Feminism በአባወራው እይታ

ውድ ወንድሜ ይኼ ጽሑፍ ያንተን ምቾት ለመጠበቅ፣ ደስም እንድትሰኝበት የተጻፈ አይደለም። የታዘብኩትን እውነት ስለመመስከር እንጂ።ለዚህም ኹልጊዜ እንደምመክርህ ኾደ ባሻነትህ እስካለቀቀህ ድረስ አታንበው።

በሥነ ፍጥረት እንደምንረዳው አብዛኛዎቹ ፍጥረታት ጥንድ ጥንድ ኾነው ተፈጥረዋል።ይኽ ጥንድነታቸው ፈጣሪ የዘራቸውን ቀጣይነት እንዲረጋገጥ ኾን ብሎ የከወነው ነው።የሚገርመው ግን ይኼን ጥንድነታቸውን የመሠረተው በልዩነት መኾኑ ነው። ወንድ እና ሴት አድርጎ በዚኽ ልዩነት ቢፈጥርም ቅሉ ተመጋጋቢ፣ ተደጋጋፊ፣ ተሟይ(የሚሟሉ) አደረጋቸው፣ አዋደዳቸው፣ አፈላለጋቸው እንጂ ልዩነታቸው የሚያራርቃቸው፣ የሚያጣላቸው አልነበረም።

በዚህ አምሳያ ዐለማችን ላይ በተቃራኒነታቸው ተዋደው፣ ተሳስበው የሚኖሩ፣ ልዩ ያደረጋቸውን ተፈጥሮኣዊ ጠባዕይ ባጎሉ ቁጥር በመካከላቸው ያለውን የመሳሳብ ኃይል የሚያሳድጉ፣ በዚህም ኃይል ከእነርሱ አልፈው ለሌሎች የሚበቁትን ፦
>>> የማግኔትን ተቃራኒ ዋልታዎችንና በመካከላቸው ያለውን ማግኔጢሳዊ ኃይል (magnetic field)
>>> የኮረንቲ ወይም የኤሌክትሪክ ጫፎችንና(charges) በመካከላቸው ያለውን (electric field) አስተውል።

እንደላይኛው ማሳያ ኹሉ እኛም ተፈጥሮ የሰጠንን የጾታ ልዩነት ይዘን፣ ይዘን ብቻም አይደለም አበልጽገን፣ አበልጽገን ብቻ አይደለም፣ በኑሮ ልምምድም አዳብረን ብንገኝ በተቃራኒ ጾታ ዘንድ የሚያስፈልገን፣ የሚያስወድደን ውበታችን፣ የሚያቀራርበንም ስበታችን፣ አንድም የሚያደርገን ኃይላችን ነው።

ኾኖም ግን አኹን ባለንበት ነባራዊ ወቅት ሴቶችን “በጾታቸው ምክንያት ለሚደርስባቸው ጭቆና እንቁም” በሚል መሪ ኃሳብ የተነሳው Feminism ይኼን የጠቀስነውን የጾታ የልዩነት አጥር በእኩልነት ስም ሲንድ በዚህም የሰው ዘርን ሲጎዳ ይስተዋላል።

ሴቶቹ በተፈጥሮ ከወንዶቹ ጋር በሕብረት በአንድነት ይኖሩበት ይሟሉበትም ዘንድ የተሰጣቸው ከወንዶቹ የተለየ ልክ አላቸው። ወንዶቹም እንዲሁ ከሴቶቹ ጋር በሕብረት በአንድነት ይኖሩበት ይሟሉበትም ዘንድ የተሰጣቸው ከሴቶቹ የተለየ ልክ አላቸው። ይኼ ልክ በሚመሠርቱት የጋራ ሕይወት ውስጥ የሚኖራቸውን ሚና ግምት ውስጥ የከተተ እርሱንም የሚያደረጅ አንድነታቸውንም የሚያጸና ነው።

በfeminism በኩል የመጣው የሴቶች “እኩልነት” ግን ሴቶች በማሕበራዊው ተሳትፎም ኾነ በፖለቲካው ምሕዳሩ ከወንዶች እኩል ድምጻቸው እንዲሰማ ብቻ ተወስኖ አልቀረም። ይልቁንስ ወንዶች የያዙትን የቤተሰብም ኾነ የማሕበረሰብ ስልጣን የመጋራት አልያም የመገልበጥ ሴራ ይዞ ብቅ አለ እንጂ።

በዚህም ምንም እንኳ ሴቶችን ከወንዶች ማስተካከል ቢባልም (ወትሮውንም የወንዶቹ እና የሴቶቹ ልክ ለየቅል ነበርና) ሴቶቹን ከነበራቸው ሚና ያፈናቀለ፣ ራሳቸውን ኾነው ተጸጥሮኣዊ ስጦታቸውን አዳብረው ከወንዱ ጋር ተሟልተው አንድ መኾን የሚችሉበትን ጠባዕይ ያሳጣ፣ መሟላትን መተጋገዝን ገፎ መፎካከርን ያላበሰ፣ የተከበረውን ሴትነት ያዋረደ፣ ሴቶቹንም ከፈጣሪያቸው ፈቃድ እና ኃሳብ አውጥቶ የጠላት መጠቀሚያ ያደረገ ምን አለፋችሁ በአካልና በመንፈስ ሴቶቻችንን ያቆረቆዘ ነው።

ስለኾነም feminism በእኔ አተያይ ሴቶችን በስነ ልቦና ደረጃ አቆርቁዟልና ሴት-አቆርቋዥ ስለው ከዚህም ሴታቆርቋዥ ይገኛል።
ሴታቆርቋዥ፦ በአፍኣ “ለሴቶች እኩልነት ቆሜያለሁ” የሚል በኅቡዕ ግን ሴቶችን ከተፈጥሮኣዊ ክብራቸው የሚያወርድ፣ የሚያዋርድና የሚያቆረቁዝ በዚህም ደስታቸውን የሚያጠፋ ነው።

***ሴታቆርቋዥ (Feminism) ለሴቶች እንደኾነ ንፋስም ለገለባ ነው
Feminism ሴቶችን እንደ ገለባ ነው የተጫወተባቸው። ከፍሬ መሃል ለይቶ ወደ ሰማይ ሲሰቅላቸው እውን ከፍ ያደረጋቸው ልከኛ ቦታም ያገኘላቸው ይመስላቸዋል። ነፋስ ገለባን በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ዐየራት ከፍታ አውጥቶ አፋፉን ጨርሶ ገደል ላይ ሲደርስ ይለቀዋል። ያንጊዜ የነፋስ ትከሻ የራቃቸው ገለቦች በሕዋሕው ላይ ይቀራሉ መሬት መያዝ በአንድ ቦታ መወሰንም ያቅታቸዋል።የማንም ሳይኾኑ በአራቱም አቅጣጫ ሲዋከቡ መኖር እጣ ክፍላቸው ይኾናል።

Feminism ሴቶቻችንን በተለይ በሦስቱ የሕይወት ክፍሎች ጎድቷቸዋል እነርሱም፦
1ኛ በአደባባይ
በሥራ፣ በትምህርት፣ በስኬት (career) በሚባሉ ደላይ የነፋስ ትከሻዎች ተሸክሞ እያከነፈ ይወስዳቸዋል። በዚህም ፈጣሪ በማሕበረሰቡ ውስጥ የሰጣቸውን ቦታ ያናንቅባቸዋል። “እንዲህ ብለሽ ለወንድ እጅ እንዳትሰጪ፣ተማሪ፣ ሥሪ ቀስ ብለሽ ታገቢያለሽ….” ይባላሉ እነርሱም ከዲፕሎማ፣ ዲግሪ፣ ማስተርስ፣ ፒ. ኤች. ዲ. ሲሉ የእናትነት ወጉን፣ የማግባት ጥቅሙን ሳያውቁት ያከንፋቸዋል። አፋፉ ላይ ከገደሉ መጀመሪያ(ዐለማዊ ክብሩን ሲደረሱበት) ይለቃቸዋል። በዚህ ጊዜ ያ ልጅነት ያ ለምለምነት ተመልሶ ላይመጣ ሄዷል፤ ማግባትና መውለድም ጊዜው አልፎበታል፤ ሕይወትንም ትርጉም ያጡባታል። ኃብት ንብረት አፍርተው ኑሮአቸውን በዓለማዊ ቁሳቁስ አደራጅተው ሕይወታቸው ግን ኦና ይኾንባቸዋል።

ሴታቆርቋዥ(Feminism) እግዚአብሄር በትውልዱ ውስጥ ያለውን ዓላማ ስለ ስጋዊ ጥቅም ከወንድ ጋርም ስለሚደረግ አላስፈላጊ ፉክክር ሲል ያስጥላቸዋል። እነዚህ ሴቶች መቼም የወሲብ ፍላጎት አላቸው ነገር ግን እንዳያገቡ ሴታቆርቋዥ(Feminism) እንደ ዐላማ አይቆጥረውም ስለዚህም ከማንም የሚጓተቱ ነውራቸውንም ከክብር የቆጠሩ ይኾናሉ።

2ኛ በእልፍኝ
ሴታቆርቋዥ(Feminism) በትዳር ውስጥ ያሉትን ሴቶች ለባሎቻችሁ አትገዙ ይላቸዋል። እኩል ኾናችሁ ሳለ መታዘዝ መመራት ውሳኔንም ኾነ ተግሳጽን መቀበል አይጠበቅባችሁም ይላቸዋል። በዚህም ብዙዎች ከባላቸው ምንም ዓይነት ትዕዛዝ ለመቀበል ፈቃደኛ አይደሉም። “ያለትዕዛዝ መኖር አይቻልም ወይ?” ብለውም ይሞግታሉ። በዚህም ፈለግ ልጆቻቸውን ያስከትላሉ። በውጤቱም በአባወራው ላይ ያመጸ ቤተሰብ ይገኛል። ይኽ ደግሞ መረን የኾነ ትውልድን ያመጣል። የሚገርመው የባልየው ልዕልና የባልየው ውሳኔ ከማንም በላይ እርሷን የሚጠቅም ነበር። በምርጫ ብዛት እና በስሜት ማዕበል ለሚናጠው ውስጧ ወደቧ እርሱ ነበርና።

3ኛ በመኝታ ቤት
ሴታቆርቋዥ(Feminism) ሴቷን በመኝታ ክፍሏ ተራክቦ ላይ ባለመብት አድርጎ ሲያስቀምጣት ተራክቦዋን ልክ እንደ አንድ የኑሮ አጀንዳ በመነጋገር ላይ የተመሠረተ እና የተወሰነ ነው ይላል። ብዙውን ጊዜም እንደ መደራደሪያ ኃይል(bargaining power) ይወሰዳል።ይኽም ሲኾን ወሲቡ ተፈጥሮአዊ መሳሳቡን(Intimacy) አጥቶ በአደራ ያስቀመጡትን እቃ እንደመጠየቅ እንደመለመንም ይመስላል። በስተመጨረሻም ወደ ስሜት አልባ ወሲብ ተሸጋግሮ ጭርሱን ይጠፋል፣ ትዳርም ይፈርሳል።

ሲጠቃለል
በአጠቃላይ ከላይ ባየናቸው ሦስት መስኮች(በአደባባይ፣ በእልፍኝ፣በመኝታ ቤት) በተለይ ሴታቆርቋዡ (Feminism) የሴቶችን አካላዊም(physiological) ኾነ አእምሮአዊ(mental namely; conscious &subconscious make up) አወቃቀር ያላገናዘበ ነው።
ገለባን አለሁልሽ ብሎ አፋፍ ላይ ወስዷት ከላይ መሰቀሏን ከኹሉ በላይ መኾኗን አጣጥማ ሳትጨርስ ከሥሯ ተሰውሮ ሕዋሕው ላይ የሚያስቀራት፤ ተጣብቃበት ከምትኖረበት ፍሬ ለይቶ ያንዱም ሳትኾን ግን ደግሞ ለማንም የሚዳርጋትን ንፋስን ይመስልብኛል።….ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *