ከጀግኖች ገድል ጀግንነት ይቀዳል

ዛሬ የካቲት ፳፫ ጀግኖች አባቶቻችንና አስደናቂ ድላቸውን የምንዘክርበት ታላቅ ቀን ነው። እነርሱ በደም እና በአጥንት በከፈሉት ዋጋ እኔ ዛሬ በክብር ቆሜያለሁና ልዘክራቸው(ላስባቸው) ማልጄ ከልጆቼ ጋር ከንጉስ አደባባይ(ከአጼ ምኒልክ አደባባይ) ገስግሻለሁ።

ከሁለቱ ልጆቼ፦ከስድስት ዓመቱ ወንድና የአራት ዓመቷ ሴት(ሦስተኛዋ ትንሽ ናትና)ጋር ጠዋት አስራ አንድ ሰዓት ከእንቅልፋችን ነቅተን አስራሁለት ሰዓትም ከቦታው ደርሰን ድንቅ ጊዜ አሳለፍን። በአንደበታችን ዘመርን አባቶቻችንንም ኾነ ፈጣሪን አመሰገንን፣ በእጃችንም አጨበጨብን፣ ሽለላና ቀረርቶውን ሰምተን አይተንም አድንቀንም ተመለስን።

ለምን? ጀግንነት ድል አድራጊዎችንና ሥራቸውን በመዘከር፣ ፈለጋቸውን በመከተል በተግባር በመለማመድም ይወረሳልና፤ እኛም የነበራቸውን ወኔ የታጠቁትንም ጽናት ልንላበስ ወደናልና።

ሳተናው ወንድሜ!
ጀግንነት ዓላማ ይፈልጋል። ስለምን፣ ስለማን እና ለምንስ ምክንያት ራስህን ትሰዋለህ?
ጀግና ዓላማ አለው! እንዲሁ በዋል ፈሰስ ሰው ጀግና አይኾንምና። በግል በተሰማራህበት መስክ፣ እንደቤተሰብ መሪነትህ በተሰጠህ ሚና፣ እንደሀገር ተረካቢነትህ በደምና ባጥንት እንደተረከብከው አደራ፦ የግል፣ የቤተሰብም ኾነ ሀገራዊ ዓላማ ሊኖርህ ይገባል።

ቁርጥ ያለ ዓላማ ሲኖርህ በተለይም ደግሞ ዓላማህ ከዚህ በፊት ያልተሞከረና ያልተደፈረ ሲኾን (ልክ እንደዛሬዋ ዕለት በአፍሪካውያን ያልተደፈረ/ያልተደረገ ድል) እንደ ሰውነትህ ፍርሃት ይይዝሃል(ተፈጥሮኣዊ የስጋ ጠባይ ነውና)። ፍርሃት ተፈጥሮኣዊ ቢኾንም አንተ ግን የዓላማ ጽናት አለህና ፍርሃትህን ዋጥ አድርገህ ወደ ዓላማህ ትዘረጋለህ።

የፍርሃትህን መኖር ባትክድም፤ በድል ለመንገስ ግን ከፍርሃትህ በላይ በብቃት፣ በእውቀትም ልትናኝ ይገባሃል። ለምሳሌ እኔ የምነግርህ “ነገረ አባወራ” ለብዙዎች የማይቻል ጭርሱንም በዚህ ዘመን የማይሞከር ሲያስቡትም ውጤቱ የሚያስፈራ (“የሚወዱትን ያሳጣል” ተብሎ) ነው። ይኹን እንጂ ተፈጥሮህን ብትመረምር፣ የተሰጠንን ጸጋ(ላንተም ኾነ ለሴቷ) ከሚናው ጋር አሰናስለህ ብታስተውለው፣ የተፈጠርንለትንም ዓላማ ብታጤነው፤ የነገርኩህ ነገር ተፈጥሮኣዊ ሐቅ፣ ቢደረግ አግባባዊ፣ ለተፈጥሮአችን ተስማሚ፣ ውጤቱም አመርቂ መኾኑን ትገነዘባለህ፤ ፍርሃትህም ይርቃል፣ ለጀግንነትህም ቦታ ይለቃል።

ጀግንነትህ ደግሞ ከሦስት ነገሮች ይመጣል ወይም በሦስት ነገሮች ይመጣል
፩ ብዙውን ጊዜ ጀግና፣ ጀግንነት ጀግኖች የሚሉትን ቃላት ከሰማንባቸው የልጅነት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ከአካል ብቃትና ግዝፈት ጋር ይገናኝብናል። የሰውነት መጠንከር፣ መፈርጠም የተወረወረብንንም መመከት መቻል፣ ያሰብነውንም ከዳር ማድረስ የሚችል አካላዊ ብቃት ለጀግንነታችን አስተዋጽዖ እንዳለውም እንሰማለን፤ እንረዳለንም።

በድሮ አባቶቻችንም ዘንድ አካላቸውን ጠላት ቢመጣ መመከት እንዲችል ሚስቶቻቸውን ልጆቻቸውን ብሎም ሀገራቸው መታደጊያ እንዲኾን በተለያዩ ስፖርታዊ ጨዋታዎች ያጠነክሩት ነበር። ይኽም አድካሚ እና አሰቃቂ በነበረው ከእነርሱ ወቅት ጦርነት መሐል በጀብደኝነት ለመዋጋትና በድል ለመውጣት ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል።

ይኹን እንጂ ጉልበት ቢዳብርም ቅሉ አእምሮ በተገቢው እውቀት በስርዓት እስካልሰለጠነ ድረስ ፍርሃት መንገሱ፣ ሰውነት ጡንቻን ተሸክሞ ሃሞተ ቢስ ወኔ አልባ መኾኑ አይቀርም። ስለዚህም ሰውነታችንን የሚያዘውን አእምሮ በእውቀት ልንገነባው ግድ ይለናል።

፪ አእምሮአዊ ጀግንነት
በዚህ ባለንበት ዘመን ሰብዓዊ ተፈጥሮአችንን ሳናጣ ኑሮን ለማሸነፍ በምናደርገው ትግል የሚደርሱብን ፈተናዎች በመጠንም ኾነ በዓይነት ከአባቶቻችኑ ዘመን እጅጉን የበዙ ናቸው። ይኹን እንጂ መፍትኼዎቻቸው ደግሞ በብዛትና በዓይነት ከቀደመው ዘመን በተሻለ ወደኛ ቀርበውልናል አስተዋይ ልብ አጣን እንጂ።

ለዚህ ፍቱን መድኃኒት ደግሞ አእምሮዎን ለቦውን ሳልብን አሳድርብን እያሉ ማንበብ ነው። አባቶቻችን የእጃቸው አሻራ ያረፉባቸው ድንቅ ዓለማዊ ሥራዎች እንዳሉ ኹሉ መንፈሳዊ እውቀትንም ገንዘብ ያደረጉ እርሱንም ይኖሩት እንደነበር ከታሪክ ማሕደራቸው ይነበባል። ይኽ ደግሞ ለእውነት፣ በእውነት በጀግንነት ለመቆም አብቅቷቸዋል።
፫ መንፈሳዊ(ስነልቦናዊ) ጀግንነት
፫.፩ ልክ ነው ብለህ ያመንክበትን ዓላማ ከዳር ለማድረስ የምትከፍለው ዋጋ፣የምታሳየው ቁርጠኝነት ነው
፫.፪ በቤትህ ላቆምከው ሕግ፣ ለዘረጋኸው ስርአት፣ ለቃልህም ታማኝነትህን መግለጥ በተለይም ከቀደመው(ከአእምሮአዊው የእውቀት) ጀግንነትህ ተነስተህ ሚስትህና ልጆችህ ምን እንደሚያስፈልጋቸው ስትረዳና በምንስ እንደሚጎዱ ስታውቅ እርሱንም ስታምን መንፈስህ አይረበሽብህም። የልቦናህም ቁርጠኝነት ይጨምራል፤ ከስሜታዊነት ርቀህ በእውቀትም መጥቀህ ምክንያታዊ ኾነሃልና።

ስነልቦናዊ ወይም መንፈሳዊ ጥንካሬ ስለራስህ ተፈጥሮ ያለህ እውቀትና በፈጣሪህ ላይ ያለህ እምነት ሲጨምር ያይላል(ይጨምራል)።

የእለቱን ገድል(የአድዋን) ስታነብ ወይም ዕለቱን የሚዘክሩ ድርሳናት ስታገላብጥ አልያም ስትሰማ የሚነግሩህ ይኽንኑ እውነት ነው።

ሳተናው!
ትዳርህ፣ ልጆችህና ሀገርህ ጀግና ይፈልጋሉ። ዓለም በቀጣፊ መገናኛ ብዙኃኖቿ ተጠቅማ ኹን የምትልህን ለማዳ አንበሳ ወይም የሳሎን ውሻ አትኹንላት። ያንተን ፍዝነት ተጠቅማ ትዳርህን ልታፈርስ፣ ሚስትህንም ልታስት፣ ልጆችህን ልትበትን ሀገርህንም ልትወርስ ነውና።

ጀግንነትን ከአባቶችህ ተማር ውረሰውም። የተፈጠርክበትን ዓላማ ተረድተህ ስታበቃ አንተ በስርዓት በመኖር ልጆችህን በስርዓትና በስነምግባር አሳድግ።
…ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *