ፈተናህንና አብሮት የሚመጣውን አደጋ ፊት ለፊት ተጋፈጥ

ወንድሜ በአባወራነት ጉዞህ ላይ በአካል፣ በመንፈስም ኾነ በአእምሮህ እያደግህ መኼድ ትፈልጋለህን? እንግዲያውስ በቁርጥ አቋምህ በእውነተኛና ተፈጥሮኣዊ እውቀትህ በወሰንከው መንገድ የሚገጥምህን ፈተና ፊትለፊት ተጋፈጥ።

ከፈተና በራቅህና ከአደጋ በሸሸህ ቁጥር በነፃነትና በደስታ የምትኖር ይመስልሃል። እውነታው ግን ከዚህ በጣም የራቀ ነው።

ጸጋ እንዲበዛልህ፣ ጥበብ እንዲጨመርልህ፣ እውነትንም ልትገበይ ከፈቀድህ ፈተናን አትፍራ። ያንተ እንደኾነችና ልትጠጣትም የተቆረጠች ጽዋ እስከኾነች ድረስ ተነስተህ አደግድገህ ተቀበላት። እርሷን በመጋፈጥ የሚከተሉትም የአደጋ ስጋቶች ላንተ ነፃነትንና በራስ መተማመንን ያሸምቱሃል።

ወንድሜ መንፈሳዊ ሕይወትህ በጸጋው እያደገ፣ ዐለማዊ እውቀትህም እውነተኛ ሲኾን በዐለም ላይ የሚያስፈራህ ነገር ወደ ኢምንትነት ይጠጋል(ምንም ነገር ወደ አለመፍራት)። ስለኾነም ፈተና ሲመጣብህ ነብር ያየ ይመስል አትደነብርም።

አደጋ(ፈልገህ የምታመጣው ሳይኾን አንተ ቁርጥ ሀሳብ ስትይዝ የሚመጣ) በሞላበት የሕይወት መስክ ውስጥም ከአደጋው ባሻገር ስላለው ድል እያሰብክ ዐላማህን በልቦናህ ሰሌዳ ስለህ በከፍተኛ የራስ መተማመን ትገባለህ ደግሞም ትሻገራለህ።

በተለይ ምስኪን ስንኾን በሕይወታችን ውስጥ የሚገጥመንን ግጭት፣ ተቀባይነት ማጣትን፣ የአደጋ ስጋቶችን(Risk) ማስወገድ እንፈልጋለን።የሚገርመው ግን ከእነዚህ እየሸሸን ስንሄድ መኾን የምንፈልገውን ዐይነት ጠንካራ ስብዕና ያለው ሰው መኾን አለመቻላችን ነው።

ወንድሜ ጥቅሶችን መሰብሰብ አባባሎችንም መለጠፍ አንተን የምትፈልገው ዓይነት ሰው አያደርግህም የምትፈልገው ቦታም አያደረስህም። ይልቅስ ባወቅኸውና በተረዳኸው መጠን ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ ይኑርህ። ውሳኔ ደግሞ የቅጽበት ሥራ እንጂ ኺደት አይደለም።

በእርግጥ እንዳትወስን የሚያደርጉህ አንድም ፍርኃት አንድም ደግሞ ሰበባ ሰበቦች ናቸው።
ፍርኃት መፈተንህ ላይቀር ባጭር ታጥቀህ፣ ወኔን ይዘህ እንዳትገጥመው ፈተናውን አግዝፎ፣ አደጋውን አጉልቶ ይስልብህና በርደት(በመንቀጥቀጥ) ያጋጥምህና ሽንፈትህ እሙን ይኾናል።

ሰበባ ሰበቦች ደግሞ ሀገርህ ድሃ ናት፣ ባሕሉ ጥሩ አይደለም፣ ሰው ተበላሽቷል፣ ፖለቲካው አያስኖርህም፣ ዘረኝነት ሥር ሰዷል፣ ጥሩ ሴት(ሚስት)እኮ የለም፣ ኑሮ ተወዷል፣ የመኖሪያ ቤት የለም፣ ካልሰረቅህ አያልፍልህም፣ የስነሥርዓትና የስነምግባር ሰው መኾን ሞኝነት ነው፣ አባወራ ልኹን ብትል ማንም አይሰማህም፣….

እነዚኽን ኹሉ አልፈህ ያጽናኑኛል ብለህ የምትኼድባቸው የእምነት ተቋማት ውስጥ ደግሞ ያን ዐለም ላይ ንቀህ የመጣኸወን መከፋፈል አካል ነስቶ ልታገኘው ትችላለህ። ይኼን ጊዜ ከዐላማህ ገሸሽ እንድትል ከዐቋምህም እንድትንሸራተት ሰበብ ሊኾንህ ነው።

አንተ ቤትህን በአባወራነት ለመምራት ስትወስን፣ ስታደርግም ከሚስትህም ኾነ ከሌሎች የቤተሰብህ አባላት የሚመጣውን ፈተና አትፍራ።

ልብ አድርግ! ዐላማ አለህ፦ ስኬታማ ትዳር ልትመራ፣ኃላፊነት የሚሰማቸው ለሀገርና ለወገን ፍቅር ያላቸው ፈሪሃ እግዚአብሄርን የታደሉ ልጆችን ልታሳድግ ማላ(መሐላ) አለህ።

ስለዚህም ከጀግንነትህ ከዐላማህ ዝንፍ ሳትል ማላሕን ጭልጥ በማድረግ አስመስክር።

ዛሬ ዛሬ ፈተናን ለመቀበል ስጋቱንም ለመውሰድ ፈሪ የኾንነው ለምን ይመስልሃል፤ አዎን ከልጅነታችን ጀምሮ አደጋ ያመጣሉ የተባሉ ጨዋታዎችን እንዳንጫወት ስለምንከለከል ነው።

ፈተናን መድፈር የሚከተለውንም ስጋት መጋፈጥ ደግሞ በይበልጥ በማውራትና በመስማት ሳይኾን በተግባራዊ ልምምድ ብቻ ገንዘብ የምናደርገው ነው። መፈተንን ስትለማመደው ሊያስከትል የሚችለውንም አደጋ እያወክ ስትጋፈጠው በራስ መተማመንህን ይጨምራል።

ፈተናህን ለመጋፈጥ እውነተኛና ተግባራዊ የሕይወት ተሞክሮ ካላቸው ሰዎች ጋር በመኾን ልምዳቸውን ቅሰም። እነዚህ ሰዎች ዐለማዊ ትምሕርት ተምረናል፣ ብልኃተኛም ነን ሲሉ ፈተናንና አደጋውን በ”ብልሃታቸው” እያጎነበሱ፤ የሚያልፉ ከምቾት ኑሮኣቸው ፈቀቅ ብለው ራሳቸውንም ኾነ ቤተሰባቸውን፣ ሀገርንም የመለወጥን መራር ኺደትን የማይሞክሩ አይደሉም።
ወንድሜ ዐለም በተለይም ሴቶች በምንም መመዘኛ(በፍቅርም ቢኾን) ለፈሪ ቦታ የላቸውም(አይፈልጉምም)። ግን “ፈሪ ለእናቱ” እያሉ ፈሪ አድርገው ያሳድጉሃል። ትልቅ ስትኾን ግን በአባወራ ቦታም ስትገኝ አላደገብህምና ድፍረትን ከመለማመድ ይልቅ ለፍርሃትህ የዳቦ ስም እየሰጠህ መደበቅን ትሻለህ።

“እንደዚህ ብዬ ብወስን ሚስቴ ብታኮርፈኝስ፣ ብትጠላኝስ፣ ፊት ብትነሳኝስ፣ ወሲብ ብትከለክለኝስ….” ወዘተርፈ ትላለህ የሚገርመው ግን በልጅነት ፈተናን እንድትሸሽ አደጋንም እንዳትጋፈጠው “ፈሪ ለእናቱ” እያሉ ያሳደጉህ ዛሬ ግን ፍርኃትህን አይታገሱትም ስለዚህም በሕቡዕ(በምስጢር)ይርቁሃል።

ራስህን፣ አካባቢህን፣ ሀገርህን፣ በማየት፣ በማድነቅ፤ ከሌሎችም ስኬታቸውን፣ ሽንፈታቸውንና ተግዳሮታቸውን በመጋራት ራስህን በአባወራነት መሥራት….ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *