ድንበር፣ ወሰን ይኑርህ!

ሳተናው!

ትዳር የወንድና የሴት አንድነት ነው ሲባል ውሕደት እንጂ ቅልቅል አይደለም። አንድነታችሁ ከመዋሃዳችሁ ቢመጣ እንጂ በቅልቅል አይኾንም።

አንተ ሚስት ስታገባ ብትዋሃድ እንጂ አትቀላቀልም። መቀላቀል በስጋችንም ኾነ በስሜት ፣ በአስተሳሰብ፣ በስነልቦናም አይታሰብም አይኾንምና። መቀላቀል ከቅልቅል በፊት የነበረን ተፈጥሮኣዊ ባሕርይ፣ ስጋዊ ጠባይ፣ የልብ መሻት እርግፍ አድርጎ ትቶ በተቀላቃዩ ባሕርይ ጠፍቶና እርሱንም አጥፍቶ ሌላ ዐዲስ ማንነት መያዝ ነው።

ትዳር ተጋቢዎች ሁለት ኾነው ሳለ በውሕደት ቀድሞውኑ የነበራቸውን ስብዕና ይዘው አንድነታቸው ልዩነታቸውን ሳያጠፋ ልዩነታቸውም አንድነታቸውን ሳይከለክል አንድ የሚኾኑበት ሚስጥር ነው። ከዚህም ትዳር ልጅ ቢወለድ እናትንም አባትንም መስሎ በአንድ አካል ይገኛል።

ይኹን እንጂ ዛሬ ዛሬ ትዳርን ስኬታማ እንዳይኾን ከሚያደርጉት ነገሮች ውስጥ ዋነኛው ሁለቱ አካላት ልዩነታቸው(ተቃራኒ ዋልታነታቸው) የማይታይና ድንበራቸውም የፈረሰ መኾኑ ነው።

(የሁለቱ ተፈጥሮኣዊ እና ተቃራኒ የኾነው ዋልታ ረገጥነት፦ እርሱ ፍጹም ወንድ እርሷ ፍጹም ሴት መኾን ትዳርን በጠረጴዛ ዙሪያ ከመምራት ይልቅ ስኬታማ ያደርጋል አንድ ቀን እናወራበታለን)። ይኽም ማለት ፍቅረኛሞች በተሳሳተ ግንዛቤ ድንበር የለሽነትን የመወደዳቸው ልክ የፍቅራቸውም ጣሪያ ያደርጉታል። ተፈጥሮኣዊው እውነታ ግን ከዚህ ፍጹም የራቀ ነው።

ሳተናው! ከሚስትህ የተለየ፣ የታወቀ እና የሚታይ ድንበር ሲኖርህ ለሠራኸው ሥራ ኃላፊነት መውሰድ ትችላለህ። አንተ በሠራኸው ሚስትህ እርሷም በሠራችው አንተ ተጠያቂ የማትኾኑት ከሰበበኝነትም የምትርቁት ተለይቶ የተከለለ የታወቀና የተረዳ ድንበር ሲኖራችሁ ነው።

ምስኪንን ከሚገልጹት ጠባዮቹ አንዱ ድንበር የለሽነቱ ነው። ይኽ ድንበር የለሽነቱ ደግሞ መጠን ካለፈ አጥብቆ ፈላጊነቱ እና አጥብቆ በፈለገው ነገር ላይ ካ፥ለ ጥገኝነቱ ይመነጫል። “ሴት እፈልጋለሁ” (ተፈጥሮኣዊ ነው)፣ “ሴት ታስፈልገኛለች”?፣ “እከሊትን የእኔ ብቻ ነች”?፣ “ካለ እርሷ መኖር አልችልም”?፣ “እርሷን ካጣሁ ራሴን አጣለሁ”?…..።

ድንበር ካለኝ ፍቅር መመሥረት አልችልም ሚስቴን፣ ትዳሬን፣ ልጆቼን ወዳጆቼን አጣለሁ ይላል። በዚህ አጥብቆ ፈላጊነቱ እና በእነዚህ ሰዎች ላይ ባለው ጥገኝነቱ የተነሳ የእርሱን አቋም፣ ፍላጎት፣ ዝንባሌ የሚገልጽ ድንበር የለውም። ስለዚህም የራሱን ስሕተት አውቀውበት እንዳይሸሹት ሲደብቅ ሌሎች ለሠሩት በተለይም የሚስቱን ልወደድ ሲል ኃላፊነት ይወስዳል።

ስነስርዓትና ድንበር

ሳተናው!
አንዲት ሀገር የምትደዳርበት ሕግ አለኝ ስትል ሕጓ ተፈጻሚ የሚኾንበትን የግዛት ጠረፍ ድንበር አድርጋ ነው። ድንበር ከሌላት ሕጓም (ስርዓቷም) ተፈጻሚነቱ የላላ እንደውም የተናቀ ነው። ሌሎች ሀገራትም ከዚህች ሀገር ጋር የጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ግንኙነት መመሥረት ይቸግራቸዋል። ይሉንስ የማንም ወራሪ መጠቀሚያ መኾኗ የማይቀር ነው።

አንተን በሚስትህ ዘንድ የሚያስከብርህ ግልጽ አድርገህ የምታስቀምጠው ስነስርዓትህ ሲኾን እርሱም የታወቀና የተረዳ ድንበር ሊኖረው ይገባል፤ ያስወድድሃልም። ጊዜህ፣ ገንዘብህ፣ ደግነትህ፣ ትዕግስትህ፣ ቸርነትህ፣ ይቅርታህ፣ አንደበትህ፣ ስልጣንህ፣ ተጠያቂነትህ.. …እና የመሳሉት በሚስትህ ዘንድ የታወቀ መጠን የሚታይም ድንበር ሊኖራቸው ይገባል።

ይኽ ካልኾነ ግን ለሠራኸው ሥራ ኃላፊነት የማትወስድ ደካማ፣ ሌሎች በሠሩት የምትወቀስ ምስኪን ትኾናለህ። ከዚህም አልፎ ስርዓትህ የማይከበር መብትህም የማይጠበቅ የተናቅክም ትኾናለህ።

ትዳርህንም ኾነ ሚስትህን ማትረፍ ከፈለግክ እርሷ በድንበሯ ውስጥ ልትወስደው የሚገባትን ተጠያቂነት አንተ መውሰድ የለብክም። እርሷ ከድንበር የለሽነት እና ከጥገኝነት ተነስታ ስሕተቶቿን ባንተ ብታሳብብ አንተ ግን ፈርጠም ብለህ “የራስሽን ስሕተት ማንም ላይ አታድርጊ ይልቁንስ በሥራሽ ውጪ” ልትላት ይገባል። ይኽን ስታደርግ እውነተኛ መውደድህ ሲገለጽ ሚስትህም ከሰበበኝነትም እንድትርቅ ያስችላታል።

አስረጅ፦ ብዙውን ጊዜ ሴቶች(እህት፣ እናት፣ ሚስት) ከጎረቤት ከወዳጅ… ይጣሉና ባሎቻቸው ወይም ልጆቻቸው(በተለይ ምስኪን ባልና ምስኪን ወንድ ልጅ) የጸቡን ኃላፊነት ወስደው ይቅርታ ይጠይቃሉ፤ አልያም ተደርበው ይጣላሉ።

ጨከን ብሎ “ችግሩ ያንቺ ነው፤ ይኼን ይኼን ዓመልሽን ብታስተካክይ ጥሩ ነው ፤ ሰዎችን ከመሸሽና በእነርሱም ከማሳበብ ማሕበራዊ ኑሮውን እወቂበት…” የሚል ደፋር በተናገረውም የሚጸና ወንድ፣ ባል፣ ልጅ ብዙም አይገኝም።

እንዲህ ተናግሮ እናቱን፣ እህቱን፣ ሚስቱን “ከሚያጣ” የፈጠረቻቸውን ችግሮች እየሸፈነ፣ እየተጋፈጠ መኖርን ይመርጣል። በዚህም እርሷ(እናቱ፣ እህቱ፣ ሚስቱ) ለእኔ ያላት ፍቅር ይጨምራል ትወደኛለችም ብሎ ያስባል።

እዚኽ ጋር ሁለት ነገሮችን ማስተዋል እንችላለን፦

፩ኛ -መታረም በሚገባው ስነምግባር ችግር እየፈጠርን ሳለ ዓመላችንን ከማረም ይልቅ ለችግሩ ብቻ መፍትሔ ለዚያውም ከሰው መፈለግ፤
-ይኽም በራሳቸን ድንበር ውስጥ ላለ ችግር ሌሎችን ለመፍትሔ መጋበዝ
-በዚኽም ከሌሎች ውለታን ሰንጠብቅ ስናጣ ደግሞ መከፋት ይመጣል።(በሴቶች ይልጡን ይታያል)

፪ኛ ሰዎች በተለይ የምንወዳቸው የቅርብ ሰዎች ሊታረም የሚገባ ዐመል እያላቸው እርሱን ትተን በእርሱ ምክንያት የመጣ ችግራቸውን መፍትሔ እንፈልጋለን። ይኼም እኛ ከምንጠየቅበት ድንበር ውጪ ወስዶ በሌሎች የማንነት ክበብ ውስጥ ያስገባናል። በዚኽም ተወዳጅነት ተፈቃሪነትን ለማትረፍ እንሞክራለን (የብዙ ምስኪን ወንዶቸ መለያ ነው)።

ሳተናው!

ለሰው(ለሚሰትህም ቢኾን)የምትሰጠው ጊዜህ፣ ደግነትህ፣ ገንዘብህ፣ ትዕግስትህ፣ ይቅርታህ ገደብ ሊኖረው ይገባል። ይኸንንም ለሚስትህ በግልጽ ማሳወቅ አለብህ።

እንጂማ እርሷን “ላለማጣት” እያልክ ለፍላጎትህ ይሉኝታ፣ ላልበደልከው ይቅርታ፣ ላልሠራኸው ስሞታን የምታስተናግድ ከኾነ አተርፋለሁ ያልከውን ሰው ታጣዋለህ፣ ሚስትህንም(ትዳርህንም) እንዲሁ።

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *