ደረጃህን ከፍ አድርግ

ሳተናው!
አንተ ጀግና ዘወትር ራስህን ለማሻሻል በእውቀት፣ በመንፈሳዊ ልቀት፣ እንዲሁም በአካል ብቃት ለማሳደግ የምትጥር ትጉህ ወንድሜ እንደኾንክ አልጠራጠርም!

ምንጊዜም እንደሰው በሰውነታችን ማደግ መለውጥ አለብን ስልህ እነዚህን ሦስቱን አትርሳ። ከእነዚህ ውጪ ያሉት እድገቶችህ ኹሉ ሰውነትህን ሳትረዳውና ሳታሳድገው የሚመጡ ከኾኑ አንተን ከመጥቀም ይልቅ የሚጎዱህ ይኾናሉ።

ስለዚህም አእምሮኣዊ እውቀትህ ምንግዜም ራስህን ለማሳደግ ራስህን ለማስተማርና ለማሳወቅ ጣር ይኽን ስታደርግ ግን መለኪያህን ሌሎች አታድርግ። ራስህን ማስተማር ማሳወቅ የዘወትር ሥራህና ልማድህ ኾኖ መቀጠል ስላለበት እንጂ።

ራስህን በእውቀት የመገንባቱ የማሳደጉ ሥራና ግቡ የአንድ ሙያ ባለቤት፣ የአንድ የእውቅና ጥግ ላይ መድረስም ብቻ መኾን የለበትም። “ዶ/ር፣ ኢ/ር” መኾንህ አንተ እኽል ውሃ ታገኝባቸው ዘንድ ቢያግዙህ እንጂ እንደ ሰውነትህ ተፈጥሮህን ለማወቅ፣ ከሌሎች ጋር የሚኖርህንም መስተጋብር ለመረዳትና ለማሳደግ አይጠቅሙህም።

አንተ ግን እስከ ዕለተ ሞትህ ድረስ ራስህን በግድ ሳይኾን በውድ ግን ደግሞ ጨክነህ አስተምር። መኖርህን በመማር፣ የተማርከውን በመኖርና በእርሱ ላይም በማደግ አትም።

ተፈጥሮህን፣ አካባቢህን፣ ሀገርህን እወቅ። ይኽን የምታውቀውንም እውቀት ዘወትር አሳድግ። ወዳጄ ምዕራባውያን ሀገራችን ልዩ እንደኾነችና ብዙ ያልተነኩ ኃብታት ባለቤትም እንደኾነች ያውቃሉ። ምናልባትም በዚህ ዘመን ካለነው ትውልድ የበለጠ ቋንቋችንን፣ ባሕላችንን፣ መልክዓ ምድራዊ ንብረታችንንና ተፈጥሮኣዊ ኃብቶቻችንን ያጠናሉ እነርሱንም ጠንቅቀው ያውቃሉ።

በመንፈሳዊ ሕይወትህም ዘወትር ማደግህን እርግጠኛ ኹን። ስለ ፈጣሪህ፣ ስለትዕዛዛቱ እንዴት ልትኖር እንዳለኽና ለምን እንደምትኖር ተረዳ። ዘወትርም በቃሉ ውስጥ እየተሠራህ እደግ በምግባርህም ያወቅከውን እና ያመንከውን በኑሮህ(በድርጊት) አትመው። እምነትህ ያለመግባር ሙት ነውና።

በመንፈሳዊ ሕይወትህ በተግባር መፈተንን ውደድ። በተግባር ስትፈተን ግን ችግሮችን የምትፈታበት ብቃት እንደ ልጅነትህ ከኾነ አኹንም ባለህበት የምትረግጥ “ከርሞ ጥጃ” መኾንህን አትዘንጋ። አልያም “መንፈሳዊ ነኝ” እያልክ ነገር ግን አንተን ከሚያጠነክሩህ የትኞቹም ፈተናዎች የምትሸሽ ከኾነ ዛሬም በምናባዊ ዓለም የምትዋኝ የዋህ ከልጅነትህም ፈቀቅ ማለት የማትደፍር ምስኪን መኾንህን ያሳያል።

ሳተናው!
አንተን ከልማድ መንፈሳዊነት የሚለይህ የሚያነጥርህ እሳት ፈተና ነው። ፈተና ስትፈተን ዐይንህን በፈታኙ፣ በፈተናው እና በጉዳቱ ላይ ከማሳረፍ ይልቅ ከፈተናው ስለምታገኘው ጸጋ አስብ። ፈተናን ሸሽቶ ከፈተና ነጻ ሕይወት የኖረ የለምና መንፈሳዊ ስንቅህን በደንብ ሸክፍ፤ ዘወትርም አሳድገው።

ሰውነትህን በአግባቡ ጠብቅ፤ ውፍረት ምቾት ቅጥነትም የመንፈሳዊነት መገለጫ አይኾኑም። ጀግናው! ይልቅስ አካላዊ ብቃትክን በጤንነትና በስፖርት ጠብቅ። የትኛውንም ሱሰኝነት፣ ሴሰኝነት፣ ሰነፍነት፣ እንቅልፋምነት፣ ስግብግብነትን አስወግድ እነዚህ ስጋህን ብቻ ሳይኾን መንፈስህንም የማቆሸሽና የማጎሳቆል አቅም አላቸውና።

ሳተናው!
አባቶቻችን የሥራ ሰዎች ነበሩ ጸሎተኛም ጭምር፤ ከዚኽም የተነሳ በርካታ በሰዎች ዘንድ ይቻላሉ ተብለው የማይታሰቡ ሥራዎችን ሠርተውና አውርሰውን አልፈዋል። ልብ አድርግ! መሥራት አንድ ብቃት ቢኾንም ሳይበረዝ፣ ሳይዘረፍና ሳይከለስ ማቅረብ መስዋትነትን እንዲሻ።

“ይኼ እንዴት ተቻላቸው?” ብትለኝ ከግዑዙ ዐለም በፊት፣ ለራሳቸው ኃብትና ንብረት ከማካበታቸው በፊት ፍጥረታቸውን ተረድተው፣ እንደፍጥረታቸው ለራሳቸው ከፍተኛ ግምት ሰጥተው፣ ያን ደረጃ ለመጠበቅና ለማሳደግም ይጥሩ ስለነበር ነው። ስብዕናቸውን፣ በሥላሴ አርኣያ መፈጠራቸውን፣ ከሌላው ፍጥረት በላይ መኾናቸውን(መሰልጠናቸው) ስለሚያውቁና እርሱንም ዘወትር መኮትኮትና ማሳደግ በሌላው ኹሉ ማትረፍና መትረፍረፍ እንደኾነ ስለገባቸው ነው።

ከዚህም የተነሳ ለሰነፍ ሰው፣ ለኢስነምግባራዊ ሰው፣ ለኢኣማኒ …. ሰው በሕብረተሰባቸው መሓል የተናቀ ቦታ ሲኖራቸው በተቃራኒው ደግሞ ለጎበዝ ሰው፣ ለግብረገብ እና እምነቱ ታላቅ ሥራን ለሚሠራ ሰው ደግሞ ትልቅና የተከበረ ቦታ ነበራቸው። በእኛ ዘመን ግን እንዴት እንደኾነ አይጠፋህም፤ የተገላቢጦሽ ዘራፊዎች ሲሾሙ፣ ሲሸለሙ ሲወደሱ፣ መንግስትም ከለላ ሲሰጣቸው …..እህህህህም።

ሳተናው!

እንዲህ ልጠቅልልልህ፦

1ኛ ለራስህ ከፍ ያለ ደረጃ ይኑርህ(ቀለህ አትገኝ)፤ ለታላቅ ዓላማ በምክንያት ተፈጥረሃልና ራስህን የምትለካበት ከፍ ያለ ደረጃ ይኑርህ። በምንም ዓይነት መልኩ የእንደ ነገሩ ኑሮን አትታገስ፤ ከስንፍናም የተነሳ አማካይ ማንነት አትያዝ። ከአባቶችህ ልቀህ፣ ባቆዩልህ ላይ ጨምረህ መገኘት አለብህ!!! (ልብ አድርግ! ብትችል አላልኩህም ትችላለህና!!!)።

2ኛ አንተነትህ የእነዚህ የሦስቱ(የአእምሮ፣ የመንፈስና የአካል) ጥምር ውጤት ነውና ለሦስቱም ደረጃን ሰቅለህ በእውቀት ታግዘህ ኮትኩተህ አሳድጋቸው።

…ይቆየን
ሳምንት ብንኖር
አንተ ገንዘብ ባደረግከው ደረጃን ከፍ አድርጎ በተሻለ ማንነት መመላለስን ለሚስትህና ለልጆችህ እንዴት እንደምታጋባ እንደምታወርሳቸውም እናያለን።

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *