ቀጥቃጭ ለሰይፉ አባትም ለልጁ

 

ቀጥቃጭ ለሰይፉ አባትም ለልጁ 1ጀግናው ወንድሜ ቀጥቃጭ ሰይፍን እንዲሠራ አባትም ልጁን ይቀርጻል። ቀጥቃጭ ሰይፍን መሥራት ብቻ አይደለም ስለቱንም ዘወትር እንዲስል፤ አባትም ልጁን በጥሩ ስነምግባር የተቀረጸ ብቁ ዜጋ ማድረግ ብቻ ሳይኾን ይኼንንም እንዲጠብቀው ክትትል ያደርግለታል።

እስከዛሬ አንተን ብቁ ስለሚያደርጉ ቁምነገሮች ተጨዋውተናል። እነዚህያወራናቸውኹሉ በአንድ ቀን የሚፈጸሙ አልያም የአንድ ሰሞን ድርጊት አይደሉም። ዘወትር የምታሳድጋቸውና የምታድግባቸው የእድሜ ልክ ልምምድ እንጂ።

ዛሬ ደግሞ እየተሠራህ በምታድግበት ሕይወት ውስጥ ልጅህን ገና ከልጅነቱ ጀምረህ በአንተ አርአያነት ስለመቅረጽ እናውጋ።

ወላጅነት በተለይም ደግሞ አባትነት ልጆችን በስነምግባር በስነስርዓት መቅረጽና ኃላፊነት የሚሰማው ትውልድን ለሀገር ማትረፍን እንጂ ሙልቅቅ ያሉ ሀገራችውንና ወገናቸውን የሚጠየፉ ደንታቢሶችን ማፍራት አይደለም።

በአባትነትህ ልጆችህ ጥሩ ጥሩውን መመገባቸውንና መልበሳቸውን፣ ጥሩ ትምሕርትቤት መማራቸውን፣ መዝናናታቸውም ብቻ ሳይኾን ወገንን ጧሪ፣ ሀገርን ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት ከፍተኛ ጥረትና ትኩረት ልትሰጣቸው ይገባሃል።

ስለዚህም ከአንተም ኾነ ከእናታቸው በቂ ፍቅር ማግኘታቸውን እርግጠኛ ኹን። ሲቀጥልም በተፈጥሮአቸው ደስተኛ፣ በራሳቸው የሚተማመኑ፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው አድርገህ አሳድግ።

በተለይም ወንድ ልጅህ

ወንድ ልጅህና ሴት ልጅህ በተናጥል እንዲኹም ደግሞ አንድ ላይ በጋራ የሚማሩት አላቸው። ይህም ትምሕርት ይበልጡን በአንደበትህ ከምትነግራቸው ይልቅ አንተ ስታደርገው የሚያዩት ይኾናል።

ቤትህ ውስጥ የመሪነትህ የአስተዳዳሪነትህ ሚና ጎልቶ የሚታይ ከኾነ ወንዱ ልጅህ ይህንኑ ካንተ ይወርሳል። አልያ ግን ሚስትህ በአዛዥነት ሾር የምታደርግህና አንገትሀን ደፍተህ ድምጽህንም አተጥፍተህ ከሰጡህ በልተህ ካጣህ ተደፍተህ የምትኖር ከኾነ ወንዱ ልጅህ የወጣለት ፈሪ እና ምስኪን ይኾናል።

አንተ ራስህን በስነስርዓት ቀርጸህ የምትኖር ከኾነ ልጅህም የዚህ ፈለግ ተከታይ ነው የሚኾነው። ጠዋት የመነሳት ልምድ እንዲኖረው ከፈለግህ ጠዋት ተነስተህ አሳየው፣ መጽሐፍትን እንዲያነብም ከፈለግህ አንተም እያነበብክ ለእርሱም በእድሜው የሚኾን አስይዘው።

ድፍረት፣ ጥንካሬ፣ ኃላፊነት መውሰድ፣ ቃልን መጠበቅ፣ ተስፋን አለመቁረጥ፣ እግዚአብሄርን መፍራት ሰውንም ማፈር፣ ራሱን ማስከበር፣ ስነምግባር እነዚህን አንተ አርአያ ኾነህ አስተምረው።

እንዳትወድቅ፣ እንዳትሰበር እያልክ አንተ እየተሳቀቅህና እያሳቀቅኸውም ደፋር ሊኾን አይችልም። ቤት ውስጥ ቁጭ ብሎ ቲቪ እያየና ጌም እየተጫወተ ጠንካራ ሊኾን አይችልም። ለስህተቶቹ ሰበባ ሰበብ መደርደር እያስተማርከው ኃላፊነት መውሰድን አያውቀውም።

ልጅ ነው ጨዋታ ያታልለዋል እያልክ ቃሉን ሳይጠብቅ ሲቀር ካለፍከው ቃላባይነቱ ያድግበታል። የጀመረውን ሥራ እንዲጨርስ ከማበረታታት ይልቅ ደክሞኃል፣ ርቦኃል ብለህ ካስተጓጎልከው ጀምሮ መጨረስ አይኾንለትም። ድብድብ ኃጢአት ነው ብልግና ነው እያልከው ራሱንም ኾነቤተሰቡን የማይጠብቅ ፈሪ ታደርገዋለህ።

አንተ ስነስርዓት ኖሮህ ቤተሰቡን በስነስርዓት የምትመራ ከኾነ ከላይ የዘረዘርናቸውን መፈጸም ቀላል ነው። ትልቁ ነገር አንተን የምትሰማ ለሕግህ የምትገዛ ልጆችህ አንተን ይሰሙ ዘንድ አርአያ የምትኾን ሚስት ማግኘት ነው። እርሷ ማን ናት?

ወዳጄ ጠንካራ ብርቱ እና ግብረገብ ስንኾን ልጆቻችንም ኾነ ትውልዱ እንዲህ ይኾናሉ። ሀገርም ትጠቀማለች። አልያ ግን እኔ እና አንተ የራሳችንን ግዴታ ሳንወጣ በንዝህላልነት ከዘራናቸው ፍሬዎቻችን ቁም ነገር መጠበቅ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ይኾናል።

ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *