ዱርየው ወንድ(bad boy)

እኛ ባነሳነው ዐውደ ንባብ(context) ዱርዬ ወንድ የምንለው ለሚኖርበት ማሕበረሰብ እሴት፣ ወግ፣ ኃይማኖት የማይጨነቅ አፈንጋጭ የኾነውን ነው።

*** በጭራሽ ግን ማጅራት መቺን፣ አስገድዶ ደፋሪን፣ ሕገ ወጥን፣ ተደባዳቢ፣ … አያካትትም።***

ዱርየው የሚፈልገውን ነገር በትሕትና፣ በጥያቄ አስፈቅዶ ሳይኾን በአስገዳጅ ብልጠት አልያም በኃይል መውሰድን ይመርጣል፣ ያውቅበታልም። ይሉኝታ፣ ትሕትና፣ አክብሮት እርሱ ጋር ቦታ የሌላቸው ናቸው።አንድን ነገር ማግኘት ካሰበው እርሱን ለማግኘት ልምምጥ፣ ድርድር ይሉኝታ ሳይኖርበት የእርሱ ያደርገዋል።

ይኹንና ዱርዬዎች በአፍኣ ወይም በውጭ በሚታየው ሰውነታቸው ሽቅርቅር ባይሉም ሳቢ ተክለሰውነት አላቸው። በራስ መተማመንን የተግናጸፉ ቁመናንና ግርማ ሞገስን የተላበሰ ትከሻ አላቸው፤ እንዲኖራቸውም ይጥራሉ።

በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ፈታ ያሉ መዝናናትን የሚወዱ የሚያውቁበትም ናቸው። ታዲያ ምንም እንኳ ዱርዬ ቢኾኑም ይሄ ጨዋታ አዋቂነታቸው በሴቶች በሕቡዕ(በድብቅ) ያስወድዳቸዋል። ምስኪኑ ማፍቀሩን ለመናገር ዓመት ሲታሽ ዱርዬው ግን በቀላሉ የሚጨልጣት ጽዋ ናት።

ለዱርዬው ወንድ ትዳር፣ ቤተሰብ፣ ልጆች፣ ትውልድ ቦታ የላቸውም፤ ያቺን ሲጎትት ይኽቺን ሲገፈትር ይኖራል እንጂ። በእርግጥ አኹን አኹን “ወሲባዊ ጥቃቶችን ለመከላከል” በሚል ሕጎች እየጠበቁ ከመምጣታቸው አንፃር ዱርዬውን ወንድ ከእይታ ሰውሮታል።አብዛኞቹም ከዱርዬነት ወደ ሴት-አውልነት ተሸጋግረዋል።

አንተ የምወድህ ወንድሜ ጣትህን ቀስረህ በግልም ይኹን በማሕበር ተደራጅተህ ዱርዬውን ወንድ ስላወገዝክ አንተን አባወራ አያሰኝህም። የሴቶቻችንንም ልብ ከመሸፈት አይመልሰውም። አልያም ብዙዎች እንደሚሉት “ራሳችንን ሰጥተናቸዋል ወርቅ አይደለም እኛን አንጥፈንላቸዋል ነገር ግን ተራምደውን ሳይኾን ረግጠውን ዱርዬው ጋር በመሄዳቸው ልባችን ተሰብሯል” ትላለህን? አንተስ የቱ ጋር ነህ?

አኹን በብዛት የሚገኘው ወንድ ምስኪን ነው። አይደለኹም ሊል ይችላል አብዛኛው ግን ምስኪን ነው። ታማኝነቱ፣ ራሱን ጥሎ ለሚስቱ እና ለልጆቹ መልፋቱ ያስወድደዋል። በተለይ ደግሞ ለሚስቱ ስህተቶች ኹሉ ድንበር የለሽ ይቅርታው ወሰን የለሽ ምሕረቱ ያስወድደዋል። “ጥሩ አባት”ም ነው። ግን…ግን.. ዘመነኛ ነኝ ሲል መግባባትን በመነጋገር እንጂ በተፈጥሮኣዊ ስሜት ስለማይረዳ ከሚስቱ የተቆራረጠ (እያለ የሌለ) ነው።

ሴት አውሉ አንደበቱ ማር ነው፣እትት ሲል ቅቤ ያቀልጣል፣ ወሬው ቀልብን ይገዛል፣ ቃሉ በጆሮ ኩልል ሲል ስሜት ይኮረኩራል። ሙገሳው፣ ቁልምጫው፣ እንክብካቤው አይጣል ነው ከምስኪኑም በብዙ ይሻላል። ግን.. ግን… የኹሉም ነው። አንዷን በግራው ሌላዋን በቀኙ፣ አንዷን በቤት ሌላዋን በደጁ ያደርጋልና ከእርሱ ጋር ትዳርና ቤተሰብ የማይታሰቡ ናቸው።

ዱርዬው ወንድ ግን በተለይ ሞገደኛ ለኾነው ስሜቷ፣ እንደ ማዕበልም ለሚንጣት አምሮቷ ኹነኛ እና ተስተካካይ ትይዩም የኾነ ወንድ ነው። ተፈጥሮኣዊ የኾነውን፣ እውቀት-አልቦውን የልቦናዋን መሻት የሚያውቅ እንጂ የማይጠይቅ፣ የሚፈጽም እንጂ የማያስፈቅድ ነው። ልቧ የሚረታበትን በራስ መተማመን፣ድፍረት፣ ቆራጥነት …. የታጠቀ ነው። አይደለም ይዟት ስታየው አልያም ድምጹን ሰትሰማው ገና ልብ ምቷ ይጨምራል። የማትቋቋመው ስበት ወደ እርሱ ይጠራታልና ግን…. ግን… ምን ያደርጋል ዱርዬ ነው።

ወንድሜ? ሴቶቻችን ለምንድነው “የሚያከብራቸውን፣ የሚንከባከባቸውን፣ የሚወዳቸውን” ፣ “የልጆቻቸውን አባት”፣ “የሞላ ቤታቸውን ትተው ብር ብለው ዱርዬው ጋር የሚሄዱት?” “ምንስ ይሻላል?” ትላለህን? እንግዲያውስ ጣፈጠህም መረረህም ና ልንገርህ…… ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *