ለልጆችህ ከምትሰጣቸው ስጦታዎች ኹሉ የሚበልጠው

ሳተናው!
ለልጆችህ ከምትሰጣቸው ስጦታዎች ኹሉ አንተ ትበልጣለህ።ይኽም ለእነርሱ በምትሰጣቸው ጊዜ ይለካል። የነገ ማንነታቸውን በመቅረጹ ዙሪያ ያንተ ሚና ከፍተኛ ነው።

ለልጆችህ ውድ ዋጋ ያላቸውን(በገንዘብ) ዕቃዎች ገዝተህ የመስጠቱ ነገር አያስጨንቅህ። ይኽንንም በሚያደርጉ ወላጆች አትቅና። የልጆችህ ልጅነት ተመልሶ እንደማይመጣ ስታውቅ ከእነርሱ ጋር በሚኖርህ ጊዜ በነገ ሕይወታቸው አብቦ የሚያፈራን ዘር ዝራበት።

ይኼን ለማድረግ ደግሞ መጀመሪያ ራስህን ቀጥሎም ሚስትህን በስነስርዓትና በስነምግባር መግራት ግድ ይልሃል። ቤትህን በፍቅር ብትመራም ፍቅር ግን ያለ ስነስርዓትና ስነምግባር አይኾንም፤ ካለዚያ ግን በፍቅር እመራበታለሁ(ላልቶ) እመራበታለሁም(ጠብቆ) የምትለውን አቋምህን መዘባበቻ ቀጥሎም ጥራዝ ነጠቅ ትውልድ ማፍሪያ ይኾናል።

ሳተናው!
አንተ ራስህን ከስጦታዎች ኹሉ አልቀህ መስጠትን እወቅበት! በምንም ዓይነት መልኩ ልጆችህ አንተን ሲያዩ ጣፋጭ፣ መሓላቸው ስትገኝ ሲኒማ፣ ገንዘብም ስታወጣ መጫወቻ ዕቃ እንዲያስቡ አይኹን።

ይልቅስ አንተን ሲያገኙ ዛሬ ደግሞ ምን እንሥራ? ምን እናንብብ? ይበሉ እንጂ።
ለዚህ ደግሞ፦

፩ኛ አብረሃቸው ጊዜን አሳልፍ
ይኽን ስል ምናልባትም ብዙዎቻችን “ይኽንንማ እናደርገዋለን” እንላለን። ነገር ግን አብሮነታችንን በምን መልክ እንገልጸዋለን? ወንድሜ እኔ ግን አብረሃቸው TV/ ድራማ ማየትን ማለቴ አይደለም። ይልቅስ ከቤት ውጪ ወስደሃቸው አብራችሁ በጨዋታና በሥራ የምታሳልፉትን ጊዜ ማለቴ እንጂ። በዚህ ወቅት ከልጆችህ ጋር ስትጫወት የምትወያይባቸው ርዕሶች ይነሳሉ፣ ቀልዶች ይፈጠራሉ፣ ሕይወትንም ቀለል አድርገው ማየት ይችላሉ።

ይኽ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ የንግግርን፣ የጨዋታን፣ የቀልድን ስርዓትንና አግባብን ታስተምራቸዋለህ። ከ smart phone, video game, እና ከTV ነጻ ኾናችሁ ዐይን ለዐይን እየተያያቸሁ፣ ሰውነት ለሰውነትም እየተነካካችሁ፣ ትንፋሽ ለትንፋሽም እየተለዋወጣችሁ የሚማሩበት ፍቅራችሁም የሚደረጅበት ነው።

፪ኛ አብረሃቸው አድካሚ ሥራን ሥራ
አንዳንድ ጊዜ ልጆችህን ይዘህ ከቤታችሁ ራቅ ወዳለ ቦታ በእግራችሁ ሂዱ። ይኽን ለማድረግ መጀመሪያ የት ደርሳችሁ መምጣት እንደምትፈልጉ ወስኑ። ከዚያም በጉዞአችሁ ላይ ድካም እንኳ ቢኖር ላለማቋረጥ ተበረታቱ። በምንም መልኩ ግን ደርሰን እንመጣለን ካላችሁት ቦታ ሳትደርሱ አትመለሱ።

ይኽ ልጆችህን ሊሰሩት ያላቸው ሥራ ሕልማችው ወይም ዓላማችው ከኾነና አስቀድመው አስበውበት ከተነሱ ምንም አድካሚ እንኳ ቢኾን እንኳ በጽናት ከዳር ማድረስ እንደሚቻላቸው ነው።

፫ ፍለጋህን አሳያቸው
ልጆች የአንደበትህን ቢሰሙም በአእምሮኣቸው የሚቀረጸው፣ በልባቸውም የሚያምኑት የሚያደርጉትም አንተ የምታደርገውን ነው። ስለዚህም እንዲያነቡ እንዲያጠኑም ትፈልጋለህ አንብቡ ብቻ ሳይኾን አብረሃቸው አንብብ፣ ቤተክርስቲያን እንዲሄዱ ከምስጢራትም እንዲካፈሉ ትፈልጋለህ ይኽንንም አድርግ፣ ሀገራቸውን እንዲወዱ ደሃን እንዳይበድሉ ትፈልጋለህ ሰው አየኝ አላየኝ ብለህ ከምታጠፋው የሀገር ኃብት ታቀብ፣ ካለህም ለደሃ ስታካፍል ስትራራም አሳያቸው።

፬ ይወድቁ ዘንድ ተዋቸው
ልጆችህ ይወድቁ ዘንድ ስትተዋቸው
፬.፩ በሕይወት ውጣ ውረድ መውደቅ የጉዞው አካል እንደኾነ ይማራሉ
፬.፪ ለምን እንደወደቁ ያስተውላሉ
፬.፫ ሲወድቁ ከማልቀስ ይልቅ በቀጣይ ላለመውደቅ መፍትሔውን ይፈልጋሉ
እኔና ወንዱ ልጄ አብረን ስንኾን በተለይም እኹድ እኹድ የምናደርጋቸው ነገሮች ሚስቴን ያናድዷታል ምክንያቱም “ወድቆ ይጎዳል” ስለምትል። የሚገርማችሁ ግን በእነዚህ ልምምዶች ልጃችን ዐዲስ ነገር ለመሞከር ደፋር፣ እኔ ትችላለህ ካልኩትማ “ምንተስኖት”።

ልጄ ወድቆ እንዲጎዳ ባልፈልግም እኔ በሕይወት እያለሁ ግን ከውድቀቱ እንዲማርና ተመሳሳይ ስህተትም ሳይሠራ እንዴት ካሰበው መድረስ እንዳለበት እንዲያውቅ እፈልጋለሁ።
ሳተናው! ልጅህ ሲወድቅ “ተው ትሰበራለህ” ብለህ አታስቀምጠው ይኽ በሕይወቱ ዐዲስ ነገር ምናልባትም ራሱን፣ ቤተሰቡን፣ ሀገሩን የሚያነሳበትን ርዕይ እንዳይሞክር በፍርሃት ወኔውን ይሰልባልና።

ስለዚህም ለልጆችህ የምትሰጣቸው ቁሳዊ ስጦታ ስለሌለህ፣ ገንዘብም ስለሚያጥርህ ከጓደኞቻቸው በታች ይኾናሉ ብለህ ያላዋቂ ኃሳብ አይግባህ። ይልቅስ አንተ በሕይወት ስላለህላቸው ኃሴትን አድርግ፤ እንዴትስ አብረሃቸው በመኾን ራሳቸውን እንዲያቁ፣ እንዲችሉና ሀገራቸውንም እንዲጠቅሙ እየያደረግህ አሳያቸው።….. ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *