የተናቀው፣ የተገፋው አባወራና ስልጣኑ

ሳተናው ወንድሜ!
አንተ በቤትህ ባለ ሙሉ ስልጣን ነህ! የሀገር መሪ ለመኾን መመኘትና መኾን ከማሰብህ በፊት ሀገርን የምትገነባዋን ጡብ እርሷም ቤተሰብን መምራት ቻልበት።

ይኽች ትንሿ የቤተሰብ መሪነት አስተዳዳሪነት በተሰጠህ ስልጣን ከሥርህ ያሉ ሰዎችን ማገልገል የምትለማመድባት ቦታ ናት።

አዎን! ስልጣን ማገልገያ መሣሪያ ነው!

አስረጅ፦
ሳተናው! በምትኖርበት አካባቢ ያለው የወረዳችሁ አስተዳዳሪ ከወረዳው ነዋሪ ከፍተኛው ባለስልጣን ነው። ስልጣኑም ለአገልግሎት ይረዳው ዘንድ ከወረዳው ነዋሪ በላይ ቢያደርገው እንጂ በሰውነቱ ከማንም አይበልጥም።

ይኽ የወረዳ አስተዳዳሪ ግን ነዋሪውን ለማገልገል ሌሎችን የሚያዝበት፣ የሚመራበት የተከበረና የሚፈራ ስልጣን ሊኖረው የተገባ ነው። ለምሳሌ ነዋሪውን ስብሰባ ቢጠራ፣ የፅዳት ዘመቻ ቢያውጅ፣ ስለወረዳቸው ጸጥታ ቢያወያይ እሺ በጄ ብለው ሊታዘዙት ሊሰሙት ይገባል።

ነዋሪው ደግሞ በምትኩ ከወረዳው አስተዳደር የውሃ፣ የመብራት፣ የመንገድ፣ የጸጥታና ሌሎችም አገልግሎት ይፈልጋል። ይኽ ሁሉ አገልግሎት ከወረዳው አስተዳደር ሲጠበቅ ከነዋሪው ግን በዋነኛነት አንድ ነገር ይጠበቃል። እርሱም ለወረዳው አስተዳደር ሥርዓትና ደንብ መገዛት።

የወረዳውን አስተዳደርም ኾነ አስተዳዳሪውን ንቆ የሚጠበቅብንንም ግዴታ ወደጎን ገፍቶ አገልግሎትን መጠበቅ የማያስኬድ ስርዓት ነው።

ሳተናው!
ወደ ቤትህም ስትመጣ ተመሳሳይ ነገር ታገኛለህ። ትዳር ተቋም ሲኾን መሥራቹም እግዚአብሄር ነው። እርሱ ይኽን ተቋም ከአንድ ወንድ እና ከአንዲት ሴት ሲመሠርት ወንዱን በሴቷ ማሕፀን ዘርን የመዝራት፣ ተቋሙን የመምራት የማስተዳደርና ለተቋሙ ህልውና ራሱን እስከመሰዋት የሚደርስ ኃላፊነት ሰጥቶታል።

ለሴቷ ደግሞ ከወንዱ ዘርን ተቀብሎ የመክበድ የመውለድ ባሏን በመታዘዝ ለልጆቿ ደግሞ ትኅትናን በማውረስ የመንከባከብና የመመገብ ኃላፊነት ተሰጥቷታል።

እንግዲህ በስርዓት ብንሄድ ጤናማ፣ ደስተኛና ብቁ(ለእግዚአብሄር ዓላማ) የኾነ ትውልድ ማፍራት ይቻለናል። ይኽም አባወራ የቤቱ ባለሙሉ ስልጣን እንደኾነ(ኤፌ ፭፥፳-፳፰) ስልጣኑም ሚስቱንና ልጆቹን የሚያገለግልበት ከዚህም የተነሳ አንዲት ነፍሱን እንኳን አሳልፎ የሚያሰጥ ስርዓት ተሠርቶልናል።

ይኹን እንጂ እንዲህ ነፍሱን እንኳ ሳይቀር አሳልፎ ለመስጠት ዝግጁ ለኾነው አባወራ ግዴታውን ይወጣ ዘንድ ሚስቱና ልጆቹ በተራቸው ለተጣለበት/ ለተሰጠው ስልጣን ሊገዙለት በትኅትና ሊታዘዙትም የተገባ ነው።

ቀደም ብለን ባነሳነው አስረጅ የወረዳው ነዋሪ ለኑሮ የሚያስፈልጉት መሠረታዊ አገልግሎቶች አሉ። እነዚህን ለማግኘት ግን የወረዳው አስተዳደር ለሚያወጣው ሕግ መገዛት ደንቡንም ማክበር ግድ እንዲለው፤ እንዲሁም ሚስትህ ዘርን ከወገብህ፣ የአስቤዛ አቅርቦትን ከደመወዝህ፣ ደኅንነትን(ጥበቃን) ከጉልበትህ ትፈልጋለች። ልጆችህም እንዲሁ የአባትነትህን ፍቅር፣ ጥበቃ ክብካቤ ይሻሉ። አነዚህን ለማግኘት ግን የተሰጠህን የአባወራነት ስልጣን ማክበር፣ ቃልህን መጠበቅ አንተንም መፍራት አለባቸው።

ኾኖም ግን ሴቶችና ሕፃናት በአብዛኛው ይኽ ላንተ የተሰጠህ ኃላፊነት የፈጣሪህን ፈቃድ፣ ዓላማና መንግስቱንም የሚያስፈጽም መኾኑን አይረዱም(ከአምክንዮአዊነት ስሜታዊነት ስለሚያደላባቸው)። ፈጣሪህ ግን አንተን ቤትህን እንድትመራ፣ እንድታስተዳድር ሲያዝህ እንዲሁ በዘፈቀደ ሳይሆነ በአካል፣ በአእምሮና በስነልቦና ደረጃ አስፈላጊውን ትጥቅ(logistic) ሰጥቶህ ነው።

በተጨማሪም ሴቶችንንና ሕፃናትን እንዲታዘዙህ መመሪያ ሲሰጣቸው ፍጥረታቸውን ስለሚያውቅ አንተ ለእርሱ በመታዘዝ እንዳረፍክ እነርሱንም አንተን በመታዘዝ ባንተ ጥላ ሥር ሲያሳርፋቸው ነው።

ታዲያ ያለመገዛት ጠባያቸው ከየት መጣ? ስንል ተፈጥሮኣዊ(ባሕርያዊ) ያልኾነ በአፍአ ያለ ከአመጸኛዋ ዓለም የተወረሰ ጫጫታ መኾኑ ነው።

ሳተናው ልብ አድርግ!
ዘመነኛዋ ሚስትህ በአንደበቷ “አንተ ማነህ የምታዘኝ፣ የምትመራኝ” ብትልህ የሠራ አካላቷ ግን ለመታዘዝ፣ ለመመራትና ለመገራትም የሰጠ ነው። የአንደበቷ ዐመጽ ግን አንድም ከዓለም የእኩልነት አባዜ የወረሰችው፣ አንድም ያንተን አቅም የምትፈትሽበት ብልኃት አልያም አባቷ በስርዓት መክሮ ቀጥቶ ያለማሳደጉ ምልክት ነው።

አንተ ግን በዚህ አባወራና ስልጣኑ በተገፋበት በተናቀበትም ዘመን ብትኖርም ቅሉ ዘመን የማይሽረውን የፈጣሪህን ቃል በልብህ ሰሌዳ አትም። ቃሉን ግን ብትገፋ ዘመን የማይሽረውንም ዘመን አልፎበታል ብለህ ብትንቀው በሚስትህም ኾነ በልጆችህ ተንቀህ ታልፋለህ።

ሕይወት ስርዓት ይኖራት ዘንድ እርሱን የሚያሰፍንላት ኃይል ትፈልጋለች። ይኽ ኃይል ደግሞ ባለሙሉ ስልጣን ከኾነ አካል የሚመነጭ ነው። ቤትህ ስነስርዓት ይኖረው ዘንድ ስርዓትን የሚያሰፍንለት አካል/ኃይል ይሻል(ካንተና ከሚስትህ አንዱ)። ይኽ አካል/ኃይል ግን ስሜቱ የሰከነ ባለሙሉ ስልጣን ሲኾን እርሱም አንተ አ.ባ.ወ.ራ.ው. ነህ።

ስልጣንህ በእርሱም ውስጥ ያለው ኃይል በቤትህ ሊመጣ ላለው ስርዓት አመንጪም ኾነ ጠባቂ ነው። ግን እንዴት …… ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *