የፍቺዎቻችን ምስጢር

ጀግናው ወንድሜ!

ዛሬ ዙሪያችንን ስለከበበን በአንዳንዶቻችንም ቤት በጭምጭምታ ስለሚሰማው ፍቺ መነሻ ምክንያት ላጫውትህ ፈቅጃለሁ። በዘመናችን ላሉ ሊዘረዘሩ ከሚችሉ የፍቺ ምክንያቶች ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው ምናልባትም ለሌሎቹም ምክንያቶች መንስዔ የሚኾነው የሚከተለው ነው።

እርሱም፦ ወንዶችም ኾነ ሴቶች ተፈጥሮ የሰጣቸውን የጾታ ልዩነት በእርሱም ያለውን ጸጋ በቅጡ አለማወቅ፣ አለማመንና አለማክበር ከዚህም የተነሳ አለመለማመድ(በኑሮ) ነው።

ወንድሜ እግዚአብሄር ሲፈጥርህ ወንድ ያደረገህ በበቂ ምክንያት ለዓላማ ነው። ስለዚህ በወንድነትህ የተሰጠህን ሚና እንደ ከንቱ፣ እንደ ርካሽ አንዳንዶችም እነሚዳርጉት እንደ ወንጀል አትቁጠረው።ባይኾን በወንድነትህ በራስህ ለራስህ፣ ለሚስትህ፣ ለልጆችህ፣ ለሚሕበረሰቡ፣ ለትውልድ ብሎም ለሃገር ስለምታበረክተውና ስለተፈጠርክበት ዓላማ ጠይቀህ ተረዳ።

አንተ ይኽንን ጠንቅቀህ ስታውቅና ስትኖረው ሚስትህም የራሷን ሚና ትያለች ልጆችህም እንደየ ጾታቸው እንዲሁ። ልብ አድርግ! ዓላማህ በተለየ፣ በታወቀና በተረዳ ሚና የሚሳካ እንጂ በጉራማይሌ ኑሮ አትደርስበትም።

ጀግናው ወንድሜ!
ደግሜ ደግሜ እነግርሃለሁ። አብዛኛዎቹ የመገናኛ ብዙኃን ኾኑ የሴታቆርቋዦቹ(Feminists) ምክር አትከተል። እነርሱ በገንዘብ የሚደጉሟቸውን ተቀማት ፈቃድና “ብንናገር ሰውን አያስከፋም” ያሉትን ከማስተላለፍ ውጪ “ጣፈጠም መረረም ትውልድ ይኼን የተፈጥሮ እውነት ማወቅ አለበት” ብለው ሐቁን አይነግሩህም።

ስለ ሰዎች(ስለሴት ልጅም ቢኾን) እኩልነት ፈጣሪህ የነገረህን ያላወቅህና፣ ያልተረዳህ የማትኖረውም ከኾነ ሌላ ማንም ከዚኽ ውጪ በኾነ ጥበብ ቢያስረዳህ አይደለም ሌላውን የራስህን ተፈጥሮ በመበደልና በማርከስ ትኖራለህ።

አንተ ተፈጥሮህን እወቅ ኹነውም፤ ለተፈጥሮህ ባዕድ የኾነ ጠባይም አትደብል። ይኽን ተፈጥሮህንም ኮትኩተው አበልጽገው። አንተ ራስህን ተፈጥሮህን በመኾን ሚስትህ ተፈጥሮዋን ታውቀው፣ ትኖረው፣ ታበለጽገውም ዘንድ አግዛት።
ይኽ ሳይኾን ግን ለአንድ ዓላማ በተለያየ ጾታ ለየቅልም በኾነ ሚና ተፈጥራችሁ ሳለ “አውቄያለሁ” ብለህ ይኽን ልዩነት ብትንደው አንድነትህ አይጸናም።

ጀግናው ወንድሜ!
ጀግንነት ውስጥህ ነው፣ ተፈጥሮህ ነው፣ ፈልገህ አስነሳው፣ አታስተኛው፣ ግለጸውም። እመነኝ የሴት ልጅ ልብ በፍቅርሽ ላብድ ነው እያለ ለሚነፋረቅ ወንድ ሳይኾን በጀግንነትና በግርማ ሞገስሊወስዳት ለሚያኮበኩብ ወንድ ነው የሚሸነፈው።

ጀግንነት በሥራህ፣ ጀግንነት በቃልህ(ታማኝነት) ጀግንነት በአካል ብቃትህ፣ ጀግንነት በአመራርህ፣ ጀግንነት በኃላፊነትህ ይኹን። በፈጣሪህ ከተሰጠህ በጾታህም ተገልጾ ከተቀመጠው ሚናህ ውጪ ወደ ዓላማህ የምትደርስበት አቋራጭ መንገድ የለም። ቢኖር ግን እርሱ ያንተን ተፈጥሮ የሚያሳጣ፣ በሴቷም ያለህን መከበርና መወደድ የሚያሳጣህ ነው።

የምዕራቡ ዓለም ዛሬ በሴቶች የእኩልነት ዜማ የጀመረውን ወደ ጾታ የለሽ ትውልድ ወደ ማፍራት አሳድጎታል። ይኽንንም የምስራቁ ዓለም አፍሪካን ጨምሮ እንዲከተሉት ተፍ ተፍ ይላሉ። የእኔና ያንተ እህቶች ደግሞ ይኽቺ ከንቱና ክፉ ዓለም የደገሰችላቸውን አያውቁ ምክንያት እየፈለገች ስትሾማቸው ስትሸልማቸውና ስትልካቸው ለሴቶች መብት እንቆማለን ብለው ፈቃዷን ይፈጽማሉ።

ወንዱም ሳይመረምር ዐዲስ አስተሳሰብ ዐዲስም እይታ አገኘሁ ብሎ የእነርሱኑ ጩኸት መልሶ ያስተጋባል። የትዳሩ መሸርሸር፣ የልጆቹን ከስርዓት መውጣት፣ የትውልዱን መረን መኾን የራሱንም ከተፈጥሮው በእጅጉ የራቀ ኑሮ ችላ ብሎ ለዓለም አስረሽ ምቺው ራሱንም ኾነ ቤተሰቡን ይገብራል።

ጀግናው ወንድሜ!
ጀግናው የምልህ በጀግንነትህ አንዳችም ጥርጥር ስለሌለኝ፤ ወንድሜ የምልህም የትዳራችን፣ የቤተሰባችን፣ ብሎም የሀገራችን ሕልውና የሚያሳስበን ውድ ወዳጅ ነህና ነው።

ልንገርህ!
የተፈጥሮ ሕግ እንጂ በጭራሽ ፍርኃት አይግዛህ። ከምስኪንነት ወጥቼ አንተ የምትለውን አባወራ ብኾን ሚስቴ ትፈታኛለች፣ ልጆቼም ይጠሉኛል ማንስ ይጦረኛል አትበል። ፈጣሪ በምክንያት በዓላማ የፈጠረህ ወንድ ነህ። በተፈጥሮ ሕግ ደግሞ አንተ ወንዳወንድ ወንድ እየኾንክ ስትሄድ ሴታሴቷን ሚስትህን ትወዳታለህ እርሷም ታከብርሃለች።

በጭራሽ እንዳትደለል! እኔ ከኖርኩበት ከተሳሳትኩበት፣ በጥናትም ካመሳከርኩት ይኽን አልኩህ። ለምን? አምላክህን እንዳታሳዝነው፤ አንተም እንዳትጎዳብኝ፤ እወድሃለሁምና ነው።

ለነገዎቹ ልጆቻችን በሴታቆርቋዦቹ(Feminists) የተደገሰውን አንተ እና እኔ የምናደንቃት Celine Dion እንዲህ ታስተዋውቀዋለች። ከቻልክም በCNN ላይ የሰጠችውን አስተያየት ተመልከት።

ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *