጋላቸው። የመምሕራችንን ወርቃማ ሕግ ልብ በል “እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ኹሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይኽ ነውና” ማቴ ምዕ7፦12።

ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *