ከሳሽነት ከአሞጋሽነት 

ሳተናው ወንድሜ!
ዛሬ ሳተናው ያልኩህ አውቄ እና አስቤበት ነው። ለምን መሰለህ “ሳተናው” የምትለው ሰው አንድን ድርጊት ለመፈጸም ማሰብና መፈለግ ብቻ ይበቃዋል ማድረጉ የማይቀር ቅጽበታዊም ነውና።

ሳተናው አንተም ራስህን ለመለወጥ ወደ አባወራነት ከፍታም ለመውጣት ማሰብና መፈለግ ብቻ ይበቃሃል። ተስፈንጥረህ በልዕልና ቁብ ማለቱን በሰበብም ኾነ በክስ ሊገታ አይገባም።

ወዳጄ ከሳሽነት የጠላት ገንዘብ ነው፣ ያውም ያቅመ ደካማ። ላንተ ለሳተናው አይመጥንህም። ከሳሽ አቋሙ ልፍስፍስ፣ እምነቱ ደካማ፣ እውቀቱም ምንም ነው። ስሜታዊነት፣ ስንፍናና ጉስቁልናም ይገልጡታል።

በከሳሽነት ጠባይ ትዳር አይመመሠረትም፣ ቤት አይገነባም፣ መንፈሳዊነት አያድግም፣ ትውልድ አይጸናም ሀገርም እንዲሁ።

ሰው ኾኖ የማይስት እንጨት ኾኖ የማይጤስ የለምና የሰዎችን እንከን የመፈለግ/የማየት አይቶም አደባባይ ላይ የማውጣት ልምድ አይኑርህ። “የሰዎችን ስሕተት ዐይቼ ባርማቸውስ” ብትለኝ ግን አንተ ስሕተታቸውን እንዳየህ የእነርሱም ዐይን ያይ ዘንድ የቀናውን እውቀት አካፍላቸው እልሃለሁ።
አልያ ግን አንተ የማትስት፣ የማትወቀስ፣ የማትከሰስም ይመስልህና አወዳደቅህ እንዳይከፋ።

ወደ ከሳሽነት ጠባይ ከሚወስዱህ ተለይ
፩ ስንፍና
፪ መሃይምነት
፫ መንፈሳዊ ዝለት

፩ ስንፍና፦ ሰነፍ ሰው ከሳሽ ነው ሰዎች ቀድመው ስለ ስንፍናው እንዳይወቅሱት ሲል ሰበብ በመደርደር ጀምሮ ለስንፍና “የዳረጉትን” በመክሰስ ይጨርሳል።

ሳተናው ወንድሜ! አንተ ግን ራስህን ችለህ ትዳር ልትመሠረት፣ ቤት ልትሠራ፣ ሀገርም ልትገነባ እንዳለህ በዚህም ለስንፍና ቦታ ልትሰጥ እንዳይገባ አስተውል።

፪ መሃይምነት ፦ መሃይምነት ለከሳሽነት ከፍተኛ አስተዋጽዖ አለው። መሃይምነት ስልህ ግን የሒሳብ መዝገብ አያያዝ፣ የሕክሙና ሙያ፣ የምሕንድስና ጥበብ እና ሌሎችንም ትምሕርቶች አለመማር በእነርሱም የዲግሪና የዶክተሬት ብዛት አለመሰብሰብን አይደለም።

ስለተፈጥሮህ፣ ስለፈጣሪህ፣ ስለዓለምና በወስጧ ስላሉት ፍጥረታት ከእነርሱም ጋር እንዴት መኖር እንዳለብህ ስታውቅ ላንተም ያለህን ክብር ስትረዳ ከከሳሽነት ማዕቀፍ ትወጣለህ።

አልያ ግን የበታችነት ስሜት እየተሰማህ በዙሪያህ ያሉትን ኹሉ በዐይነ-ቁራኛ ማየት ድርጊታቸውንም መጠራጠር ብሎም በመክሰስ ሕይወት ትጠመዳለህ።

፫ መንፈሳዊ ዝለት
ሰው በመንፈሳዊ ሕይወቱ እያሽቆለቆለ መኾኑን ከምትረዳባቸው መንገዶች አንዱ ዘወትር ከአፉ ክስ ከምላሱም ሰበብ የማይለየው ሲኾን ነው። በእውቀት ማደግ ላለመቻሉ፣ አካሉ ብቁና ጤናማ ላለመኾኑ ሰበብ አልፎ ተርፎም አባቱንና እናቱን የመክሰስ ድፍረት ውስጥ የሚገባው በመንፈሳዊ ሕይወቱ ሲዳከም ሲዝልም ነው።

ሳተናው! መክሰስ ካለብህ ራስህን ክሰስ ለስሕተትህ ይቅርታ ጠይቅ ለኃጢአትህም ንስሃ ግባ። መንፈሳዊ ከኾንክ የይቅርታ ትርጉሙ የንስሃም አቅሙን ካወቅህ ከበታችነት ስሜት ከከሳሽነትም መንፈስ ትወጣለህ።

ከሳሽነት ከክብር የሚያወርድህ የተናቀ ድርጊት ነው። አንተ ሳተናው ደግሞ አባወራ፣ የቤትህ ንጉስ ነህ። ንጉስ ደግሞ በዙፋኑ ክስ ቢሰማ እንጂ መክሰስ ወጉ አይደለም።

“ምን ላድርግ?” አልከኝ? አሞጋሽ ኹን

ሳተናው! ልብ አድርግ ከማሞገስ ማመስገን ይቀድማል። ላንተ መልካም የሚያደርጉልህን አመስግናቸው፣ በወዳጆቻቸውም ፊት አሞግሳቸው። ይኼ በበለጠ በመልካም ሥራቸው እንዲተጉ፣ አውቀህ የናቅኸውን ድክመታቸውን እንዲያርሙ ያበረታታቸዋል። በቤትህም ሚስትህን በሙያዋ፣ በጠባይዋ አምግሳት ልጆችህንም እንዲሁ።

አባወራ በቤቱ ክስ ቢሰማ እንጂ ሚስቱንና ልጆቹን ወደ ውጭ ሲከስ አያምርበትም። ለማንስ ይከሳል? የመጨረሻው ስልጣን የእርሱ ኾኖ ሳለ። ይልቅስ አሞጋሽ ነው! በዚህም አርኣያ ትኾናቸዋለህ።

ሚስትህንስ ቢኾን ዘወትር የሚያቆለጳጵሳትንና የሚጠብቃትን አባቷን እግር ስመህ መውሰድህን ትረሳለህን? የምትወዳትንና የምትንከባከባትን እናቷን ትታ አንተን ፈቅዳ በመምጣቷ ይኽስ አይገባትምን?

ሚስትህንና ልጆችህን በመልካም ሥራቸው አሞግሳቸው፤ የድክመታቸውን ገመና በአደባባይ ከድነህ በቤትህ ግን አይናቸውን እያየህ ምከራቸው፣ ገስጻቸው፣ ተቆጣቸው ቅጣቸውም።

ሳምንት ብንኖር
አንተ በልዕልና ኃላፊነትን ስትሸከም ሚስትህ በትኅትናዋ ታርፋለች….. ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *