ድንበር የለሹ አፍቃሪ

 

ምስኪን-ወንድ የእርሱ ለሆኑ ስሜቶች፣ ፍላጎቶች ፣ድርጊቶች፣ ኃሳቦች፣ ሰብዓዊ መብቶች ዓላማዎች አጥር፣ ቅጥር ፣ድንበር ወሰን አያበጅላቸውም፤ ቢያበጅላቸውም በቀላሉ መናድ የሚችሉ የእምቧይ ካቦች ናቸው።
ፍላጎቴ፣ ስሜቴ፣ ኃሳቤ ይሄ ነው ብሎ መናገርም ሆነ ማድረግ ሰውን ቅር የሚያሰኝበት በተለይም የእኔ የሚላት ሚስቱን የሚያስከፋበት ይመስለዋል እውነታው ግን በተቃራኒው ሆኖ ሳለ።ተወዳጅነትም የሚያተርፍለት እየመሠለው የራሱን ስሜቶች ፍላጎቶች ይጨቁናል፤ ችግሮች ፈተናዎች ሲመጡም የበለጠ የእርሱን እየጨቆነ የእርሷን ስሜት ለመፈጸም ይደክማል በዚህም ከድጡ ወደ ማጡ ይወርዳል።

ይህን የምስኪን-ወንድ ጸባይ ተፈጥሮአዊ እና መሠረታዊ በሆነው ከሚስቱ ጋር ባለው የወሲብ ግንኙነት ላይ ይበልጥ መታዘብ ይቻላል።በብዙ ወንዶችም ላይ የመኝታቤት አካባቢ ምስኪንነት በስፋት ይታያል። ለብዙ ወንዶች ከሚስታቸው ጋር ለሚፈጽሙት የወሲብ ግንኙነት በሚስታቸው ቸርነት እና ለጋስነት (መሆን የማይገባው) ላይ የተመሠረተ ነው(ራሳችሁን እና ጓደኞቻችሁን ታዘቡ)። ይህን የዓለም ሠራዒ፣ ዘዋሪ ፣አስተዳዳሪ ነን ብለው የሚፈነጬ ኃያላን አገሮች ምስኪኖቹ ላይ ከሚጥሉት ማዕቀብ ጋር አመሳስለዋለሁ።

ምስኪኖቹ ሃገሮች በተፈጥሮ ያገኙትን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ፣ የመነገድ መብታቸውን ተነፍገው እናድርገው ሲሉም በዛቻ እና ማስፈራሪያ ተሳቀው ይኖራሉ። ኑሮ ሲከብድባቸውም አቤቱታ እና ልምምጥ ይጀምራሉ በዚህን ጊዜ ነፍሳቸውን መታደግ የሚያስችል በጊዜ እና በቦታ የተገደበ የእርዳታ ቀጠና (humanitarian corridor)ይፈቀድላቸዋል። እነዛ በጭንቅ ያሉ ሃገራትም ተቻኩለው የፈለጉትን አይነትና መጠን ቢፈቀድም ባይፈቀድም አግበስብሰው እና አጭበርብረው ያስገባሉ በዚህ የሚበሳጬት ኃያላንም ከበፊቱ የከፋ ማዕቀብ ይጥሉባቸዋል።

ምስኪኑ-ባልም ብዙውን ጊዜ ወሲብ(ተራክቦ)የሚፈጽመው በሚስቱ ቸርነት ነው።ትናንት ደከመኝ ዛሬ አመመኝ፣ነገ ደበረኝ፣ ከነገወዲያ ሥራ አለኝ፣ከዛ ወዲያ ጥናት ላይ ነኝ፣ከዚያ ወዲያ ፀሎትላይ ነኝ………በሚባሉ በጨዋ ደንብ በሚቀርቡ በርካታ ማዕቀቦች ተከቦ በባልነቱ የሚገባውን በልምምጥ፣ በስጦታ በሽልማት ይጠይቃል። እርሷም የነፍስ አድን ስራ ይመስል አለፍ አለፍ ብላ ትፈቅድለታለች። እርሱ ግን ይህችን አጋጣሚ በጉጉት ሲጠባበቃት ነበርና መልሳ ሳትወስድበት ተቻኩሎ ይጠቀምባታል። በዚህም ለጊዜው ፍላጎቱ ተንፈስ ይበልለት እንጂ በቦታው ግን ሌላ ጥልቅ የፍላጎት እና የጉጉት ሸለቆ ተክሎበት ይሄዳል። እርሷ ደግሞ በጥድፊያ እና በችኮላ የመጣው ምስኪን መጣ ስትል ሲቀር፣ ያዘኝ ስትል ሲለቅ፣ ጀመረ ስትል ሲጨርስ ለዚሁ ነው ያስቸገረኝ ብላ ከበፊቱ የባሰ ማዕቀብ ትጥልበታለች።

ለአባወራው ግን እንዲህ አይደለም ምን ጊዜም ሚስቱን በሥራዋ ማመስገን ውበቷን ማቆለጳጰስ ፍቅሩን እና ለእርሷ ያለውን ስሜት መግለጽ ያስደስተዋል።የእርሱንም በግልጽ በወሰን በድንበር የታጠረ ፍላጎቱን ስሜቱንም ያሳውቃል፤ ሲፈልግ ያገኛል፤ሲያገኝም ልኩን ፣መጠኑን፣ጥራቱን የጠበቀ ሥራ ይሠራል፤ሳይፈልግም አይፈልግም፤እንደምስኪኑ ስፍስፍ ወይም እንደሱሰኛ ጥድፍ አይልም።ከምንም በላይ የእርሷን ሴትነት በሚሞላ እና በሚያሟላ ወንድነት ይንከባከባታል እርሷም በእንክብካቤው እርፍ ባለው ማንነቷ ትንከባከበዋለች በልቶ የሚጠግብ ጠጥቶ የሚረካ አይመስላትም እንጂ ደግሞ የምን ማዕቀብ።

በተለይም በተራክቦ ጉዳይ የእርሱ ብቻ በሆነ እና እርሷን ውዱን ብቻ በሚያሳፍርበት የእርካታ መንኮራኩር(spaceship) ጭኖ ከአልጋ ላይ ነጥቆ፣ ጣሪያን ሰንጥቆ፣ ደመናን ጥሶ፣ ዓለሟን አሳይቶ የሚመልሳት መጀመሩንም መጨረሱንም የሚያቅበት ጥበበኛ ሆኖ(ጥበቡ ብዙ ሴት ከማወቅ የመጣ ሳይሆን የወንድ እና የሴትን ተፈጥሮ ከመረዳት የተቀዳ ነው)የምን ማዕቀብ ያርፍበታል። ፈልጎ አይከለከልም ሳይፈልግም የሚያስገድደው የለም፤ይህ የእርሱ የአባወራው ደፈረ፣ ጠፈር፣ ድንበር፣ አጥር፣ ቅጥር ነው እርሱም የማይንደው ለማንምም የመናድ እድል የማይሰጥበት።

ይህ ለሚስቱ አንድም ፍላጎቱን እና የፍላጎቱን ወሰን የሚያውቅ እና የወሰነ ባልን ያሳያታል። አንድም ደግሞ በሁለቱ መካከል ከመጠባበቅ ይልቅ መከባበርን ይፈጥራል አልያ ግን ያላከበሩትን ማንነት ይዞ አክብሩኝ ማለት ይሆናል። ይሄም ወደ ሌላው የአባወራው ስብዕና ይወስደናል እርሱም፦ራስን እና ወሰንን ማክበር እና ማስከበር እነዚህን ከማያከብሩ ሰዎች ጋርም ጊዜን አለማጥፋት……..ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *